መልካምነት በእናንተ ውስጥ ይኖራልን?

Roy Oksnevad

ትርጉምና ቅንብር በአዘጋጁ

መልካምን ሕይወት ለመኖር የሚደረገው ጥረት ማለቂያ የሌለውና አድካሚ ስራ ነው፡፡ ብዙዎቻችን መጥፎዎቹን ሥራዎቻችንን ለመቆጣጠር እንታገላለን፡፡ መልካምንም ተግባር ለመፈፀም እንጥራለን፡፡ ይህም የእኛን ሙሉ ትኩረትና ሙሉ ኃይላችንን ይወስድብናል፡፡ ከዚህም በላይ እኛ በገለልተኛ ዓለም ውስጥ አንኖርም፡፡ ይህ ዓለም ፈተናዎች፣ የግድ የሚጠይቃቸው ነገሮች እና ችግሮች አሉት፡፡ እንደምናውቀው መኖር የሚገባንን ያህል ለመኖር ስንል የቀረንን ትንሽ ኃይል ይጨርስብናል፡፡  እግዚአብሔር ትግላችንን ያውቀዋልን? ድካሞቻችንን አያስተውላቸውምን? ወይንስ እግዚአብሔር የተለየ ዓይነትን ልምምድ እንድንለማመድ - ትክክል የሆነውን ለማድረግ ኃይላችን ያለበትን ይፈልጋልን?፡፡

ፍጥረት፦

እግዚአብሔር የሰውን ልጅ የፈጠረው ያለምንም ኃጢአት ወይንም ድካም ነበር፡፡ የመጀመሪያዎቹ ሰዎች አዳምና ሔዋን ፍፁማንና ሙሉዎች ነበሩ፡፡ አዳምና ሔዋን መልካምም ነበሩ እንዲሁም ትክክል የሆነውን ነገር ሁሉ ለመስራት ይፈልጉ ነበር ምክንያቱም የመልካምነት ተፈጥሮ በውስጣቸው ነበረና፡፡ በውስጣቸውም ምንም መጥፎ ወይንም ክፉ የሚባል ነገር በጭራሽ አልነበረባቸውም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም በእርግጥ የሚለው እግዚአብሔር ሰውን ከፈጠረ በኋላ የፈጠረው ነገር ሁሉ መልካም መሆኑን እራሱ መናገሩን ነው፡፡ መልካምነት ለሰዎች ሕይወትንና የሕይወትን አቅጣጫ ሰጥቷቸዋል፡፡

ታዲያ እኛ እግዚአብሔር እንደፈጠርን ያልሆንነው ለምንድነውን? (ለዚህ መልሱ እንደሚከተለው ነው)፡-

ውድቀት፦

ከአዳም ጀምሮ የሰው ልጅ ጠላት የሆነው ሰይጣን እግዚአብሔር የፈጠረውን ለማጥፋት ፈልጓል፡፡  አዳምና ሔዋን እግዚአብሔርን እንዳይታዘዙ ሰይጣን ፈተናቸው እነሱም በእሱ ፈተና ወደቁ፡፡ ሰዎችም እግዚአብሔርን ባልታዘዙበት ጊዜ ሁለት ነገሮች ሆኑ፡፡

በመጀመሪያ፡- ክፉ በውስጣቸው ገባ፡፡ ከዚያን ጊዜም ጀምሮ እያንዳንዱ ሰው ከክፉ ጋር ወይንም በውስጡ ከሚኖረው መጥፎ ጋር መታገል አለበት፡፡ ይህ ክፉ ተፈጥሮ እግዚአብሔር ለፍጥረቱ የነበረው የመጀመሪያ  ዕቅድ አልነበረም፡፡

ሁለተኛው ደግሞ፡- በሰዎች ውስጥ የነበረው መልካም በኃጢአት ሲወድቁ ሞተ፡፡ መልካምነት ምን ማለት እንደሆነ እንረዳለን ነገር ግን መልካምነት በራሱ ሕይወት የለውም፡፡ በእርግጥ መልካምን ለማድረግ እና ክፉው ከእኛ ውስጥ እንዳይወጣ ለማድረግ ያለና የሌላ ኃይላችንን ሁሉ እናውላለን፡፡ በምንደክምበት ጊዜ ወይንም አንድ ሰው ሲያሳዝነን በውስጣችን ያለው ክፉ መልካሙን ሁሉ ያሸንፈዋል፡፡ አዎ መልካሙ ነገር እንዲሆን የእኛን ጥረት ይጠይቃል፡፡

ለምሳሌም ያህል አንድ ባል በሚስቱ አካባቢ እንዴት መመላለስ እንዳለበት ያውቃል፡፡ እሷን ማፍቀርና ተገቢ የሆነንም እንክብካቤ ለእሷ ማድረግ እንዳለበት ያውቃል፡፡ ነገር ግን ይህንን የሚያውቀውን ማድረግ፣ የሚገባውን መልካምን ነገር ማድረግ አይችልም፡፡ ልክ እንደዚሁ ወላጆች ለልጆቻቸው ጥንቁቅና የሚረዷቸው ለመሆን ይጥራሉ፣ ነገር ግን እርስ በእርስ በሚኖረው ግንኙነታቸው ክፉው ጎናቸው ይወጣና ይታያል፡፡ ልጆችም እንኳን ክፉ መሆንን መማር አያስፈልጋቸውም፡፡ እኛ ያለማቋረጥ መልካም እንዲሆኑ ስናስተምራቸውና ስናርማቸው ነው የምንገኘው፡፡ ነገር ግን እኛ ከምናደርገው ትጋት የሞላበት ጥረት በሻገር እነሱ ክፉን ነገር ሲያደርጉና እንዲሁም መልካምን ነገር ለመማር በጣም የዘገዩ በመሆን ይገኛሉ፡፡

እናንተና እኔ በሕይወታችን ውስጥ ያለውን ክፉ ነገር ለመቆጣጠር ልናደርግ የምንችለው ምንድነው? በውስጣችን ላለው መልካም ነገር እንዴት አድርገን ነው ሕይወትን እንደገና ልናመጣለት የምንችለው?

ሕይወት የማደስ ሙከራ፦

በሕይወታችን ውስጥ ያለውን መልካም ነገር ስለማደስ ሰዎች ልዩልዩ ሐሳቦችን ይሰነዝራሉ፡፡ አንዳንዶች ለዚህ ቁልፉ እውቀት ነው ይላሉ፡፡ ሰዎችን ብዙ ባስተማርናቸው መጠን መልካምን ለማድረግ ይለወጣሉ ይላሉ፡፡ ነገር ግን ሰዎች እውቀታቸውና የአዕምሮ ችሎታቸውን በመጠቀም የራሳቸውን ሁኔታ ሲያመቻቹ ወይንም ሌሎች ሰዎችን መጠቀሚያ ሲያደርጉ (ይታያሉ)፡፡ ስለዚህም እውቀት ሕይወትን ወደ መልካምነት አያመጣውም፡፡

ሌሎች ደግሞ ሥነ-ስርዓት (ዲሲፕሊን) ቁልፍ ነው ይላሉ፡፡ እኛ በሕይወታችን በጣም ስነ ስርዓት ያለን ከሆንን ማለትም - በሐሳባችን፣ በልማዳችን፣ በእንቅስቃሴያችን ወ.ዘ.ተ. ከሆንን በጣም እንሻሻላለን የበለጠ መልካምን እንሰራለን ይላሉ፡፡ ነገር ግን ለእኛ በጣም ቅርብ የሆኑ ሰዎች በእውነት ምን ዓይነት ሰዎች መሆናችንን ያውቃሉ፡፡ በስነ ስርዓተኝነት በአዕምሮአችን ውስጥ የራሳችን ዓለም እንፈጥር ይሆናል፣ ሆኖም አሁንም እኛ እየኖርን ያለነው በዚህ ምድር ውስጥ ነው፡፡ ብዙው የስነ ምግባር ልምምድ በሕይወት ውስጥ መልካምን ለማምጣት ብቃት የለውም፡፡ 

ሃይማኖት ሌላው አማራጭ ነው፡፡ ምናልባትም እኛ ወደ ቤተክርስትያን፣ መስጊድ ወይንም ምኩራብ  ብንሄድ ወይንም የአንድ የአዲስን ሃይማኖት አመለካከት ብንወስድ የተሻልን ሰዎች እንሆን ይሆናል፡፡ ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ ከሃይማኖት የምናገኘው (በዚህች) በምታረጀው ዓለም ውስጥ ያለ ሌላ አመለካከት ነው እንጂ በውስጣችን የአዲስ ሕይወት ጅማሬን አይደለም፡፡

በመጨረሻም አንዳንዶች መልካምን ለማግኘት ሕጉ የተሻለ ምርጫ ነው ይላሉ፡፡ እኛ ባህርያችንን የሚቆጣጠር አንድ ሕግ ቢኖረን በተለይም የሞራል ባህርያችንን ከዚያም እኛ የተሻልን ሕዝብና ዜጋ እንሆናለን ይላሉ፡፡ ነገር ግን ተጨማሪ ሕጎች የሚመሩት ትክክልን ለማድረግ ወደ መፈለግ ሳይሆን ወደ ጭቆና ነው፡፡ የእኛ ሰዋዊ ተፈጥሮ በሕጎች ዙሪያ የሚፈልገው ከሕግ ውጪ ለባህርያችን የሚስማማውንና የምንሰራውን ስራ የሚደግፈውን ነገር ነው፡፡ በመሆኑም ሕጉ በውስጣችን ላለው ሕይወት መልካምነትን አያመጣም፡፡

እውቀት፣ ስነ ስርዓት፣ ሃይማኖት እና ሕግ ለሕይወታችን ብዙ ነገርን ይጨምራሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ መፍትሔዎች መጥፎ ባሕርይን ለመቅረፍ ይሞክራሉ ነገር ግን በውስጣችን ያለውን መልካም ነገር ሊያድሱልን በፍፁም አይችሉም፡፡ እነዚህ ሁሉ ውጪያዊ የሆኑ ተፅዕኖዎች ናቸው፡፡ በውስጣችን ያለውን ክፉ ለመቆጣጠር የምናደርገውን ትኩረት በምናቆምበት ጊዜ እንደገና ለእሱ ተፅዕኖዎች እንንበረከካለን፡፡ 

መልካም ለመሆን በምናደርገው የአንዳንድ ጊዜ ጥረታችን ብቻ ደስተኞች እንሆናለንን?

እኛ መልካም ነንን?

ሁል ጊዜ መልካም ሆኖ መገኘት የማይቻል ስለሆነ ብዙዎች የደመደሙት ይህ የማይቻል ግብ ነው በማለት ነው፡፡ ክፎዎቹን ስራዎቻችንን ለማካካስ በጣም ብዙ መልካም ስራዎችን ማድረግ ብቻ ነው ያለብን ይላሉ፡፡ ይህም ደግሞ ድርጊቶቻችን ልክ በሚዛን ላይ እንደተቀመጡ ያስመስላቸዋል፡፡ ስለዚህም የእኛ ስራ (የሚሆነው) በሕይወታችን ያለው መልካም ክፉውን እንዲመዝን ማድረግ ነው፡፡ ስለዚህም ሕይወት ከክፉ ይልቅ ብዙ መልካምን ለማድረግ የምንችልና የማንችል መሆናችንን የመፈተኛ ቦታ ነው፡፡

እግዚአብሔር እኛን የፈጠረን ለዓላማ እንጂ ሊፈትነን አይደለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው እሱ የፈጠረን መልካምን እንድናደርግ እንጂ ከክፉ ይልቅ መልካምን ማድረግ አለማድረጋችንን ለመፈተን አይደለም፡፡ እውነተኛ ሕይወትም ማለት እግዚአብሔር እንዲኖረን የሰጠን ሙሉ መልካም ሕይወት ማለት ነው፡፡ ይሁን እንጂ መልካሙ በቅድሚያ ወደ ሕይወት መምጣት አለበት፡፡

የእኛም ሕይወት እንደ ሚዛን መቀመጫ ሳይሆን ልክ እንደ ሙሉ ብርጭቆ መሆን ነው ያለበት፡፡  እግዚአብሔር በውስጣችን ልንሰራ በሚፈልገው መልካም ነገሮች ሁሉ ብርጭቆው እስከ አፉ ድረስ ተሞልቷል፡፡ እኛም ልናደርግ የምንችለውን መልካም ነገርን ሁሉ በምናደርግበት ጊዜ በብርጭቆው ውስጥ ምንም ነገርን ልንጨምር አንችልም ምክንያቱም እኛ ያደረግነው የእኛን ድርሻ ወይንም ሃላፊነት ብቻ ነውና ማለትም እግዚአብሔር እንድናደርገው ያቀደውን ነገር ብቻ  ነው ያደረግነው፡፡

ሆኖም በጣም ብዙ ጊዜ ከብርጭቆአችን ውስጥ መገኘት ያለበትን ወስደን አጉድለን እግዚአብሔር ለሕይወታችን ካቀደው በታች ወድቀን እንገኛለን፡፡ ይህም የሚሆነው እኛ ክፉን ነገር በምንሰራበት ጊዜ ወይንም መልካም የመስራትን ዕድል በማንጠቀምበት ጊዜ ነው፡፡ ይህም ደግሞ የሚሆነው የምናደርገው መልካም ነገር እኛ የምንመኘውን ነገር እስካደረገልን ድረስ ነው፡፡ ለምሳሌም ያህል እኛ ለሚስቶቻችን መልካም እንሆናለን ምክንያቱም ቆይቶ የምንጠይቀው ውለታ ስለሚኖር ነው፡፡ በእንደዚህ ዓይነት መንገዶች እግዚአብሔር ለእኛ ያቀደውን ዕቅድ በእውነት መልካም መሆንን እንስታለን፡፡ በሕይወታችንም ሁሉ ከብርጭቆአችን ውስጥ እንወሰድና ከታቀደልን መልካም ሕይወት ጎድለን እንገኛለን፡፡

እኛ እውነተኛ መልካም ሰው የመሆናችን ብቸኛ ተስፋ ያለው በፈጠረን በእሱ በእግዚአብሔር ዘንድ ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሔር እንዴት ነው ሊረዳን የሚችለው? በእኛ ውስጥ ያለውን ክፉ ነገር ለመቆጣጥር እና ለሕይወት መልካምን ነገር ሊሰጠን ምንድነው ያደረገው?

የእግዚአብሔር መፍትሄ!

እግዚአብሔር በምድር ያሉትን ሰዎች ሁሉ ምንም ክፉ ሳይኖርባቸው እንደገና ለመፍጠር የሚችል ኃይል አለው፡፡ ነገር ግን ይህን ከማድረግ ይልቅ እሱ ፍጥረቱን አክብሮ እንዳለ ጠብቆታል፡፡ ስለዚህም ኃይሉን በሌላ መንገድ ለመጠቀም እና በሕይወታችን ጣልቃ ለመግባት መረጠ፡፡ ሰይጣን በሰዎች ውስጥ ያለውን ኃይል ለመስበር እንዲሁም ለእኛም አዲስን ሕይወት ሰጥቶ መልካምነት እንደገና በእኛ እንዲኖር አደረገ፡፡

በሰይጣንና በእግዚአብሔርም መካከል ያለው ጦርነት እግዚአብሔር የፈጠረው ይህ ዓለም ነው፡፡ ሰይጣንን እና ስራውን እንዲዋጋ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ መሢሁን ወደዚህ ዓለም ላከው፡፡ ሰይጣንም ያለውን ጥበቡን ሁሉ በኢየሱስ ላይ ወረወረው፡፡ ኢየሱስም ተልዕኮውን ባልተረዱት በክፉዎች ሰዎች እጅ መከራን ተቀበለ፡፡ የእሱም ምስክርነት በውሸት ተበከለ፡፡ በመጨረሻም ሰይጣን ፍትህ አልባ በሆነ የመንግስት ባለስልጣን ተጠቅሞ ኢየሱስ ባልሰራው ወንጀል እንዲገደል አስደረገ፡፡ ኢየሱስ ይህንን ሁሉ ክፉ ነገር በፈቃዱ ወሰደ፣ ነገር ግን ሰይጣን በፍፁም አላሸነፈውም፡፡ እሱም ክፉን በክፉ አንዴም እንኳን አልመለሰም፡፡ እሱ ክፉን በመልካም አሸነፈ፡፡

ሰይጣንን ለማሸነፍ መሢሁ ኢየሱስ ሆነ ብሎ (በፈቃዱ) ሞትን ቀመሰ፣ ይህም (ሞት)የሰይጣን ከፍተኛ መጠቀሚያ መሳሪያው ሲሆን፣ በዚህም ሰይጣንን ድል ነሳው፡፡ ወደ ሕይወትም በመመለስ በሰይጣን እጅ ካለው ታላቅ ክፉ ነገር የበለጠ ኃይለኛ መሆኑን ኢየሱስ አሳየ፡፡ በምድር ከኖሩት ሰዎች ሁሉ ይልቅ ሞትንና ክፉን የተዋጋ (ደግሞም ያሸነፈ) መሢሁ ኢየሱስ ብቻ ነው፡፡   

ኢየሱስ መሢሁ ያሳየው ነገር እሱ ከሰይጣን እንደሚበልጥ ነው፡፡ ኢየሱስ ሰይጣን የያዘውን ኃይል ሰብሮ ሕይወትን ለእኛ ለመስጠት ኃይል አለው፡፡ እሱ ብቻ ነው በእኛ ውስጥ መልካም እንደገና እንዲኖር ማድረግ የሚችለው፡፡

በውስጣችን ባለው ክፉ ላይ ኢየሱስ ስልጣኑን እንዴት ሊገልጥ ይችላል?

መሢሁን ኢየሱስን መከተል!

አንድ ጊዜ አንድ ሰው ከእስር ቤትና ከእስር ቤት ጠባቂዎች ሁሉ በጣም ጠንካራ ነኝ በማለት ይኮራና ይናገር ነበር፡፡ የዚህንም ሰው ጉራ ሰምቶ የእስር ቤቱ ጠባቂ ይህንን ሰው ሊይዘው ሄደ፡፡ ነገር ግን ሰውየው ተሰወረ፡፡ ታዲያ ያ ሰውዬ ከእስር ቤቱ ጠባቂ የበለጠ ጠንካራ ነበር እንዴ?

እንዲሁም ሌላ ሁለተኛው ሰው ደግሞ ከእስር ቤትና ከእስር ቤት ጠባቂዎች የበለጠ ጠንካራ ነኝ በማለት የሚናገር ነበረ፡፡ ጠባቂዎቹ ሊይዙት ሲመጡ ወጣና ተገናኛቸው፡፡ እነሱም ያዙት በጣምም መቱት አሰሩትም ከዚያም በእስር ቤቱ ውስጥ ወስደው በጣም መጥፎ በተባለው ማሰሪያ ቦታ ውስጥ ጣሉት፡፡ እዚያም ውስጥ ቆለፉበት ጠባቂዎችንም በበሩ ላይ አስቀመጡ፡፡ የእስር ቤቱም ተቆጣጣሪዎች ሃላፊ በሰውየውና በጉራው ላይ በቢሮው ውስጥ ተቀምጦ ይስቅ ነበር፡፡

ነገር ግን ሳቁ ብዙ አልቆየም፡፡ ወዲያው በእስር ቡቱ ውስጥ ታላቅን ጪኸት ተሰማ፡፡ ሰውየው ሰንሰለቱን በጣጥሶ በሩን ገፍቶ ከፈተው፣ ጠባቂዎቹንም ወዲያ ወርውሮ ሌሎቹን የእስር ቤቶች ክፍሎች አንድ በአንድ ከፋፈተና ‹ይህን እስር ቤት መልቀቅ የሚፈልግ ማንም ሰው ቢኖር ይከተለኝ በማለት ጥሪ አቀረበ›፡፡ አንዳንዶቹ እስረኞች ፈርተው ነበር፡፡ ይህንን ሰው ቢከተሉትና እንደገና ቢያዝ ከእሱ ጋር ከበፊት ስቃያቸው የበለጠ እንደሚሰቃዩ አሰቡ፡፡ ነገር ግን ሌሎቹ ደግሞ እንደዚህ አሉ ‹በእሱ ላይ ማድረግ የሚችሉትን ክፉ ነገር ሁሉ አድርገውበታል ነገር ግን አሁን እሱ ከእነሱ የበለጠ ኃይለኛ መሆኑን አሳይቷቸዋል፡፡ እንከተለዋለን እንወጣለን› አሉ፡፡

እሱንም እስከ እስርቤቱ መጨረሻ ድረስ በቅርበት የተከተሉት የየእስር ቤቶቹን ክፍሎች ለመክፈት እና በመንገድ ላይ ያሉትንም ጠባቂዎቹን ለማሸነፍ ኃይሉን እያካፈላቸው አገኙት፡፡ በመጨረሻም እስከ ፅድቅ መንግስቱ ድረስ ተከተሉት፡፡

ኢየሱስ መሢሁ በእሱ ለሚያምኑትና እሱንም እንደ አዳኛቸው አድርገው በሚቀበሉት በእያንዳንዱ ሰውና ሴት ሕይወት ውስጥ መልካምነትን እንደገና ለማነሳሳት ቃል ኪዳንን ገብቷል፡፡ በእስር ቤት የተመታው እሱ ነው ነገር ግን (በኃይሉ) ከክፉ እስር ቤት ውስጥ ወጥቷል፡፡ እሱም ወደ መልካምነት አዲስ ሕይወት ውስጥ እንድንመጣ ይጠራናል፡፡

ሕይወት በመሢሁ በኢየሱስ ውስጥ፦

ኢየሱስ በእኛ ውስጥ መልካም እንዲኖር ሲያደርግ እኛ ትክክለኛ ምርጫዎችን ለማድረግ ነፃ እንሆናለን፡፡ እኛም መልካምን ነገር የማድረግ ፍላጎቶች ይኖሩናል ይህም ከውጭ የሚመጣ ሳይሆን ከውስጥ የሚመጣ ነው፡፡ እኛ መልካምን የማድረግ ጥንካሬ ይኖረናል፡፡ እኛ ፍፁም አዲስ ሰዎች እንደምንሆን መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፡፡ የአዲሱም ሕይወት ምንጫችን እራሱ እግዚአብሔር ነው፡፡

እኛ አሁንም ችግር አለብን፡፡ አሮጌውና መጥፎው ክፍላችን በእኛ ውስጥ መኖሩን ይቀጥላል፡፡ እግዚአብሔር ቃል የገባልን በመንግስተ ሰማይ ውስጥ በውስጣችን ያለውን መጥፎ ነገር አስወግዶ በመጀመሪያ ስንፈጠር የነበረንን ሕይወት መልሶ እና አድሶ ሊያቆመን ነው፡፡ እስከዚያ ድረስ ግን እኛ በውስጣችን በክፉውና በመጥፎው መካከል የሚካሄድ ትግል ይኖረናል፡፡

እንድናመቻምችም ውጪያዊ ግፊቶችን እንጋፈጣለን፡፡ እኛ የምንኖረው በገለልተኛ ዓለም ውስጥ አይደለም፡፡ ሁኔታዎችና ሌሎች ሰዎች እኛ እንድናመቻምች ተፅዕኖ ለማድረግ ጥረት ያደርጋሉ፡፡ ለምሳሌም ያህል ከእኛ ጋር አብረው የሚሰሩት ሰዎች ለአለቆቻችን እነሱ በሰዓታቸው ላይ እያታለሉ እንደሆነ ወይንም አንዳንድ ነገሮችን ከሥራ ቦታ መውሰዳቸውን እንዳንናገር ይፈልጋሉ፡፡ እንዳንናገርባቸውም እኛም እንደ እነሱ እንድናደርግ ይፈልጋሉ፡፡ ሰይጣንም እንደዚሁ አዲሱን ሕይወታችንን ይቃወመዋል፡፡ እሱ እኛን ለማጥፋት እና በውሸቱ ሊያታልለን ይፈልጋል፡፡

ለዚህ ዓይነቱ ትግል እግዚአብሔር እንዴት ነው እርዳታ የሰጠን?

ይህን አዲስ ሕይወት መኖር፦

እግዚአብሔር እኛ በእራሳችን እንድንቆም አልተወንም፡፡ እግዚአብሔር ያደረገው ነገር በመሢሁ በኢየሱስ በኩል በውስጣችን ያለውን መልካም ማደስ ብቻ ሳይሆን ይህንን አዲስ ሕይወትም እንድንኖር የሚያስችለንን አስፈላጊውን ነገር ሰጥቶናል፡፡ እግዚአብሔር ይህን አዲስና ትርጉም ያለውን ኑሮ እንድንኖር የሚያስችሉንን ሦስት ጠቃሚ ነገሮችን ሰጥቶናል እነዚህም ሀ. መጽሐፍ ቅዱስ፣ ለ. መንፈስ ቅዱስ እና ሐ. ቤተክርስትያን የምትባለው አዲስ ማኅበረ ሰብ ናቸው፡፡  

መጽሐፍ ቅዱስ ለኑሮ የሚያስፈልገን መመሪያችን ነው፡፡ እሱም የሰይጣንን ውሸቶች ይቃወማቸዋል፡፡ በእሱም ውስጥ እኛ የምናገኘው አሁን እኛ በደስታና በሐሴት የምንከተለውን የእግዚአብሔርን ሕግ ብቻ ሳይሆን ስለዚህ ሕይወትና ስለ ዓለም ሊኖረን የሚችለውንም አመለካከት ጭምር ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ነው እሱም የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንድናውቅ ይመራናል፡፡ ያለ እሱ እኛ ትክክለኛውን አቅጣጫ ማግኘት አንችልም፡፡ እኛ ገለልተኞች አይደለንምና ሐሳባችንን እንዲመራልን የእግዚአብሔር ቃል ያስፈልገናል፡፡

መንፈስ ቅዱስ ደግሞ በክርስቶስ አዲስን ሕይወት ከተቀበልንበት ጊዜ አንስቶ በውስጣችን የሚኖረው የእግዚአብሔር መንፈስ ነው፡፡ እሱም በክርስቶስ ሕያው ለሆነው ሰው ከእግዚአብሔር መንገድ ጋር ተቃራኒ የሆኑትን ሐሳቦችና ድርጊቶች ይነግረዋል፡፡ በዚህ አዲስ ሕይወትን ባገኘው ሰው ውስጥ የሚኖረው እግዚአብሔር ነው ስለዚህም ሰይጣንንና የእሱን እርኩሳን መናፍስት መፍራት አይኖርበትም፡፡ አንድ ሰው በውስጡ የመንፈስ ቅዱስን ድምፅ በሚሰማበት ጊዜ ትክክለኛ ውሳኔን በማድረግ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመከተል ይችላል፡፡

ቤተክርስትያን የእግዚአብሔር ሕዝብ ማኅበረ ሰብ ናት፡፡ እኛ አሁን የአዲስ ቤተሰብ፣ ማለትም የእግዚአብሔር ቤተሰብ አባላት ሆነናል፡፡ በክርስቶስ ያለውን አዲስ ሕይወት ቤተክርስትያን ሞዴል (አርዓያ) ሆና ታሳያለች፡፡ መንፈስ ቅዱስን የሚከተሉ የሰዎችን ምሳሌነትም ትሰጠናለች፤ ይህም ለመታዘዝ ከፍተኛ ዋጋን በሚያስከፍልም ሁኔታ ጭምር ውስጥም ነው፡፡ እነዚህ ምሳሌዎች በክርስቶስ ላለው አዲስ ሰው ትክክለኛ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ በሕይወት አስቸጋሪ መንገዶች ውስጥ በመታገል ላይ እያለን ይህንን አዲስ ሕይወት እንድንኖረው ቤተክርስትያን ማበረታቻዎችንና አቅጣጫዎችን ትሰጠናለች፡፡

ከእነዚህ ሦስት ነገሮች ውስጥ አንዳቸው ቢጎድሉ በክርስቶስ አዲስ የሆነው ሰው በሰይጣን የፈተና ወጥመድ ውስጥ ሊወድቅ ይችላል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ፣ በመንፈስ ቅዱስና በቤተክርስትያን አማካኝነት እግዚአብሔር ከሰጠው እርዳታ ውጭ በዚህ ዓለም ውስጥ ያለውን ክፉ ለመቋቋም አይቻልም፡፡

በክርስቶስ ያለው አዲስ ሕይወት ለፍርድ ቀን ያዘጋጀናልን?

የፍርድ ቀን፦

ብዙውን ጊዜ እኛ እግዚአብሔር የሚፈርድብን በሰራነው መልካምና ክፉ ነገር ላይ ተመስርቶ እንደሆነ እናስባለን፡፡ ይሁን እንጂ እኛ አሁን የምንሰራው ማንኛውም ነገር በውስጣችን የሚኖረውን ነገር የሚያሳይ ነው፡፡ እግዚአብሔር የሚፈርድብን አዲስን ሕይወት ከእሱ በማግኘትና ባለማግኘታችን አማካኝነት ነው፡፡ ይህ አዲስ ሕይወት ካለን የፍርድ ቀን በሚመጣበት ጊዜ በውስጣችን ያለውን ክፉ እግዚአብሔር ያስወገደዋል፡፡ እኛም እግዚአብሔር በመጀመሪያ ሲፈጥረን እንደነበረው እንሆናለን እሱም ወደ መንግስተ ሰማይ ያመጣናል፡፡ ይህ አዲስ ሕይወት ከእግዚአብሔር ዘንድ ከሌለን ግን ስለ መልካምም የሚኖረን እውቀት ይወሰድብናል ከዚያም ወደ ሲዖል እንጣላለን፣ እሱም ለሰይጣንና ለተከታዮቹ የተዘጋጀ ቦታ ነው፡፡ 

በክርስቶስ አዲስ የሆነው ሕይወት አላችሁን? እውነተኛ መልካም ሰው ለመሆን ትፈልጋላችሁን?

የእናንተ ውሳኔ፦

ብዙ ሃይማኖት፣ እውቀት፣ ስነ ስርዓት ወይንም ሕጎች ለአንድ ሰው አዲስን ሕይወት አይሰጡትም፡፡ የሰይጣን ኃይል ተሰብሮ አዲስ ሕይወት በውስጣችሁ መግባት አለበት፡፡ ማንም ነቢይ፣ የሩቅ ምስራቅ እምነት አስተማሪ፣ ሃይማኖት ወይንም ቅዱስ የተባለ ሰው ይህንን አዲስ ሕይወት ሊሰጣችሁ አይችልም ወይንም ከሰይጣንና ከእሱ ክፉ ስራዎች በተገቢ መንገድ ሊጠብቃችሁ በፍፁም አይችልም፡፡

በትክክል እውነተኛውን መልካም ሕይወት ለመኖር የሚያስችለው ቁልፉ ያለው መሢሁ ኢየሱስ ክርስቶስ ለእናንተ በሠራው ሥራ ላይ ነው፡፡ እሱ ፍፁምን ሕይወት በምድር ኖረ፡፡ እሱም የሰዎች ልጆችን የኃጢአት ዕዳ ለመክፈል እራሱን በፈቃዱ ሰጠ፡፡ ሞተ ተቀበረ በሦስተኛውም ቀን ሞትን ድል አድርጎ ተነሳ፡፡ አሁን ጌታ ኢየሱስ አዲስ ሕይወትን ለሚፈልጉት በንስሐ ቀርበው ቢጠይቁት ለመስጠት ፈቃደኛና ዝግጁ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ‹ለተቀበሉት ሁሉ ግን በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ስልጣንን ሰጣቸው› ዮሐንስ ወንጌል 1.12 በማለት ይናገራል፡፡ ስለዚህም አሁን ማድረግ የሚገባችሁ ነገር ከልባችሁ በመሆን በንስሐ ቀርባችሁ እሱ ይቅር እንዲላችሁ እና አዲስንም ሕይወት በልባችሁ እንዲፈጥርላችሁ መጠየቅ ነው፡፡ በእሱ ያመኑና ከእሱም ዳግመኛ ልደትን ያገኙ ሁሉ የእሱ ልጆች ይሆናሉ፡፡ ወደ እግዚአብሔር ቤተሰብነት በምንደባለቅበት ጊዜ ከዚህ ቀደም ያደረግነው የኃጢአት ሕይወት ሐፍረት ሁሉ ከእኛ ይወሰዳል፡፡

የአዘጋጁ ማሳሰቢያ፦

አንባቢዎች ሆይ ይህንን ጽሐፍ በሚገባ አንብባችሁት ከሆነ ልታስቡባቸው የሚገቡ ነገሮች ይኖራሉ፡፡ ከእነዚህም ዋናውና የመጀመሪያው ነገር አሁን ከሕያው እግዚአብሔር ጋር ያላችሁ የግል ግንኙነት ጉዳይ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ሰላም አላችሁን? እግዚአብሔር በኃጢአተኞች ላይ ከሚያመጣው ከቁጣው ፍርድ የምትድኑበት መዳኛ አግኝታችኋልን? አሁን ብትሞቱ የምትገቡት የት ነው?

ከእግዚአብሔር ጋር ሰላም እንዲኖራችሁ ከፍርዱም ቁጣ እንድትድኑ አንዱና ብቸኛው መንገድ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ተከፍቶላችኋል፡፡ ይህንን ለመረዳት በዚህ ድረ ገፅ ላይ የሚወጡትን ተከታታይ ጽሑፎችን እና መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ ሕይወታችሁን በሚገባ መመርመር ከዚያም ወደ ጌታ ኢየሱስ በመቅረብ እውነተኛ ንስሐ በመግባት ይቅርታን መጠየቅ ያስፈልጋችኋል፡፡ እግዚአብሔር በፀጋውና በመንፈሱ ይርዳችሁ! አሜን፡፡

 


የትርጉም ምንጭ: Does Goodness Live In You?

ለእስልምና መልስ አማርኛ  ዋናው ገጽ