በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አሉ የሚባሉ ቅራኔዎች
‹ወደ ፍርድም አስቀድሞ የገባ ፃድቅ ይመስላል፣ ባላጋራው መጥቶ እስኪመረምረው ድረስ› ምሳሌ 18.17

የቅራኔዎች መኖር ውንጀላ
በ Jay Smith, Alex Chowdhry, Toby Jepson, James Schaeffer

[ክፍል አንድ] [ክፍል ሁለት] [ክፍል ሦስት] [ክፍል አራት] ክፍል አምስት
ትርጉምና ቅንብር በአዘጋጁ

 

ጥያቄ ሃያ አራት

የንጉሱ የአቢያ እናት ስም ማን ነበር? በ 2ዜና 13.2 መሰረት የጊቢያው የኡርኤል ልጅ ሚካያ ነበረች ወይንስ በ2ዜና 11.20 መሰረት የአብሶሎም ልጅ መዓካ ነበረች?

የዚህ ቅራኔ መሳይ ስም ችግር የሚገኘው በአማርኛ ሴት ልጅ ተብሎ ለተተረጎመው (ባት)የሚለውን የእብራይስጥን ቃል በትክክል በመረዳት ላይ ነው፡፡ ምንም እንኳን የመጀመሪያ የሴት ዘር ትውልድን ለመጥቀስ የሚያገለግል ቃል ቢሆንም ይህ ቃል የሩቅ ዘመድንም ለመጥቀስ እኩል ያገለግላል፡፡ የዚህ ምሳሌ የሚሆነን በ2 ሳሙኤል 1.24 ላይ ያለው ቃል ነው፡፡ የሚለውም “የእስራኤል ቈነጃጅት ሆይ፥ ቀይ ሐርና ጥሩ ግምጃ ያለብሳችሁ ለነበረ፥ በወርቀዘቦም ላስጌጣችሁ ለሳኦል አልቅሱለት።” ይህ ከእስራኤል (ከያዕቆብ) 900 ዓመታት በኋላ የተነገረ ቢሆንም እንኳን በዚህ ላይ ግልፅ የሆነው ቆነጃጅት የሚለው ቃል ተመሳሳዩ የእብራይስጥ ቃል (ባት) የሚያመለክተው ለእስራኤላውያን ሴቶች ነው የእርሱ የሴቶች ዝርያዎችን ነው፡፡


በዚህ እውነታ መሰረት ስንመለከተው ቅራኔ የመሰለው ነገር ከፊታችን ይጠፋል፡፡ 2 ዜና 13.2 በትክክል ያስቀመጠው ሚካያ የዑርኤል ልጅ መሆኗን ነው፡፡ እኛ ልንገምት የምንችለው ዑርኤል ትዕማርን እንዳገባ ነው፣ የአቤሴሎምን ብቸኛ የቅርብ እህት፡፡ ሁለቱም በአንድ ላይ ሚካያን አገኙ ንጉሱን ሮብአምን ያገባችውን እናም የአቢጃ እናት የሆነችውን 2ዜና 11.20 እና 1ነገስት 15.2፡፡ ይህም የሚጠቅሰው መዓካ የአብሶሎም ልጅ በማለት በቀላሉ ያያያዘው በጣም ታዋቂ ከሆነው የአያቷ ዝርያ ጋር ነው፡፡ ይህም በጣም ከማይታወቀው አባቷ ይልቅ የሚያሳያው የእርሷን ንጉሳዊ ዘርነቷን ለመጠቆም ነው፡፡ አብሶሎም የሚለውም የአቢሴሎም ሌላው ስያሜ ነው (አንድ ሰው ነው) እንደዚሁም መዓካ የሚለውም ቃል የሚካያ ሌላው መጠሪያ ነው፡፡ ስለዚህም  የቤተሰቡ የዘር ግንድ የሚከተለውን ይመስላል፡፡


     አቤሴሎም/አብሶሎም
                     |
   ትዕማር ----- ዑርኤል
                      |
    ሮብአም --- ሚካያ/መዓካ
                |
            አቢጃ

ጥያቄ ሃያ አምስት

በኢያሱ የጦርነት ዘመቻ ጊዜ ኢየሩሳሌም ወዲያውኑ ተያዘች ወይንስ አልተያዘችም?  በኢያሱ 10.23፣40 መሰረት ኢየሩሳሌም ተይዛለች ወይንስ በኢያሱ 15.63 መሰረት አልተያዘችም፡፡

አጭሩ መልስ የሚሆነው በተጠቀሰው የዘመቻ ጊዜ አልያዟትም ነበር ነው፡፡ የተሰጡት ጥቅሶች ሙሉ በሙሉ ስምምነት ያላቸው ናቸው መምታታቱ የመጣው የሚመለከቱትን አንቀፆች አሳስቶ ከማንበብ ብቻ ነው፡፡

በኢያሱ 10 ላይ ኢያሱ የኢየሩሳሌምን ንጉስ ገድሏል ከተማዋ ግን አልተያዘችም፡፡ የኢያሱ 10 ቁጥር 16-18 እና 22-26 የሚያሳዩት ይህንን ነው፡፡ አምስቱ የአሞራውያን ነገስታት እና ጦራቸው ከተማዎቻቸውን ትተው በጊባዖን ለማጥቃት ወጡ፡፡ ኢያሱና እስራኤላውያን እነርሱን ድል አደረጓቸው አምስቱም ነገስታት ወደ ማካዳ ወደሚገኘው ዋሻ ሸሽተው ተሸሸጉ፣ ከዚያም ውስጥ የኢያሱ ወታደሮች አውጥተው ወደ ኢያሱ አመጧቸው እርሱም ሁሉንም ገደላቸው፡፡ ጦር ሰራዊቶቻቸውን በተመለከተ ግን ቁጥር 20 የሚከተለውን ይናገራል “እስኪጠፉም ድረስ ኢያሱና የእስራኤል ልጆች በታላቅ መምታት መምታታቸውን በፈጸሙ ጊዜ፥ ከእነርሱም ያመለጡት ወደ ተመሸገ ከተማ በገቡ ጊዜ፥”፡፡ ይህም በግልፅ የሚያሳየው ነገር ከተማዎቹ እንዳልተያዙ ነው፡፡ ስለዚህም ነገስታቱ ነበሩ እንጂ ከተማዎቻቸው ገና አልተያዙም ነበር፡፡

ኢያሱ 10.28-42 ላይ የቀረውን ነገር በተለይም የጦር ሰራዊቱን ዘመቻ ዘግቦ ይገኛል፡፡ እጅግ ብዙ ከተማዎች እንደተያዙና እንደተደመሰሱም ይናገራል እነዚህም፣ መከዳህ፣ ላኪሽ፣ ኤግሎን፣ ሄብሮን እና ደቢር ናቸው፡፡ እነዚህ ከተማዎች ሁሉም ከኢየሩሳሌም ደቡብ ምዕራባዊ ቦታዎች ናቸው፡፡ የጌዜር ንጉስ እና ሰራዊቱ ሁሉ ሌኬሽን እየረዱ ተደመሰሱ ቁጥር 33 እንዲሁም በቁጥር 30 ላይ ቀደም ብሎ ከተከናወነው የኢያሪኮ መያዝ ጋር ንፅፅር ተደርጓል ነገር ግን እነዚህ ሁለቱም ከተማዎች አንዳቸውም በዚያን ጊዜ አልተያዙም፡፡ በቁጥር 40 እና 41 ላይ የዚህን ዘመቻ ገደብ ይናገራል ከኢየሩሳሌም በስተደቡብ እና ምዕራብ በኩል የሆኑትን ነገሮች ሁሉ፡፡ ጠቃሚ በሆነ መልኩ ጊብዓ ምስራቃዊ ገደብ እንደሆነች ይናገራል እርሱም በግምት አስር ማይልስ ከኢየሩሳሌም ሰሜን ምዕራብ ይሆናል፡፡

ስለዚህም ኢየሩሳሌም በኢያሱ 10 ላይ እንደተያዘች ተደርጎ አልተገለፀም፡፡ ይህም በኢያሱ 15.63 ላይ ካለው ጋር ይስማማል ምንም ተቃርኖም የለም፡፡

ጥያቄ ሃያ ስድስት

የዮሴፍ አባት ማን ነበር? የዮሴፍ አባት በማቴዎስ 1.16 መሰረት ያዕቆብ ነበር ወይንስ በሉቃስ 3.23 ላይ እንዳለው ኤሊ ነበር?

ለዚህ ጥያቄ ያለው መልስ በጣም ቀላል ነው ነገር ግን ገለፃን ይፈልጋል፡፡ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ አዋቂዎች በአሁኑ ጊዜ የሚስማሙት ማቴዎስ የሰጠው የዮሴፍን ዘር ሲሆን ሉቃስ ደግሞ የሰጠው የማርያምን ዘር በመሆኑ ነው፡፡ በዚህም መሰረት ያዕቆብን ያደረጉት የዮሴፍ አባት ሲሆን ኤሊን ደግሞ ያደረጉት የማርያም አባት ነው፡፡

ይህ የሚታየው በሁለቱ የድንግል መውለድ ታሪኮች ውስጥ ነው በማቴዎስ 1.18-25 ላይ ያለው ታሪክ ያተኮረው በዮሴፍ ሁኔታ ላይ ነው፣ ሉቃስ 11.26-56 ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ከማርያም አኳያ የተነሳ ነው፡፡

ለመጠየቅ ሎጂካዊ ጥያቄ የሚሆነው በሁለቱም ትውልድ ሀረጎች ላይ ዮሴፍ ስለምን ተጠቀሰ? የሚለው ነው፡፡ መልሱም እንደገና በጣም ቀላል ነው፡፡ ሉቃስ የተከተለው በጣም ጥብቅ የሆነ የዕብራይስጥን ባህል ሲሆን በዚያም የጠቀሰው ወንዶችን ብቻ ነው፡፡ ስለዚህም በዚህ ጉዳይ ላይ ማርያም እዚህ ላይ የተገለጠችው በባሏ ስም ነው፡፡ ይህ አመለካከት በሁለት የማስረጃ ነጥቦች የተደገፈ ነው፡፡ በመጀመሪያ በግሪኩ የሉቃስ ጽሑፍ ላይ እያንዳንዱ ስም ከስሞቹ ቀድሞ “አርቲክል” አላቸው ለምሳሌም ያህል (የኤሊ the Heli, የማታት the Matthat) ይላል፡፡ በዮሴፍ ላይ ግን አርቲክሉ የለም ስለዚህም የዮሴፍ ስም አጻጻፍ ከሌሎቹ የተለየ ነው፡፡ ይህ እውነታ በእንግሊዝኛውም በአማርኛውም ላይ ግልጥ አይደለም በመጀመሪያው የግሪኩ ቋንቋ ላይ ግን ግልጥ ነው፡፡ ይህም ግሪክን የሚያነብ ማንንም ሰው የሚያስደንቅ ነው የሚሆነው፣ ይህም አጻጻፉ የሚያሳየው የዮሴፍን ሚስት ዘር ግንድ ነው፡፡ ምንም እንኳን የእርሱ የዮሴፍ ስም ቢጠቀስም ለመናገር የታቀደው ግን የማርያምን ዘር ነው፡፡ ሁለተኛው የማስረጃ መስመር ያለው  የአይሁድ ምንጭ በሆነው በኢየሩሳሌሙ ታልሙድ ላይ ነው፡፡ ይህም የዘር ትውልዱ የማርያም መሆኑን ያሳያል፣ እርሷን የኤሌ ልጅ እንደሆነች መዝግቧል፡፡ (ሃጊጋ 2.4)

ጥያቄ ሃያ ሰባት

ጌታ ኢየሱስ የመጣው ከየጥኛው ዘር ነው? ከሶሎሞን ዘር ነው ማቴዎስ 1.6 ወይንስ ከናታን ዘር ነው ሉቃስ 3.31?

ይህ በቀጥታ የተያያዘው በቁጥር 26 ላይ ካለውና ቅራኔ ከመሰለው አቀራረብ ጋር ነው፡፡ ማቴዎስ የዮሴፍን ዘር እንደጠቀሰና ሉቃስ ደግሞ የማርያምን ዘር እንደጠቀሰ በአዕምሮአችን ከያዝን ግልፅ የሚሆንልን ነገር ዮሴፍ ከዳዊት ዘር በሰሎሞን በኩል እንደመጣና ማርያም ደግሞ ከዳዊት ዘር በናታን በኩል እንደመጣች ሲሆን በትክክል ለተገነዘበው ምንም ቅራኔን አይፈጥርም፡፡

ጥቄ ሃያ ስምንት

የሰላትያል አባት ማን ነው? በማቴዎስ 1.12 መሰረት ኢኮኒያን ነው ወይንስ በሉቃስ 3.27 መሰረት ኔሪ ነው?

አሁንም እንደገና ይህ ችግር የሚጠፋው ከዳዊት እስከ ጌታ ኢየሱስ ድረስ ሁለት የተለያዩ የዘር ሀረጎች እንደተጠቀሱ ስንገነዘብ ነው፡፡ የሁለቱም የማርያምም የዮሴፍም ዘር ሐረግ ነውና የተዘገበው፡፡ ሁለት የተለያዩ የዘር ሐረጎች ማለትም ሁለት የተለያዩ ሰላትያል በሚባሉ ሰዎች ስር ተጠቅሰዋል ማለት ነው፣ ይህም ስያሜ ሰላትያል የተለመደ የእብራውያን ስም ነው፡፡ ስለዚህም እነርሱ ሁለቱም የተለያዩ አባቶች ያሏቸው የመሆኑ ነገር ምንም አያስደንቅም፡፡

ጥያቄ ሃያ ዘጠኝ

የጌታ ኢየሱስ ትውልድ ግንድ ውስጥ ያለው የዘሩባቤል ልጅ የትኛው ነበር? በማቴዎስ ላይ ያለው አቢዩድ ወይንስ በሉቃስ 3.27 ላይ ያለው ሬስ እንዲሁም ደግሞ በ1ዜና 3.19-20 ላይ ያለውስ ዘሩባቤል?

ልክ በጥያቄ ሃያ ስምንት ላይ እንዳሉት ሁለት ሰላትያሎች ሁለት የተለያዩ ዘሩባሌሎችም የመኖራቸው ነገር ግድ ነው፣ ስለዚህም የእነርሱ ልጆች የተለያየ ስም ያላቸው መሆኑ ጉዳይ ምንም ችግርን አያመጣም፣ እንደቅራኔም ሊወሰድ አይችልም፡፡

ስለዚህም የሰላትያል ልጅ የዘሩባቤል ስም በማርያምም በዮሴፍም የዘር ሀረግ ላይ የመገኘቱ ነገር እኛን ሊያስደንቀን አይችልም፡፡ ማቴዎስ የነገረን ነገር የዮሴፍ አባት ስሙ ያዕቆብ ነበር በማለት ነው፡፡ በእርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ የያዕቆብ ልጅ ስለሆነ ሌላ ዮሴፍም ይነግረናል፣ እርሱም በግብፅ ውስጥ ሁለተኛውና በጣም ኃይለኛ ባለስልጣን ነበረ ዘፍጥረት 37-47፡፡ እነዚህ ሰዎች አንድና ተመሳሳይ ናቸው በማለት ልንናገር አያስፈልገንም ስለዚህም ሁለት የተለያዩ ሰዎች የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤል ልጅ ተብለው ቢጠሩ ችግርን አይፈጥርብንም፡፡

ነገር ግን በ1ዜና 3.19-20 ላይ የተጠቀሰው ዘሩባቤል ሦስተኛው ሌላ ሰው ሊሆን ይችላል፡፡ እንደገናም ይህም ሁኔታ ችግርን አያመጣብንም ምክንያቱም ያ ስም የተለመደ ታዋቂ ስም ነበርና፡፡ በወንጌልም ውስጥ ማርያም የሚለው ስም የተለመደ ስም ስለነበር ማርያም ተብለው የተጠቀሱ ብዙ ሴቶች ነበሩ፡፡ ይህ በማቴዎስ 1.12፣13 ላይ የተጠቀሰው ዘሩባቤል የአጎት ልጅ ሆኖ ነው፡፡ የማቴዎስና የ1ኛ ዜና ንፅፅር የሚከተለውን የቤተሰብ የዘር ግንድ ሊሰጠን ይችላልና፡፡

ኢዮአኪን
   |
ሰላትያልን --- ማልኪራም --- ፕዳያ  ---  ሸሃዛር --- ጃካሚያ --- ሆሻማ ---ንዳቢያ ---
   |                          |
  ዘሩባቤል                ዘሩባቤል --- ሺማይ
     |                                |
  አቢዩድ               ሰባት ወንዶች ልጆች
    |  (1 ዜና 3.19፣20)             
    |
  ዮሴፍ

 

ጥያቄ ሠላሳ

የዖዝያን አባት ማን ነበር? በማቴዎስ 1.8 መሰረት ኢዮራም ወይንስ 2ዜና 26.1 መሰረት አማዚያ ነበር?

የአሁኑም ጥያቄ፣ ከጥያቄ ሃያ አራት ጋር ተመሳሳይ የሆነ ባህርይ ያለው ነው፡፡ ልክ የእብራይስጡ ቃል ባት (ሴት ልጅ) የሩቅ የቤተሰብ ዝርያን ለመጥቀስ የሚያገለግል እንደሆነው ሁሉ የእብራይስጡም (ቤን) ወንድ ልጅ እንደዚሁ ያገለግላል፡፡ ጌታ ኢየሱስ በማቴዎስ 1.1 ላይ እንደ ዳዊት የወንድ ልጅ እንደ አብርሃም የወንድ ልጅ ሆኖ ነው የተጠቀሰው፡፡ ሁለቱም የዘር ግንድ የጌታ ኢየሱስን የስጋ የዘር ግንድ ወደ ሁለቱም ሰዎች ይጠቅሰዋል ይህም የሚያሳየው ነገር የ(ወንድ) ልጅን ቃል አጠቃቀም ነው፡፡ የማቴዎስን ወንጌል የጻፈው የጌታ ደቀ መዝሙር ማቴዎስ እራሱ አይሁድ የነበረና ከአይሁድ እይታ አኳያ የጻፈው ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የሌለው ነገር ነው፡፡ ስለዚህም በእብራውያን የወንድ ልጅ ፅንሰ ሐሳብ መሰረት ነው እርሱ የጻፈው፡፡

ከዚህ በላይ ያለውን በአዕምሮአችን ይዘን አሜስያስ የዖዝያን (አዛርያስም ተብሎ ይታወቃል) አባት መሆኑን በቀላሉ ማየት እንችላለን፡፡ ኢዮራም ወይንም በሌላ ጎን የዖዝያን ቅድመ ኣያት እና ከእርሱ የመጣ ቀጥተኛ ዘር ነው፡፡ ዘሩም የኢዮራም የሚሆነው እንደሚከተለው ነው አሃዝያ - ኢዮአሽ - አማዝያ - አዛርያ ወይንም ዖዝያን እያለ ነው (2ዜና 21.4-26.1) 

የማቴዎስ የዘር አቀራረብ ተቀባይነት ያለው ነው የእርሱ ዓላማ በቀላሉ የዘርን ስረ አመጣጥ ለማሳየት ብቻ ነበር፡፡ እርሱም ያሳየው በ1.17 ላይ ሦስት የተከፈሉ አስራ አራት ትውልዶች የነበሩ መሆናቸውንና፣ በቁጥር አጠቃቀም ችሎታውም፣ ጌታ ኢየሱስ እንደ ዳዊት ልጅ ከተጠራበት አጠራር ጋር በቀጥታ ሁሉን ነገር ማያያዝ ነበር፡፡ በእብራውያን ቋንቋ እያንዳንዱ ፊደል እራሱን የቻለ የቁጥር ዋጋ አለው፡፡ ዳዊት የሚለውን ስም የሚሰጡት ፊደላት የቁጥር ዋጋም አስራ አራት ነው፣ ማቴዎስ የሦስት አስራ አራት ትውልዶችን የዘገበበትም ምክያት ይህ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህም ያነጣጠረው ጌታ ኢየሱስ የዳዊት ልጅነትንና ትክክለኛው ትንቢት የተነገረለትና የሚጠበቀው የነፍስ አዳኝ መሲህ መሆኑን የሚያሳይ የትኩረት ቦታ  ለመስጠት ነበር፡፡

የአዘጋጁ ማሳሰቢያ፡

መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥላላት በተነሱ ሰዎች ቅራኔዎች ናቸው ተብለው ከሚጠቀሱት ውስጥ ከዚህ በላይ የተመዘገቡት ሰባቱ ይገኙበታል፡፡ አብዛኛዎቹ ከስም ልዩነት ጋር የተያያዙ ቢሆኑም ለሁሉም ሎጂካልና ትክክለኛ መልስ ተሰጥቷቸዋል፡፡

በእርግጥ ልዩነት የሚባሉት ሁሉ ላይ ላዩን ብቻ ለሚመለከት ሰው ልዩነት መስለው መታየታቸው ግልፅ ነው፡፡ እኛ እንደምናምነውና እንዲሁም እንደምንጠብቀው አንድ ሰው ላይ ላዩን ብቻ በሆነ መረጃ መሰረት መኖር የለበትም፡፡ ነገሮች እውነት መሆንና አለመሆናቸውን ጠለቅ ብሎ መመርመር ይገባዋል፡፡ ችግር ናቸው ተብለው ለቀረቡት ጥያቄዎች መልስን ካገኘ ደግሞ በተሳሳተ አመለካከት መሰረት ሲያደርግ የነበረውን ውንጀላ አቁሞና ስለዚያም ተፀፅቶ ወደ እግዚአብሔር ለምህረት መቅረብ አለበት፡፡

እንግዲህ እስካሁን እንዳየነው መጽሐፍ ቅዱስ ቅራኔ የለበትም፣ ቅራኔ ናቸው ተብለው የሚጠቀሱትም መልስ አላቸው፡፡ ይህ ሁሉ የሚያሳየው መጽሐፍ ቅዱስን የሰጠው ጌታ እግዚአብሔር ቃሉን እንደጠበቀውና የእርሱ ቃል ምንም ቅራኔ እንደሌለው ነው፡፡ አንባቢዎች ይህንን እውነት ተገንዝባችሁ ቀን በሆነ አዕምሮ መጽሐፍ ቅዱስን በማግኘት እንድታነቡ ነው፡፡ ጌታ እግዚአብሔር ይርዳችሁ፡፡

የትርጉም ምንጭ: "101 Cleared-up Contradictions in the Bible"

ለእስልምና መልስ አማርኛ  ዋናው ገጽ