4. መሐመድና ውግዘት
ምዕራፍ 4
መሐመድና ውግዘት
መሐመድ የእስልምና አካል የተመሰተረበት መሰረት ነው፡፡ ይሄ ምዕራፍ ደግሞ የመሐመድን ግለ ታሪክ አስመልክቶ አጠቃላይ የሆኑ ገጽታዎችን ለመቃኘት ይሞክራል፡፡ ይሄም ደግሞ ሰዎችን በማስገደድ ኃይማኖቱን እንዲቀበሉ ያደረገበትንና የእስልምና መርሆዎችን ያካተተ ነው፡፡
የአስቸጋሪው ነገር ጅማሮ
መሐመድ የተወለደው በ570 ዓ.ም የአረብ ጎሳ ከሆኑት ቤተሰቦቹ በመካ ነው፡፡ አባቱ አብደላ ቢን አብድ ሙታሊብ የሞተው መሐመድ ከመወለዱ በፊት ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ በጨቅላነት ጊዜው ሌሎች ቤተሰቦች እንዲያሳድጉት ተላልፎ ተሰጠ፡፡ የስድስት ዓመት ህፃን ሳለም እናቱ በሞት ተለየች፡፡ ከዚህም የተነሳ አያቱ እርሱን የማሳደጉን ኃላፊነት ወሰዱ፡፡ አሳዛኙ ነገር አያቱም የስምንት ዓመት ልጅ ሳለ የሞትን ጽዋ ተጎነጩ፡፡ በመሆኑም መሐመድ ከአባቱ ወንድም ከአቡ ጧሊብ ጋር እንዲያድግ ተደረገ፡፡ የአጎቱንም ግመሎችና በጎች እንዲጠብቅ ሀላፊነት ተሰጠው፡፡ የቱንም ያህል ሌሎቹ የመሐመድ አጎቶች ሀብታም ቢሆኑም እሱን መርዳት ግን አልቻሉም ነበር፡፡
ቁርአን በቅጽል ስሙ አቡ ላሀብ (የነበልባል አባት) ብሎ ስለሚጠራው የመሐመድ አጎት በመሐመድ ላይ ስለነበረው ንቀትና ጥላቻ መጠነኛ ሀሳብ አለው፡፡
የአቡ ለሀብ ሁለት እጆች ከሰሩ (ጠፉ፤ እርሱ) ከሰረም፡፡
ከርሱ ገንዘቡና ያም ያፈራው ሁሉ ምንም አልጠቀመውም፡፡
የመንቀልቀል ባለቤት የኾነችን እሳት
በእርግጥ ይገባል፡፡
ሚስቱም (ትገባለች)፤ እንጨት ተሸካሚ ስትኾን
በአንገትዋ ላይ ከጭረት የኾነ ገመድ
ያለባት ስትኾን፡፡ (111፡1-5)
ያለ አቻ ጋብቻ
ከድጃ የጋብቻን ጥያቄ ባቀረበችለት ጊዜ መሐመድ የሃያ-አምስት ዓመት ወጣት ነበር፡፡ በአስራ አምስት ዓመት ትበልጠውም ነበር፡፡ አባቷም ጋብቻውን ይቃወም ይሆናል የሚል ስጋት ነበራት፡፡ ስለሆነም አባቷ መጠጥ ጠጥቶ በነበረበት ወቅት ከመሐመድ ጋር ተጋባች፡፡ አባቷም ወደ ማስተዋል ሲመጣ የተደረገውን ስለተረዳ ተበሳጨ፡፡ በአረብ ባህል ባል ለሚስት ጥሎሽ እንዲሰጥ ይጠበቅበታል፡፡ ነገር ግን በወቅቱ ከድጃ ኃይለኛና ኃብታም ስለነበረች ይሄ ስርአት አልተከበረም ነበር፡፡
የመሐመድ ግለ ታሪክ ጸሐፊ የነበረው ኢብን ኢስሃቅ ከድጃን “የክብርና የሀብት ሴት” በማለት ነበር የገለጻት፡፡ ድኻ የነበረውንም መሐመድ መቀበል ችላ ነበር፡፡ ከድጃ ከመሐመድ በፊት ሁለት ጊዜ አግብታ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ ጋብቻን አስመልክቶ ከነበረው መረዳት የተቃረነ ነበር፡፡ በሁለቱ መካከል የነበረውን ስምምነት በተመለከተ ግጭት የነበረበት ነበር፡፡
ወላጅን በሞት መነጠቅ
ከድጃና መሐመድ ስድስት ልጆች ነበሯቸው (አንዳንድ መረጃዎች ሰባት እንደነበሩ ይጠቅሳሉ) ፡፡ መሐመድ አስቀድሞ ሦስት ወንዶች ልጆች ነበሩት ነገር ግን ገና በጨቅላነታቸው ነበር የሞቱት ይሄ ደግሞ በመሐመድ የቤተሰብ ህይወት አሳዛኝ ነገር መሆኑ አልቀረም፡፡
የቤተሰብ ህይወትን አስመልክቶ የነበረ አሳማሚ ልምምድ
በአጠቃላይ ለመደምደም ያህል የመሐመድ የቤተሰቡን ሁኔታ በምንመለከትበት ጊዜ እጅግ ብዙ የሚያሳምሙና የሚጎዱ ሁኔታዎችን ማሳለፍ ችሎ ነበር፡፡ ወላጅ አልባ መሆን፣ አያትንም በሞት ማጣት፣ በድህነት ውስጥ ማለፍ፣ የባለቤቱ አባት ጠጪ መሆን፣ ሀይለኛ በሆኑት ዘመዶች ይደረግበት የነበረው ጥላቻ ከብዙ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ አጎቱ አቡ-ጧሊብ ያደረገለት እርዳታ እና ባለቤቱ ከድጃ እሱን ለጋብቻ በመምረጥዋ ከድህነት ለመላቀቅ ችሎ ነበር፡፡
አዲስ ኃይማኖት ተመሰረተ
መሐመድ የአርባ ዓመት ጎልማሳ በነበረ ጊዜ የመንፈስ ጉብኝት ልምምድ እንዳገኘው ይናገራል (እሱ እንደሚለው ከሆነ ጂብሪል የተባለ መልአክ ሲሆን) በመጽሐፍ ቅዱስ ገብርኤል ተብሎ የተጠቀሰው እንደ ማለት ነው፡፡
ራስን አለመቀበል
በዚህ የመንፈስ ጉብኝት የመሐመድ መንፈስ ክፉኛ ተረብሾ ነበር፡፡ ተቆጣጥሮት በነበረውም መንፈስ ተደምሞ ነበር፡፡ እራሱንም ለመግደል ጥረት አድርጎ ነበር፡፡ ይሄንን አስመልክቶ እንዲህ ብሎ ነበር፡
“ወደ ተራራ ጫፍ ላይ እወጣለሁ፣ እራሴንም ወደ ታች ወርውሬ እገድላለሁ፣ ከዚያም እረፍት አገኛለሁ፡፡”
በዚህ ወቅት ባለቤቱ ከድጃ ከደረሰበት ጭንቀት አፅናናችው ክርስቲያን ወደ ነበረውና ዋራቃ ወደተባለው የአጎቷ ልጅ ቤትም ወሰደቸው፡፡ እርሱም ያበደ ሰው ሳይሆን ነብይ መሆኑን አሳወቃቸው፡፡
ከዚህ በኋላ ለመሐመድ የተገለጠለት ነገር በመቆሙ ምክንያት እንደገና ራሱን ማጥፋት ፈልጎ ነበር፡፡ በተደጋጋሚ ራሱን ከተራራ ላይ ጥሎ ለመሞት ሙከራ እያደረገ ሳለ አንድ ቀን ጂብሪል ተገልጦ “ መሐመድ ሆይ! አንተ በእርግጥም እውነተኛ የአላህ መልዕክተኛ ነህ” አለው፡፡ መሐመድ የተጭበረበረና የተተወ ስለመሰለው እጅግ ፈራ፡፡ ቀድሞ በነበሩት ሱራዎች አላህ መሐመድን እንደማይጥለው አስረግጦለታል፡፡
ጌታህ አላሰናበተህም፤ አልጠላህምም፡፡ መጨረሻይቱም (ዓለም) ከመጀመሪያይቱ ይልቅ ላንተ በላጭ ናት፡፡ ጌታህም ወደ ፊት (ብዙን ስጦታ) በእርግጥ ይሰጥሃል፤ ትደሰታለህም፡፡ የቲም ኾነህ አላገኘህምና አላስጠጋህምን? (አስጠግቶሀል)፡፡ (93፡3-6)
የእስልምናው ማኅበረሰብ በመጀመሪያ ቀስ በቀስ ነበር ያደገው በመጀመሪያ ወደ እስልምና የተለወጠችው ከድጃ ነበረች፡፡ በመቀጠለም የአጎቱ ልጅ የነበረው እና በመሐመድ ቤት ይኖር የነበረው ወጣቱ አሊ ነበር፡፡ ከዚያም ብዙ ድሆች፣ ባሪያዎች ወይንም ከባርነት ነፃ የወጡ ሰዎችም ተከታዮቹ ሆኑ፡፡
የመሐመድ የራሱ ጎሳ
በመጀመሪያዎቹ አካባቢዎች ይሄ አዲሱ ኃይማኖት በተከታዮቹ ዘንድ በሚስጥር ተይዞ ነበር፡፡ ነገር ግን ከሦስት ዓመት በኋላ መሐመድ ከአላህ ዘንድ በአደባባይ ግለጠው የሚል ቃል መጣለት፡፡ ይሄንንም የቤተሰብ ጉባኤ በማዘጋጀት ዘመዶቹ እስልምናን እንዲቀበሉ ጥሪ አደረገላቸው፡፡ የቁረይሽ ነገድ የሆኑት የሃገሩ ሰዎች በመጀመርያ የመሐመድን ንግግር ለመስማት ዝንባሌ አሳይተው ነበር፡፡ ይህ ግን አማልክቶቻቸውን መቃወም እስካልጀመረበት ጊዜ ድረስ ብቻ ነበር የዘለቀው፡፡ ከዚህ በኋላ ኢብን ኢስሃቅ እንደዘገበው ሙስሊሞች “የተናቁ አናሳዎች” ሆነው ነበር፡፡ ውጥረቱ ከፍተኛ ሆኖ ነበር፡፡ በሁለቱም በኩል ውጤቱ መጥፎ ሆኖ ነበር፡ ተቃውሞው እየተጠናከረ ሄደ፡፡
የመሐመድ አጎት አቡ ጧሊብ ከተቃዋሚዎች ጥቃት ከለላ ሆነው፡፡ መካ የነበሩትም ወደ አጎቱ ዘንድ መጥተው “አቡ ጧሊብ ሆይ የአባትህ ወንድም ልጅ አማልክቶቻችንን እረግሟል፡፡ ኃይማኖታችንንም ተሳድቧል፡፡ በሕይወት አካሄዳችንም ተሳልቋል፡፡ አንድም እንድታስቆመው ይገባል፡፡ አሊያም ጉዳት እንድናደርስበት ልትፈቅድልን ይገባል፡፡” ሲሉ ነገሩት አቡ ጧሊብ ግን በሀሳባቸው አልተስማማም፡፡
የመሐመድን አዲስ ኃይማኖት ያልተቀበሉት አረቦች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋም በመመስረት በመሐመድ ነገድ ላይ አድማ መቱ፡፡ ይሄም ደግሞ ምንም ዓይነት ጋብቻ ከነርሱ ጋር ላለመጋባትና የንግድ ልውውጥን አለማድረግን የሚያጠቃልል ነው፡፡
ይሄ ስድብና አደገኛ ሁኔታ መሐመድ በቅርብ ዘመዱም ተደርጎበታል፡፡ በራሱ ላይ ቆሻሻ ደፍቶበታል፡፡ ሶላት በሚያደርግበት ጊዜም የእንስሳ አንጀትም ወርውሮበታል፡፡ ስደቱ እየተጠናከረ ሲሄድ ሰማንያ -ሦስት ሙስሊም ወንዶች ከነቤተሰቦቻቸው የክርስቲያን አገር ወደ ሆነችው ኢትዮጵያ ተሰደዋል፡፡ በዚያም መጠለያ የተሰጣቸው ሲሆን ጥበቃም ተደርጎላቸዋል፡፡
ራስን መጠራጠር
አንድ ወቅት መሐመድ ከቁራይሾች ከደረሰበት ተፅዕኖ አንፃር አሃዳዊ አምላክን ከማምለክ መወላወል ውስጥ ገብቶ ነበር፡፡ መሐመድ አማልክቶቻቸውን የሚያመልክ ከሆነ እነሱም አላህን እንደሚያመልኩ ጥያቄ አቅርበውለት ነበር፡፡ ነገር ግን በሱረቱ አል-ካፊሩን 109፡6 መሰረት “ለናንተ ኃይማኖታችሁ አለላችሁ፤ ለኔም ኃይማኖቴ አለኝ” ሲል ሀሳባቸውን ተቃወመ፡፡ ነገር ግን በአልጠባሪ ዘገባ መሰረት መሐመድ ራሱን ተጠራጥሯል፡፡ የሰይጣን ጥቅሶች በመባል የሚታወቀው አን ነጅም ምዕ 53 ተገልጦለታል፡፡ ይሄም ደግሞ በመካውያን ዘንድ የሚመለኩት አማልክት ማለትም አል-ላት፣ አል-ዑዛ እና መናት የተሰኙት፡ “ምልጃቸው ተቀባይነት ያለው የተከበሩ ግሃረኒቅ (በራሪዎች) ናቸው” የሚል ነበር፡፡ አረማውያን የነበሩት ቁራይሾች ይሄንን በሰሙ ጊዜ እጅግ ተደስተው ከሙስሊሞቹ ጋር ማምለክ ጀመሩ፡፡ እንደዛም ሆኖ ጂብሪል የተባለው መልአክ መሐመድን ገሰጸው፡፡ እናም መሐመድ ያ ጥቅስ እንዲወገድ አደረገ፡፡ በዚህም ምክንያት ቁረይሾቹ የበለጠውኑ ጠላቶች ሆኑበት፡፡
ከዚህም በኋላ መሐመድ ቁርአን 22፡52 ላይ የሚገኘው “ከመልክተኛና ከነቢይም ከአንተ በፊት አንድንም አላክንም ባነበበና (ዝም ባለ) ጊዜ ፡- ሰይጣን በንባቡ ላይ (ማጥመሚያን ቃል) የሚጥል ቢሆን እንጅ፤ ወዲያውም አላህ ሰይጣን የሚጥለውን ያስወግዳል፤ ከዚያም አላህ አንቀጾቹን ያጠናክራል፤ አላህም አዋቂ ጥበበኛ ነው” የሚለው ቃል ተገለጠለት ፡፡ ይሄም ከሱ በፊት የነበሩት ነቢያት ብዙዎችን እንደሳቱ አመላካች ነበር፡፡ እዚህ ጋር የምንመለከተው እንግዲህ መሐመድ አሳፋሪ ሊሆን የሚችለውን ክስተት በመለወጥ ራሱን ከፍ ከፍ ለማድረግ እንደተጠቀመበት ነው፡፡
ውስጡን በጣም የጎዳው እርሱ አጭበርባሪ እንደሆነ የሚቀርበበት ክስ እና ቀልድ በበዛበት ጊዜ መሐመድ ስነ ምግባሩ ጥሩ እንደሆነ እና የተሳሳተ ሰው ሳይሆን ታማኝ ሰው እንደሆነ የሚገልጽ መገለትን ከአላህ ዘንድ ተቀበለ፡
ሱረቱ አል-ቀለም 68፡1-4 “በብርእ እምላለሁ በዚያም (መልአኮች) በሚጽፉት፡፡ አንተ በጌታህ ጸጋ የተጎናጸፍክ ስትሆን ዕብድ አይደለህም፡፡ ላንተም (ከጌታህ) የማይቋረጥ ዋጋ በእርግጥ አልለህ፡፡ አንተም በታላቅ ጠባይ ላይ ነህ፡፡” (53፡ 1-3)
“በኮከብ እምላለሁ በወደቀ (በገባ) ጊዜ ፡፡ ነቢያችሁ (ሙሐመድ) አልተሳሳተም፤ አልጠመመም ፡፡ ከልብ ወለድም አይናገርም፡፡” (53፡1-3)
እጅግ በዛ ያሉ ትውፊቶች እንደዘገቡት ከሆነ መሐመድ የራሱ ዘር፣ ጎሳ፣ ነገድና ቤተሰብ የበላይ እንደሆነ ያምን ነበር፡፡ እንደዚሁም የማይመስል መደምደምያ እስኪመስል ድረስ ዘሮቹ ከአዳም ዘሮች ሁሉ የተለዩ እርሱም ከተለየ ጎሳ (ሀሺማውያን) የተለየ ሰው እንደሆነ ተናግሯል፡፡ “እኔ በመንፈሴም በዘሬም ከእናንተ የተመረጥኩ ነኝ ስለሆነም ማንም ሰው አረቦችን ቢወድድ እኔን ከወደደ በኋላ በእኔ በኩል እነሱን ይወዳል” ሲል ተናግሯል፡፡
ተቀባይነት ያጣባቸው ተጨማሪ አጋጣሚዎች
ለመሐመድ ነገሮች በመልካም ሁኔታ አልሄዱለትም ነበር፡፡ በአንድ ዓመት ውስጥ ባለቤቱን ከድጃን እና አጎቱን አቡ ጧሊብን በሞት አጥቷል፡፡ ይሄ ደግሞ ቀላል የማይባል አስደንጋጭ ኩነት ነበር፡፡ የእነሱ እርዳታና ጥበቃ ባይኖር ኖሮ ቁራይሾች የበለጠ በእርሱ ላይ ጠላት ለመሆን ይደፋፈሩ ነበር፡፡
የአረቡ ማኅበረሰብ ግንባር ፈጥሮ የመረዳዳትና የመመካከር መሰረት ነበረው፡፡ የደህንነት ጥበቃ የሚፈለግበት አንዱ መንገድ ያ ሰው ከአንተ የተሻለ ጠንካራ ሆኖ ሲገኝ ነው፡፡ ለመሐመድና ለተከታዮቹ አደገኛ ነገሮች እየጨመሩ ከመምጣታቸው የተነሳ እንደዚሁም በራሱ ጎሳዎች ተቀባይነትን በማጣቱ ከሌሎች ዘንድ ትድግና መፈለግን ምርጫው አድርጎ ነበር፡፡ መሳቂያና መሳለቂያም ሆኖ ነበር፡፡ ከታኢፍም በአመጽ ተባርሮ ነበር፡፡
የቱንም ያህል ሁኔታዎች ለመሐመድ መልካም ባይሆኑም በስተመጨረሻ እርሱን ሊታደጉ የሚችሉ ማኅበረሰቦችን ማግኘት ችሎ ነበር፡፡ እነዚህም ብዙ አይሁዶች በሚኖሩባት በመካ የሚኖሩ አረቦች ናቸው፡፡
አዲስ ተባባሪዎችና ከመካ ሽሽት
በመካ በሚደረገው አመታዊ ትርኢት ላይ ከመዲና የሆኑ በቡድን የተደራጁ ጎብኚዎች ለመሐመድ ያላቸውን ታማኝነትና ታዛዥነት ለመግለጽ ቃል ኪዳን በመግባት እሱ ላስተማረው የአንድ አምላክ መልእክት ለመኖር ተስማምተዋል፡፡
በቃልኪዳኑ የመጀመርያ ጊዜ ለመዋጋት የተደረገ ምንም ዓይነት ራስን መስጠት አልነበረም፡፡ በቀጣዩ ዓመት በነበረ ትርኢት ግን ከመዲና የሆኑ በዛ ያሉ ቡድኖች መሐመድ ለፈለገው ጥበቃ ቃል ኪዳን ገብተዋል፡፡ አንሳር ወይም “ረዳት” በመባል የሚታወቁት የመዲና ሰዎች ሐዋርያቸውን ሙሉ በሙሉ እንዲታዘዙ ይሄንን የማያደርጉት ግን ተገድለው እንዲቀበሩ የሚል ትእዛዝ አስተላልፎ ነበር፡፡
ከዚህ ውሳኔ በኋላ ሙስሊሞች የተረጋጋ የፖለቲካ ክበብ ለመመስረት ወደ መዲና መሰደድ ችለው ነበር፡፡ መሐመድ በመስኮት ሾልኮ ወደ መዲና ለማምለጥ የመጨረሻው ሰው ነበር፡፡ መዲና በደረሱ ጊዜ መሐመድ መልክቱን ያለምንም እንቅፋት እና በሚገባቸው ሁኔታ በማቅረቡ ብዙ አረቦች ወደ እስልምና ተለውጠዋል፡፡ በዚያን ጊዜ መሐመድ የሃምሳ ሁለት ዓመት ጎልማሳ ነበር፡፡
መካ በቆየባቸው ጊዜያቶች መሐመድ በራሱ ቤተሰቦች እና ጎሳዎች ተቀባይነትን ያጣ ሰው ነበር፡፡ ጥቂት ለየት ያሉ የተዋረዱ ድሆች በእርሱ አምነዋል፡፡ ሆኖም አብዛኛዎቹ ተሳልቀውበታል፣ አስፈራርተውታል፣ አዋርደውታል በተቀሩት ሁሉ ጉዳት እንዲደርስበት ተደርጓል፡፡
መሐመድ ለመጀመሪያ ጊዜ በራሱ እርግጠኛ አልነበረም፡፡ በነብያዊ ጥሪው ላይ ፍርሃት ነበረው፡፡ አንድ ወቅት የቁራይሾችን አማልክት የተቀበለ መስሎ ነበር፡፡ ሆኖም ግን በስተመጨረሻ የቱንም ያህል ተቃውሞ ቢኖርበትም መሐመድ ቁርጠኛ በሆነ ሁኔታ በመንቀሳቀስ ራሳቸውን ሙሉ በሙሉ ለርሱ የሰጡ ተከታዮችን ማፍራት ችሎ ነበር፡፡
ተቀባይነትን ማጣት እና የመካ መገለጥ
ሰላማዊ ምስክርነት?
ብዙ ጸሐፍት እንደሚናገሩት መሐመድ በመካ የቆየባቸው አስር ዓመታት ሰላማዊ ነበሩ፡፡ ይሄ አባባል በአንድ ጎኑ እውነት ነው፡፡ ነገር ግን በቁርአን የመካ ምዕራፎች ላይ የቱንም ያህል አካላዊ ጉዳት የታዘዘም ባይሆንም እነዚህ ቀደምት መገለጦች የመሐመድን ጎረቤቶች አስፈሪ በሆኑ ንግግሮች በሚቀጥለው ህይወት ለተቃዋሚዎች የተዘጋጀውን አሳቃቂ ቅጣት በመግለጽ ማስፈራራታቸው አልቀረም፡፡
በቁርአን ውስጥ የሚገኙት የመካ ፍርዳዊ ጥቅሶች ዓላማ በቁራይሽ አረቦች ተቃውሞ በተጻራሪ መሐመድን መደገፍ ነበር፡፡ ለምሳሌ ያህል ብንወስድ መሐመድ በሙስሊሞች ላይ የሚስቁ የከፋ ቅጣት እንደሚያገኛቸው ተናግሯል፡፡ በገነት የሚኖሩ ሙስሊም አማኞች በምቾት ውስጥ ሆነው ወይን እየጠጡ ሲደሰቱ ሙስሊም ያልሆኑት ደግሞ በእሳት ውስጥ እየተጠበሱ ሲቃጠሉ ወደ ታች እያዩ ይስቁባቸዋል፡፡ (83፡29-36)
ይሄ የፍርድ መልእክት በመካዎች ዘንድ ያለምንም ጥርጥር የግጭት እሳት እንዲቆሰቆስ አድርጓል፡፡ ጣዖታትን የሚያመልኩ ሰዎች የሰሙትን ነገር ሊወዱት አልቻሉም፡፡
አስቀድሞ ማስጠንቀቅ በመካ
መሐመድ የዘላለም ፍርድን ብቻም አልነበረም የሰበከው፡፡ ኢብን ኢስሃቅ እንደዘገበው ከሆነ አስቀድሞ በመካውያን ዘመን መሐመድ ጣዖታውያኑን ለመግደል ሐሳብ እንደነበረው አስቀድሞ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር፡፡ “እናንተ ቁራይሾች ትሰሙኛላችሁን? ህይወቴን በእጁ ላይ ባደረገው እናንተን ጭፍጨፋን አመጣባችኋለሁ፡፡”
መሐመድ ወደ መዲና ከመሸሹ በፊት በቡድን የተደራጁ ቁራይሾች ወደ እርሱ መጥተው ፊት ለፊት በመጋፈጥ እርሱን የማይቀበሉትን እንደሚገድል ተናግሯል ሲሉ ከሰሱት “መሐመድን የማትከተሉት ከሆነ ትሰዋላችሁ፡፡ ከሞት ከተነሳችሁም በኋላ በእሳት ባህር ውስጥ ትቃጠላላችሁ” ብለሃል ሲሉ ነበር የከሰሱት “መሐመድም እውነት ነው ብያለው ደግሞም ትክክል ነኝ” ሲል ምላሽ ሰጥቷል፡፡
በሙስሊሞች ላይ በመዲና ከደረሰው ጠንካራ ተቀባይነትን ማጣት የተነሳ መለኮታዊ ምሪትን በማግኘት በጠላቶቻቸው ላይ ጦርነትን ለማወጅ ተገደው ነበር፡፡
አሸናፊዎችና ተሸናፊዎች
ስኬትን፣ ማሸነፍንና መሸነፍን የሚያሳይ ቋንቋን አስመልክቶ ኢስላማዊው ፅንሰ ሐሳብ በመጀመርያ የተገለጸው መሐመድ በመካ በቆየባቸው አስራ ሦስት ዓመታት አጋማሽ ላይ እንደነበር በቁርአን ቁጥሮች ላይ እንደ ጭብጥ ሆኖ ቀርቧል፡፡ በእነዚህ ጊዜያቶች በሙሴና በግብፃውያን ጣዖታት ማካከል የተደረገውን ግጭት በአሸናፊና በተሸናፊ መካከል እንደነበር በተደጋጋሚ ለማጣቀሻነት ተጠቅሞበታል፡፡ (20፡64፣69፤ 26፡40-44፤ 29፡39)
በመጨረሻዎቹ የመካ ጊዜያት መሐመድ ስኬትን አስመልክቶ የተጠቀመባቸው ቃላቶች በእርሱና በተቀናቃኞቹ መካከል የነበረውን ትግል የሚያሳዩ ነበሩ፡፡ በአስረኛው ሱራ ወደ መዲና የተደረገው ስደት ከመጀመሩ በፊት መሐመድ የአላህን መገለጥ የማይቀበሉትን ተሸናፊዎች ናቸው ሲል አውጇል፡፡ (10፡95)
የመሐመድ ‘ፊትና’ ንጽረተ ዓለም
መከራ፣ ስደት፣ ፈተናን የሚያመለክተው ፊትና የተሰኘው የአረብኛ ቃል መሐመድ ወደ ወታደራዊ መሪነት ቀስ በቀስ እንዴት እንደተሸጋገረ ለማወቅ በጣም ወሳኝ ነው፡፡ ስርወ ቃሉ የመጣው “ከሆነ ነገር መመለስ፣ መፈተን፣ ማማለል፣ ለችግር መዳረግ” የሚሉ ትርጉሞች ካሉት ፋታና ከሚል ቃል ነው፡፡ መሰረታዊ ትርጓሜውም ብረትን በእሳት ውስጥ በማሳለፍ ብረትነቱን ማረጋገጥ የሚለውን ሊወክል ይችላል፡፡ ፊትና ፈተና ወይም መከራን በአዎንታዊና በአሉታዊ መልኩ የሚያሳይ ነው፡፡ ይህም ስቃይንም የሚያጠቃልል ነው፡፡
ፊትና የቀደሙት የሙስሊም ማኅበረሰብ አባላት ሙስሊም ካልሆኑት ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት ቁልፍ የሆነ የስነ መለኮት ፅንሰ ሐሳብ ሆኖ ነበር፡፡ መሐመድ ቁራይሾች ፊትናን ማለትም፤ ስድብን፣ ስም ማጥፋትን፣ ስቃይን፣ ማግለልን፣ የኢኮኖሚ ተፅዕኖ ማድረግን እና ሌሎች ተፅዕኖዎችን በመጠቀም ከእስልምና ለመሸሽ ሞክረዋል፣ ሌሎችንም ከእስልምና አደናቅፈዋል የሚል ክስ አቅርቦባቸው ነበር፡፡ መዋጋትን አስመልክቶ በመጀመርያ የተገለጠው ቁጥር ግልጽ እንደሚያደርገው የመዋጋትና መግደል አጠቃላይ ዓላማው ፊትናን ለማስወገድ ነው፡፡
እነዚህንም የሚጋደሉዋችሁን (ከሓዲዎች) በአላህ መንገድ ተጋደሉ፤ ወሰንንም አትለፉ፤ አላህ ወሰን አላፊዎችን አይወድምና፡፡
ባገኛችኋቸውም ስፍራ ሁሉ ግደሉዋቸው፤ ከአወጧችሁም ስፍራ አውጥዋቸው ፤ መከራም ከመግደል ይበልጥ የበረታች ናት፤ በተከበረው መስጊድም ዘንድ በርሱ ውስጥ እስከሚጋደሉዋችሁ ድረስ አትጋደሉዋቸው፤ ቢጋደሉዋችሁም ግደሉዋቸው፤ የከሀዲዎች ቅጣት እንደዚህ ነው፡፡ ቢከለከሉም አላህ መሀሪ አዛኝ ነው፡፡
ሁከት እስከማይገኝና ኃይማኖት ለአላህ ብቻ እስከሚሆን ድረስ ተጋደሉዋቸው፤ ቢከለክሉም ወሰንን ማለፍ በበዳዮች ላይ እንጂ የለም (ወሰን አትለፉባቸው)፡፡ (2፡190-193)
የሙስሊሞች ፊትና “መከራም ከመግደል ይበልጥ የበረታች ናት” ተብሎ መነገሩ አስፈላጊ ነጥብ ነው፡፡ በተቀደሰው ወር (የአረብ ጎሳ ልማድ ውጊያን በሚከለክልበት ወር) በመካ ነጋዴዎች ላይ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ ተመሳሳይ የሆነ ቃል ተገልጧል (2፡217)፡፡ የከሃዲዎችን ደም ማፍሰስ ሙስሊም ከኃይማኖቱ እንዲያፈነግጥ ከማድረግ ያነሰ ነገር መሆኑ ተመልክቷል፡፡
በዚህ ጥቅስ ውስጥ ያለ ሌላኛው ወሳኝ ነገር “ምንም ዓይነት ፊትና እስከማይኖር ድረስ ተዋጓቸው” የሚለው ነው፡፡ ይህም በመዲና በሁለኛተው ዓመት ላይ ከበድር ጦርነት በኋላ ተደግሟል (8፡39)፡፡
እነዚህ ሁለት ሁለት ጊዜ የተገለጡት የፊትና ሐረጎች ሰዎች ወደ እስልምና እንዳይገቡ የሚከለክል ምንም ዓይነት እንቅፋት ባለበት ጊዜ ወይንም ደግሞ ሙስሊሞች እምነታቸውን እንዲክዱ የሚያደርግ ነገር በተፈጠረበት ጊዜ ላይ ጂሃድ የተፈቀደ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ ሰዎችን መዋጋት እና መግደል ምናልባት የትኛውንም ያህል አሳዛኝ ቢሆንም እስልምናን መናቅ ወይንም እንቅፋት መሆን ከዚያ ይከፋል፡፡
አብዛኞቹ ሙስሊም ምሑራን ፊትና የአለማመንን መኖር ጭምር ያጠቃልላል ስለሚሉ ይህ ሐረግ “አለማመን ከመግደል ይከፋል” ተብሎ ሊተረጎም ይችላል፡፡
በንደዚህ ዓይነት መንገድ የምንረዳው ከሆነ እንግዲህ “ፊትና ከመግደል ይከፋል” የሚለው ሐረግ ሙስሊሞችን ቢተናኮሉም ባይተናኮሉም የመሐመድን መልዕክት የተቃወሙ ከሃዲዎችን ሁሉ ለመግደል ዋስትና ይሰጣል ማለት ነው፡፡ የታላቁን ሀተታ ሰጪ የኢብን ከቲርን ንግግር ለመጠቀም ያህል ለከሃዲዎች “አለማመንን መፈጸም” ከነርሱ መገደል ይልቅ የባሰ ክፋት ነው፡፡ ይህ አለማመንን በማስወገድ እስልምናን በተቀሩት አካባቢዎች ላይ የበላይ ለማድረግ ጦርነትን መጠቀምን ያጸድቃል (2፡193፣ 8፡39)፡፡
ሙስሊም ላልሆኑት ያለው እንደምታ
ሙስሊም ያልሆኑትን አለመቀበል የሚለው ኢስላማዊ ህግ የመነጨው ከመሐመድ ስሜታዊ ንጽረተ ዓለም እና ተቀባይነት ማጣትን አስመልክቶ ካለው ምላሽ ነው፡፡ በመጀመርያ መሐመድ ጠላትነቱ ከራሱ ጎሳ የሆኑ ጣዖታት አምላኪ አረቦች እንደሆኑ ትኩረት አድርጎ ነበር፡፡ እነዚህ ጣዖታውያን የሆኑ አረቦች በእስልምና አስተምህሮ ላይ ከነበራቸው መጥፎ አመለካከት የተነሳ ተገቢውን ምላሽ መስጠት እንደሚያስፈልግ መሐመድ ያምን ነበር፡፡ መሐመድ የመጽሐፉ ሰዎች ከሚላቸውም ተመሳሳይ ውግዘት ደርሶበት ነበር፡፡ እስልምናን እንደመቃወማቸው መጠን እንዲጨቆኑ እና እንደ የበታች እንዲቆጠሩ ወንጀለኞች ናቸው የሚል ታርጋ ተለጥፎባቸዋል፡፡
በሌሎች የመወገዝ ተቃውሞዎች
የመሐመድን የነብያዊነት ታሪክ በምንመለከትበት ጊዜ ተቀባይነት ስለማጣት የተሰጡ የተለያየ ደረጃ ያላቸውን ምላሾች ማጤን እንችላለን፡፡ በመጀመርያዎቹ ጊዜያቶች እንደምንመለከተው ከነበረበት ጠንካራ ውግዘት የተነሳ ራሱን የማጥፋት አስተሳሰብ፣ አጋንንት እንደተቆጣጠረው አድርጎ መፍራትና ተስፋ የመቁረጥ ሁኔታ ነበር፡፡
ተቀባይነት የማጣትን ፍርሃት ለማሸነፍ ራስን የማፅደቅያ ምላሾችም ነበሩ፡፡ እነዚህም የሚያጠቃልሉት አላህ ጠላቶቹን በሲዖል ይቀጣል የሚለውን ጨምሮ አንዳንድ አሳፋሪ አጋጣሚዎችን ለመሸፈን ሁሉም ነብያቶች አንድ ወቅት በሰይጣን ተታለዋል የሚለውን የሚመስሉ ነገሮችን መናገር፣ የመሐመድን መገለጦች የተከተሉ ሰዎች በዚህም ሆነ በወዲያኛው ዓለም አሸናፊዎች እንደሚሆኑ አላህ መናገሩን የሚገልጹ ጥቅሶችን መናገር የመሳሰሉ ነገሮች ይጠቀሳሉ፡፡
በመጨረሻም የጠብአጫሪነት ምላሾች እየጎሉ መጡ፡፡ የዚህም ውጤት ሙስሊም ያልሆኑ ሰዎችን በመዋጋት እና በማሸነፍ ፊትናን ለማስወገድ ለሚያስችለው የጂሃድ አስተምህሮ መፈጠር ምክንያት ሆነ፡፡
ተገቢ ቅጣት
የመሐመድ በመዲና ያለው ወታደራዊ ጥንካሬ እያደገ ሲሄድ ድል እየተቀዳጀ መሄድ ጀመረ፡፡ ድል ያደረጋቸውን ጠላቶቹን የሚይዝበት መንገድ ለመዋጋት ስላነሳሳው ጉዳይ የሚለው ነገር አለው፡፡ ለዚህ ጥሩ ማስረጃ የሚሆነው ቀደም ሲል በመሐመድ ላይ የግመል ፋንድያ እና አንጀት ስለወረወረበት ኡቅባ ስለተባለው ሰው የሚነገረው ነው፡፡ ኡቅባ በድር በሚባል ጦርነት ተማርኮ መሐመድን እንዲህ ሲል ተማፀነው “መሐመድ ሆይ ልጆቼን ማን ይጠብቃቸዋል?” መሐመድም “ሲዖል” ካለ በኋላ ገደለው፡፡ ከበድር ጦርነት በኋላ የተገደሉ መካውያን አስከሬን በጉድጓድ ውስጥ ተጥሎ ነበር፡፡ መሐመድም የመካ ሟቾች ላይ ለመሳለቅ በእኩለ ሌሊት ወደ ጉድጓዱ ሄዶ ነበር፡፡
እንደዚህ ዓይነቱ ሁኔታ የሚያሳየው መሐመድ እርሱን ያወገዙትን ሁሉ ተገቢውን ቅጣት በመስጠት የሚበቀል መሆኑን ነው፡፡ ይሄንን ደግሞ እስከ ህይወቱ ፍፃሜ ድረስ ሲያደርገው ኖሯል፡፡
የመካ ድል መደረግ
መሐመድን የተቃወሙ ሁሉ ሁልጊዜ ስማቸው በሚገደሉት ሰዎች ተርታ መመደቡ የታወቀ ነበር፡፡ መሐመድ መካን ድል ባደረገ ጊዜ ሰዎችን መግደል ማበረታታት እንዲቆም አድርጎ ነበር፡፡ እንደዛም ሆኖ እንዲገደሉ ትእዛዝ የወጣባቸው ሰዎች ነበሩ፡፡ ሦስቱ ወደ ኋላ የተመለሱ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ሁለቱ መሐመድን በመካ የተሳደቡ ነበሩ፡፡ ከሦስቱ አንዷ ሴት ነበረች፡፡ ሌሎች ሁለት ሴቶች ደግሞ ስለ መሐመድ ምጸታዊ ግጥምን በመግጠማቸው ምክንያት ነበር፡፡
በመካ የተገዳዮች ስም ዝርዝር መኖሩ የሚያመላክተው መሐመድን የሚቃወሙ ሰዎች የነበሩ መሆናቸውን ነው፡፡ የመሐመድን አስተምህሮ በመቃወማቸው ምክንያት ለስቃይ የተዳረጉ አርአያ የሚሆኑ ሰዎች ነበሩ፡፡ እነዚህ ሰዎች ደግሞ እስልምናን ጥሎ መውጣት እንደሚቻል ያሳዩ ሰዎች ነበሩ፡፡ መሐመድን የተሳደቡም ሆነ በእርሱ የተሳለቁ አደገኛ ሁኔታ ያጋጥማቸው ነበር፡፡ ምክንያቱም የሌሎችን እምነት የመሸርሸር አቅም ስለነበራቸው ነው፡፡
የሁዳይቢያህ ስምምነት
መካ ድል ከመደረጓ በፊት ወደ መካ እንደሚጓዝ ራዕይ አይቶ ነበር፡፡ በወቅቱ ይሄ ሊሆን የሚችል አልነበረም፡፡ ምክንያቱም ሙስሊሞች ከመካውያን ጋር ጦርነት ለመግጠም በዝግጅት ላይ የነበሩበት ወቅት ነበርና፡፡ ራዕዩን ካየ በኋላ መሐመድ ጉዞ ሊያደርግ የሚችልበትን ስምምነት ተደራደረ፡፡ የስምምነቱን ውል ያደረጉት ደግሞ ለአስር ዓመት ነበር፡፡ ከስምምነቶቹ መካከል አንደኛው መሐመድ ያለመካውያን ጠባቂዎች ፈቃድ በማንኛውም ጌዜ ከእርሱ ጋር ካሉት ጋር ወደ መካ መጓዝ እንደሚችል የሚያሳይ ነበር፡፡ ይሄ ደግሞ የሚያጠቃልለው በዚያን ጊዜ ባርያዎች ተብለው የሚጠሩትንና ሴቶችንም ነው፡፡ ስምምነቱ ሁለቱም ወገኖች በነፃነት መጓዝ የሚችሉበትን ሁኔታ ያገናዘበ ነበር፡፡
አስገራሚው ነገር መሐመድ የገባውን የስምምነት ውል መጠበቅ አለመቻሉ ነው፡፡ ለዚህም ደግሞ ምክንያቱ ሰዎች ከመካ ወደ እርሱ ሲመጡ ባርያ በማድረግ ሴቶቹንም ሚስቶቹ በማድረጉ በተጨማሪም የአላህ ስልጣን ነው በማለት ስደተኞቹን ለመልቀቅ ፈቃደኛ አለመሆኑ ነበር፡፡ የመጀመርያው ጉዳይ ወንድሟ ሊመልሳት የመጣ ኡም ኩልትም የተባለች ሴት ጉዳይ ነበር፡፡ ነገር ግን ኢብን ኢስሃቅ እንዳስቀመጠው “አላህ ከልክሏል” በማለት መሐመድ ሀሳቡን ተቃውሟል፡፡
ሱራ 60 ለሙስሊሞች የሚመክረው ነገር ቢኖር ሙስሊም ያልሆኑ ሰዎችን ወዳጅ አድርገው እንዳይወስዱ ነው፡፡ እያንዳንዱ ሙስሊም መካውያንን በምስጢር ቢወዳጅ ክህደት እንደተደረገ ይቆጠር ነበር፡፡ ሙስሊም ያልሆኑት በማንኛው ምክንያት ሙስሊሞችን ከእምነታቸው እንዲያፈገፍጉ ምክንያት ናቸው ተብሎ ይታመን ነበር፡፡ ሱራ 60 እንዲህ ከሚለው የሁዳይቢያህ ስምምነት ጋር ይጋጫል፡ “እርስበርሳችን ምንም ዓይነት ጠላትነት አናሳይም፡፡ በምስጢር የምናደርገው የተለየ ነገርም አይኖረንም፡፡” ይሁንና ሙስሊሞቹ በመካውያን ላይ ጥቃትን ከፍተው ድል ካደረጉ በኋላ ስምምነቱን ያፈረሱት ቁራይሾች እንደነበሩ ማስረጃ ሆኖ ቀርቦ ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ከጣዖታት አምላኪዎች ጋር ምንም ዓይነት ስምምነት እንዳይደረግ አላህ አወጀ፡፡
9፡3-5 “አላህ ከአጋሪዎቹ ንጹህ ነው...” “አጋሪዎቹን በአገኛችሁባቸው ስፍራ ግደሉዋቸው”
እንደዚህ ዓይነት ክስተቶች የሚያመለክቱት መሐመድ የማያምኑትን ሰዎች ሙስሊሞች ከእምነታቸው እንዲያፈነግጡ ከሚያደርጉት ወገን በመፈረጅ እነርሱ እስልምናን እስካለተቀበሉ ድረስ ከነርሱ ጋር ጤናማ የሆነ ግንኙነት እንዳይኖር ማድረጉን ነው፡፡
አይሁዶችን መታገል
በመዲናና በቃይባር ከሚኖሩ አይሁዶች ጋር መሐመድ የነበረውን ግንኘነት በተመለከተ “ የመጽሐፉ ሰዎች”ን ገና ከመሰረቱ አስገድዶ ቃል ኪዳን የማስገባት ውልን ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ ነበር፡፡
አይሁዶችን በተመለከተ መሐመድ በመጀመርያ የነበረው አመለካከት
በመካው ዘመን ከነበሩ ከአይሁዶች ጋር መሐመድ የነበረውን ግንኙነት በተመለከተ በብዙ አይሁዳዊ ነብያት መስመር ውስጥ በመግባት እርሱም ነብይ እንደሆነ ይናገር ነበር፡፡ በመካ እና በመጀመርያው ወር በመዲና የተገለጠውን ሱራ በምንመለከትበት ጊዜ በአንፃራዊነት ስለ አይሁዶች በጥቂቱ የተገለፁ ማጣቀሻዎች ነበሩ፡፡ ቁርአን በመካ ይኖሩ የነበሩትን አይሁዶች በመጥቀስ በሚናገርበት ጊዜ አንዳንዶቹ እስልምናን ያልተቀበሉ ሲሆኑ አንዳንዶቹ ደግሞ የመሐመድን መልዕክት እንደ በረከት አድርገው የተቀበሉትን ያመለክታል፡፡ (98፡ 1-8)
መሐመድ በመካ በነበረው ቆይታ ከአንዳንድ ክርስቲያኖች ጋር ግንኙነት ለመፍጠር ሞክሮ ነበር ግንኙነቱም አበረታች ነበር፡፡ ክርስቲያን የነበረው የከድጃ የአጎት ልጅ ዋራቃ መሐመድን እንደ ነብይ ተቀብሎት ነበር፡፡ እንደዚሁም በመካ የሚኖሩ የአቢሲኒያ ክርስቲያኖች ከእርሱ ጋር የመገናኘት እድል ስለገጠማቸው በእርሱ አምነው ነበር፡፡ ምናልባትም አይሁዶች የመሐመድን ማንነት በመለየት “ከአላህ የተላከ ግልፅ ምልክት” አድርገው እንደሚቀበሉትና ለመልዕክቱ አዎንታዊ ምላሽ እንደሚኖራቸው ተስፋ አድርጎ ነበር፡፡ ሱራ 98ን በምንመለከትበት ጊዜ መሐመድ አስተምህሮቱ ከአይሁዶች ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ ተናግሯል፡፡ ይሄ ደግሞ ጸሎት መጸለይና ለድሆች መስጠትን ያካትታል (98፡5)፡፡ በአይሁዶች ልማድ እንደሚደረገው በጸሎት ጊዜ በሶርያ አቅጣጫ ወዳለችው ወደ ኢየሩሳሌም እንዲዞሩ ተከታዮቹን አዟቸዋል፡፡ ኢስላማዊ ትውፊቶች እንደመዘገቡት ከሆነ መሐመድ መዲና ሲደርስ ከአይሁዳውያን ጋር ቃልኪዳን ተገባብቶ ነበር፡፡ ቃል ኪዳኑም አይሁዶችም ሆኑ ሙስሊሞች የራሳቸው ኃይማኖት ያላቸው ሲሆን አይሁዶች ለሙስሊሞች ታማኝነትን እንዲያሳዩ ትእዛዝ የታዘዘበት ነበር፡፡
በመዲና የደረሰ ተቃውሞ
በመዲና ለሚኖሩ የአይሁድ ማኅበረሰብ አባላት መሐመድ መልዕክቱን ማድረስ በጀመረ ጊዜ በፍጹም ያልጠበቀው ተቃውሞ ገጥሞት ነበር፡፡ ኢስላማዊ ትውፊቶች እንደሚናገሩት ከሆነ ተቃውሞው የቅናት ባህሪ አለው ይላሉ፡፡ አንዳንዶቹ የመሐመድ መገለጦች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማጠቀሻዎች አሉት፡፡ የአይሁድ መምህራን እነዚህን ጽሑፎች ስለመቃወማቸው ምንም ጥርጥር የለም፡፡ ከመሐመድ አተረጓጎም ጋር እንደሚቃረኑም ሳያመላክቱ አልቀረም፡፡ የሙስሊሞች ነብይ የሆነው (መሐመድ) የአይሁድ መምህራንን ጥያቄ ችግር ፈጣሪ እንደሆኑና ቁርአን ከሰማይ የወረደዉ ወደ እርሱ እንደሆነ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ በተደጋጋሚ መሐመድን ጥያቄ በመጠየቅ ሰዎች በሚገዳደሩት ጊዜ ሁኔታውን የሚጠቀምበት ሰዎች እርሱን እንዲቀበሉ በማድረግ ነው ለዚህም እማኝ የሚያደርገው ቁርአንን ነው፡፡
የመሐመድ ቀለል ያለው ስልት ምንድን ነበር? ካልን አይሁዶች አታላዮች መሆናቸውን ማረጋገጥ ነበር፡፡ ለዚህም ደግሞ ተስማሚ የሆነ ጥቅስን ከቁርአን ይጠቅስ ነበር፡፡ 936፡76፣ 2፡77)
ከአላህ ዘንድ የመጣው ሌላው ምላሽ ደግሞ አይሁዳውያን ሆን ብለውና አስበውበት ቅዱሳት መጽሐፍቶቻቸውን ውሸት እንዲቀላቀልባቸው አድርገዋል የሚል ነው፡፡ (2፡75)
በአይሁዳውያን መምህራንና በመሐመድ መሀከል የተደረገው ውይይት በኢስላማዊ ትውፊቶች ተተርጉሟል፡፡ ይሄም ደግሞ እንደ እውነተኛ ንግግር አልያም ለመሐመድ እሳቤ ምክንያታዊ ምላሾች እንደተሰጠ ተቆጥሮ ሳይሆን እንደ ፊትና (እስልምናንና የሙስሊሞችን እምነት እንደማጥፋት ተቆጥሮ) ነው፡፡
የተቃዋሚዎች ጥላቻን የተሞላ ስነመለኮት
መሐመድ ከአይሁዶች ጋር የተለዋወጣቸው አደናቃፊ ንግግሮች የሚያመላክቱት ለአይሁዶች የነበረው ጥላቻ ምን ያህል እያደገ የመጣ እንደነበር ነው፡፡ ከላይ በተገለጹት ጥቅሶች ለመግለጽ እንደተሞከረው አንዳንድ አይሁዶች እስልምናን በመቀበላቸው ምክንያት ቁርአን እስልምናን ከተቀበሉት ከጥቂቶቹ በስተቀር ሁሉም አይሁዶች የተረገሙ እንደሆኑ አውጇል፡፡ (4፡ 46)
ቁርአን እንደሚለው ከሆነ ባለፉት ጊዜያት አንዳንድ አይሁዶች በኃጢአታቸው ምክንያት ወደ ዝንጀሮነትና አሳማነት ተቀይረዋል (7፡ 166)፡፡ አላህ እንደዚሁ የነብያት ገዳዮች ብሏቸዋል (7፡166፣ 5፡60፣ 2፡56)፡፡
አላህ ቃል ኪዳንን ከሰበሩ ከአይሁዳውያን ጋር የነበረውን የባለቤትነት ግንኙነት አንስቷል (5፡70)፡፡ ይሄም የሆነበት ምክንያት ልባቸውን ስላደነደኑ ነው፡፡ ሙስሊሞች ሁሉጊዜ (ከጥቂቶች በስተቀር) ከሀዲዎች እንደሆኑ ያምናሉ፡፡ ቃል ኪዳናቸውን ስላፈረሱ አሁዶች ከሳሪዎች ተብለዋል (2፡ 27)፡፡
ወደ መዲና ከመምጣቱ በፊት የመሐመድ መገለጥ እንዳመላከተው አይሁዳዊነት ጠቀሜታ ነበረው (2፡62) ነገር ግን ይህ በ3፡85 ላይ ባለው ሀሳብ ተሽሯል፡፡ መሐመድ ወደ መዲና የመጣበት ምክንያት የአይሁዶችን ስህተት ለማረም መልዕክተኛ ሆኖ ነው (5፡115)፡፡
በሱራ 5፡115 መሰረት መሐመድ እንደደመደመው የተላከበት ቀዳማይ ዓላማ አይሁዳዊነትን ለመሻር፣ እስልምናን የመጨረሻው ኃይማኖት ለማድረግና ቁርአንን የመጨረሻው መገለጥ ሆኖ እንዲቀርም ጭምር ነው፡፡ ይሄንን መገለጥ የሚቃወሙ ሁሉ ከሳሪዎች ናቸው፡፡ ይሄ ደግሞ ለአይሁዳውያኖችም ሆነ ለክርስቲያኖች መቼም ቢሆን የጥንት ኃይማኖታቸውን እንከተል ቢሉ ተቀባይነትን የሚያገኝ አይደለም፡፡ ለመሐመድ እውቅና በመስጠት እስልምናን መቀበል የግድ ነው፡፡
ወደ ብጥብጥ የተሻገረ ተቀባይነትን ማጣት
በመዲና አይሁዶችን ለማስፈራራት ብሎም ለማጥፋት መሐመድ ዘመቻ አዘጋጀ፡፡ በበድር በሚኖሩ ጣዖት አምላኪዎች ላይ በተቀዳጀው ድል ስለተደፋፈረ ቀይኑቃ በሚባል ቦታ ላይ ወደሚኖሩ የአይሁድ ጎሳዎች ዘንድ በመሄድ በአላህ የበቀል ቁጣ አስፈራራቸው፡፡ ከዚያም ሰበብ ፈልጎ የቀይኑቃን አይሁዶች በመክበብ ከመዲና አባረራቸው፡፡
በመቀጠልም መሐመድ አይሁዶችን አደጋ ውስጥ የሚጥልና እንዲገደሉ የሚያደርግ ዓላማን ሰንቆ ተነሳ፡፡ ለተከታዮቹም “በኃይላችሁ ስር የወደቀን ማንኛውንም አይሁዳዊ ግደሉ” ሲል ትእዛዝን አስተላለፈ፡፡ “ለአይሁዶቹም እስልምናን ተቀበሉ ደህንነትም ይሆንላችኋል” ሲል አወጀ፡፡
በመሐመድ የመረዳት ዕውቀት ውስጥም ታላቅ የአቅጣጫ ለውጥ ተደረገ፡፡ ሙስሊም ያልሆኑት መኖር የሚችሉትና ንብረታቸው ሊጠበቅ የሚችለው እስልምናና ሙስሊሞችን መርዳት ከቻሉና ሲያከብሯቸው ብቻ እንደሆነም ደነገገ፡፡ ከዚህ ውጭ ያለው ግን ፊትና ስለሆነ የሀሰት እነርሱን ለመዋጋት የመነሻ ሰበብ ሆናል፡፡
ሙሐመድ ከአይሁዶች ጋር የነበረውን ጉዳይ ገና አልጨረሰም፡፡ በኑ ናዲር የተባሉት ጎሳዎች በርሱ ትኩረት ውስጥ ለመግባት ቀጣዮቹ ነበሩ፡፡ ሁሉም የናዲር ጎሳ አባላት ቃል ኪዳናቸውን በማፍረስ ተከሰው ጥቃት ደረሰባቸው፡፡ ከረጅም ጊዜ ከበባ በኋላ ንብረታቸውን ለሙስሊሞች እንደ ምርኮ በመተው ከመዲና ተባረሩ፡፡
ከዚህ በኋላ መሐመድ በስተ መጨረሻ የቀረውን የአይሁዶች ጎሳ ቁራይዛዎችን ከበበ፡፡ ከመልአኩ ጅብሪል የመጣ ትእዛዝን መሰረት ባደረገ መልኩ መሆኑ ነው፡፡ አይሁዳውያንም ያለምንም ምክንያት እጃቸውን እንደሰጡ ወንዶቻቸውን መዲና በሚገኘው የገበያ ስፍራ አንገታቸው እንዲቀላ ተደረገ፡፡ እነዚህም ከስድስት መቶ እስከ ዘጠኝ መቶ እንደሚደርሱ ይገመታል፡፡ ሴቶችንና ልጆችንም ለሙስሊሞቹ ባርያዎች እንዲሆኑ ተደረገ፡፡
መሐመድ በአረብ ምድር ከሚኖሩ አይሁዶች ጋር ያለውን ነገር ሁሉ አልጨረሰም ነበር፡፡ በመዲና የሚኖሩትን ካጠፋ በኋላ ቃይባር ላይ ከፍተኛ ጉዳት አደረሰ፡፡ የቃይባር ዘመቻ የተጀመረው ምላሽን በሚጠይቁ ሁለት ምርጫዎችን ነበር፡፡ እነርሱም ወደ እስልምና መለወጥ አልያም መሞት የሚሉ ነበሩ፡፡ እንደዛም ሆኖ ሙስሊሞች በቃይባር አይሁዶችን ባሸነፉ ጊዜ ሦስተኛ ምርጫ እንደ መደራደርያ ሆኖ ገባ፡፡ ከሚሆነው ነገር የተነሳ እጅ በመስጠት በቃይባር የሚኖሩ አይሁዳውያን የመጀመርያዎቹ የዲህሚ ህግ ተገዢዎች ሆኑ፡፡
መሐመድ ከአይሁዶች ጋር የነበረውን ግንኘነት አስመልክቶ ለማቅረብ የተሞከረውን ሀሳብ እዚህ ላይ ብንቋጨው የተሻለ ነው፡፡ አንድ ልንገነዘበው የሚገባ ነገር ቢኖር ቁርአን አይሁዶችንና ክርስቲያኖችን “የመጽሐፉ ሰዎች” በማለት በአንድ ጎራ ይመድባቸዋል፡፡ የመሐመድ ህይወትና ቁርአን ለክርስቲያኖች እና ለአይሁዶች እንደ “የመጽሐፉ ሰዎች” የሰጡት ቦታ በየዘመናቱ የሚኖሩ አሁዶች እና ክርስቲያኖች ለሚታዩበት መንገድ እንደ ሞዴል ሆኖ እንደሚያገለግል ግልጽ ነው፡፡
“ተጠቂዎች ነን”
የመሐመድ መርሐ ግብር እንደ ዋና ነገር አፅንዖት በመስጠት ይናገር የነበረው የሙስሊሞችን ተጠቂዎች መሆን ነበር፡፡ የስነመለኮታዊ አቋምን በቀጣይነት ለማስቀጠል ድል ማድረግ ማለት ነፃ መውጣት እንደ ማለት ይቆጠርም ነበር፡፡ በሙስሊሞች ላይ ይደረግ የነበረው “መጠነ ሰፊ ቅጣት” ጠላቶቻቸው የህሊና ቅጣት እንዲደርስባቸው ያደረገም ነበር፡፡ እንደ መለኮታዊ ድንጋጌ ከሆነ የሙስሊሞች ስቃይ “ከመገደል ይልቅ የከፋ” ስለሆነ እያንዳንዱ ሙስሊም ከጠላቶቹ ለሚሰነዘርባቸው ጥቃት ምንም ዓይነት የከፋ ምላሽ መስጠት እንደ ግዴታ ይቆጠራል፡፡ ሙስሊሞች ተጠቂዎች በሆኑ መጠን የእምነት አቅጣጫው ገፅታ የሚያመላክተው የእስልምናን አስተምህሮ አስፈላጊነት ነው፡፡
በቁርአን እና በመሐመድ ሱና ላይ የተመሰረተው ይህ ስነ መለኮታዊ አስተሳሰብ ነው ብዙ ጊዜ ሙስሊሞች የነርሱ ተጠቂነት እነርሱ ካጠቋቸው ሰዎች ጉዳት ይልቅ እጅግ የከፋ መሆኑን ደጋግመው እንዲናገሩ የሚያደርጋቸው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ የአልጄርያ የኃይማኖታዊ ፖለቲካ ፕሮፌሰር በሆኑት በፕሮፌሰር አህመድ ቢን መሐመድ ተንጸባርቋል፡፡ ከዶክተር ዋፋ ሱልጣን ጋር በአልጀዚራ ቲቪ ላይ በተደረገ ክርክር በዶክተር ዋፋ ንግግር በመቆጣት እንዲህ ብሎ ጮኸ፡
ተጠቂዎቹ እኛ ነን! ... በኛ (በሙስሊሞች) መካከል በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ንጹህ ሰዎች አሉ ነገር ግን በናንተ መካከል ያሉት በአስራዎች፣ በመቶዎች ወይንም በሺዎች ቢቆጠሩ ነው፡፡
ይህ የመጨቆን አስተሳሰብ እስከዚህ ዘመን ድረስ በብዙ የሙስሊም ማህበረሰቦች መካከል እንደ ወረርሺኝ በመሰራጨት ለራሳቸው ስራ ኃላፊነት የመውሰድ አቅማቸውን አዳክሞታል፡፡
ሌሎችን የሚያወግዘው መሐመድ
የመሐመድን ሌሎችን ያለመቀበል ታሪክ ቅኝት እዚህ ላይ መጠቅለሉ የተሻለ ይሆናል፡፡ ሌሎቹን በመግፋቱና ተበቃይነቱ በጠላቶቹ ላይ ስኬትን እንዲቀዳጅ አድርጎታል፡፡
እንደተመለከትነው የሙስሊሞች ነቢይ በተለያዩ ደረጃዎች ላይ ተቀባይነት ማጣትን አስተናግዷል፡፡ በቤተሰቡ መካከል፣ በመካ ከነበረው ከራሱ ማህበረሰብ እና በመዲና ከነበሩት አይሁዶች ዘንድ ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡ ምላሹን በምንመለከትበት ጊዜ መሐመድ ራሱን የመቀበል ችግር ነበረበት፡፡ በመቀጠልም ለራሱ እውቅና መስጠት ውስጥ ገባ፡፡ ከዚያም ወደ ጸብ አጫሪነት ተሸጋገረ፡፡ ያለ ወላጅ ያደገው መሐመድ ወላጅ አልባ ልጆችን አበዛ፡፡ አጋንንቶች እንዳደሩበት በማሰብ እራሱን ከመጠራጠሩ የተነሳ ህይወቱን የማጥፋት ሙከራ ያደርግ የነበረው ሰው ሌሎችን የማይቀበል እና የራሱን እምነት በሌሎች ላይ በኃይል በመጫን የሌሎችን ኃማኖት ለማጥፋት በወታደራዊ ኃይል የሚጠቀም ቀንደኛ ሰው ሆነ፡፡ በመሐመድ ስሜታዊ ንፅረተዓለም ሙስሊም ያልሆኑትን ማሸነፍና ማዋረድ ተከታዮቹን “ይፈውሳቸዋል” ብሎ ያምን ነበር፡፡ ይህ ፈውስ “የኢስላማዊ ሰላም” የሚመጣውና አሸናፊ መሆን የሚቻለው በጦርነት ነው፡፡ ይሄ እውነት ደግሞ በቁርአን ውስጥ ተረጋግጧል፡፡ (9፡14-15)
በመጀመርያ መሐመድና ተከታዮቹ በመካ በሚኖሩ የመድበለ አማልክት አምላኪዎች ዘንድ ስደት ደርሶባቸዋል፡፡ ነገር ግን በመዲና የተጠናከረ ኃይል እንዳለው በተረዳ ጊዜ ነብያዊ አገልግሎቱን ያልተቀበሉትን የመድበለ አማልክት አምላኪዎቹንም፣ የአይሁዶቹንም ሆነ የክርስቲያኖቹን አቅም ማዳከም በመጀመሩ ዝምታን መምረጥና መገዛትን እንደ መፍትሔ ወስደውት ነበር፡፡
መሐመድ ሐሳባዊና ወታደራዊ መርሐ ግብር በመመስረት እርሱንና የኅብረተሰቡን እምነት በማንኛውም አገላለጽ ያልተቀበሉትን ስልታዊ በሆነ መንገድ ለማስወገድ ተንቀሳቅሷል፡፡ እንደ መሐመድ አባባል ከሆነ የመርሐ ግብሩ መሳካት ነብያዊ አገልግሎቱን የሚያረጋግጥና ነፃ አውጪ መሆኑን አመላካች ነው፡፡
የመሐመድ ነብያዊ አገልግሎት እንዴት እያደገ እንደሄደ ቁርአን ያሳያል፡፡ ይሄ ደግሞ በመሐመድ ግላዊ ጠንካራ ማስረጃዎች የተገለጠ ነው፡፡ እርሱን ያልተቀበሉትን የመግፋት፣ ጠላትነትና ጸብ አጫሪነቱ እያደገ መሄድ ችሏል፡፡ ሙስሊም ባልሆኑት ላይ የሚጫኑት ባህርያቶች ማለትም ዝምታ፣ የህሊና ክስና ዝቅ ዝቅ ማለት መሰረታቸው መሐመድ ራሱ ተቀባይነትን ከማጣቱ የተነሳ የመጡ ናቸው፡፡ የመሐመድ ሀይለኛነት፣ ከፍተኛ ጫናና ሌሎችን አለመቀበል የሚደርስባቸው “ከአላህ በስተቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ አምናለሁ፡፡ በመሐመድም ነብይነት” የሚለውን ለመቀበል እምቢ የሚሉት ሁሉ ናቸው፡፡