መስጊድ እና በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለው ሚና

በባልታዛር እና አብደናጎ

ክፍል ሁለት

መስጊድ (በአረብኛው መስጂድ)

በአረብኛው መስጂድ ተብሎ የሚታወቀው መስጊድ የተገኘው ከሥርወ-ቃሉ ሰጂዳ ወይም ሱጁ ሲሆን ትርጉሙ አምልኮ ማለት እንደሆነ ብናስብም ትክክለኛ ትርጉሙ ግን “በአፍጢም መደፋት” ማለት ነው። በእስልምና ውስጥ የተገለጠውን የአላህን ሕግ፣ ሸሪዓ አጥብቆ መያዝና መተግበር አምልኮ ነው።

በእስልምና ውስጥ በሰውና በአላህ መካከል ግላዊ ግንኙነትን የሚያመላክት አንዳችም አስተሳሰብ የለም። እግዚአብሔር አባታችን እንደሆነ የሚያስተምረው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምሕርት በእስልምና ውስጥ በጭራሽ አይገኝም። በተመሳሳይ መልኩ ሰው ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ ይችል ዘንድ እና እንዲያውቀው የሚያስችለው የክርስቶስ ለሰዎች መሞትም በእስልምና ውስጥ አይታወቅም።

የሰው ልጆች በእግዚአብሔር አምሳል የመፈጠራቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ፤ በሙስሊሞች የሚወገዝና ቀድሞ የነበረን ታማኝነት መካድ ተደርጎ ይቆጠራል። ስለዚህ ክርስቲያኖች የሚያውቁትና (የሚደሰቱበት) የእግዚአብሔር አባታዊ ፍቅር በእስልምና ውስጥ በጭራሽ የሚታሰብ አይደለም። አምልኮ በእስልምና ውስጥ ባርያ ለጌታው የሚያደርገውን መገዛትና ፍፁም እጅ መስጠትን የሚያሳይ ነው።

ሸሪዓ ወይም የተገለጠውን የአላህን ሕግ መተግበር የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን፣ በፈቃደኝነት ይደረግም አይደረግ በራሳቸውና በሌሎች ላይ የሚጥሉት ግዴታ ነው። ይህ ተፈጻሚ በማይሆንበት ጊዜ ደግሞ ጅሐድ አስፈላጊ ሆኖ ይገኛል።

መስጊድ እንደ መሰብሰቢያ ስፍራ (በአረብኛው ጁምአ)

መስጊድን ለመጥራት በተለምዶ የሚጠቀሙት ሥርወ-ቃሉ መሰብሰብ ወይም ስብሰባ የሆነውን የአረብኛውን ቃል ጁምአ ነው። መስጊድ ለሙስሊሙ ማኅበረሰብ በተገለጠው የእስልምና ሕግ መሠረት የማዕከላዊ ሥልጣንን ሚና የሚጫወትና በሃይማኖታዊውም ሆነ በልዩ ልዩ ግዴታዎቻቸውና ደንቦቻቸው ላይ መመሪያና ትዕዛዝ የሚያሳልፍላቸው፤ እንዲሁም በዙሪያቸው ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር ያላቸውን ግንኙነት በተመለከተ የሚያመለክታቸው ስፍራ ነው።

ልዩ ልዩ ዓይነት መስጊዶች

ሁሉም መስጊዶች በተዋረዳቸው እኩል አይደሉም። ሶስቱ ልዩነቶች የሚከሰቱት በስነ-መለኮት ወይም በመሠረተ-እምነት ልዩነት፤ ማለትም፦ በሺዓ እናሱኒዎች መካከል ወይም በሱፊና በሳላፊ መካከል ካለው ልዩነት የተነሳ ብቻ አይደለም። በአንድ የእስልምና ዘርፍ ውስጥ እንኳን ያሉ መስጊዶች በጥቅማቸው የተለያየ ደረጃ ይሰጣቸዋል።

ይህ ዓይነቱ መከፋፈል የተጀመረው መሐመድ ራሱ በሌላ በየትኛውም ስፍራ በሚገኝ መስጊድ የሚደረገው አንድ መቶ ሺህ ፀሎት በመካ በሚገኘው በተቀደሰው ካባ መስጊድ ከሚደረገው አንድ ፀሎት ጋር ይስተካከላል ብሎ በተናገረ ጊዜ ነው። አያይዞም በሌላ ቦታ የሚደረገው አንድ ሺህ ፀሎት በመዲና በሚገኘው የእርሱ መስጊድ ከሚደረግ አንድ ፀሎት ጋር እኩል እንደ ሆነና በኢየሩሳሌም በሚገኘው በአል-አቅሳ መስጊድ የሚደረግ ፀሎት ደግሞ በሌላ በየትኛውም ስፍራ ባለው መስጊድ ውስጥ ከሚደረጉ 500 ፀሎቶች ጋር እኩል እንደ ሆነ ተናግሯል።  ሸዓይቶችም ቁም፣ ኢስፋሀን፣ ማሻድ፣ ናጃፍ፣ ካራባላ የተሰኙት መስጊዶች በአቀማመጥ ቅደም ተከተላቸው የፀሎት ሚዛናቸው እየጨመረ እንደሚሄድ ያምናሉ።

ከላይ ከተጠቀሰውና ከሌሎች የተወሳሰቡ ምክንያቶች የተነሳ ሙስሊሞች ለመስጊዶቻቸው ከታሪካዊ ጥቅማቸውና ከልዩ ልዩ መነሳሳቶች አንጻር የመበላለጥ ቅደም ተከተል አስቀምጠውላቸዋል። ስለዚህ በካይሮ የሚገኙት ሁለት መስጊዶች በጥቂት ማይሎች ልዩነት የሚገኙ ቢሆኑም እንኳ ከሃይማኖታዊ ጠቀሜታቸው አንፃር ልዩነት አላቸው።  በምስር አል ጋዲዳ የተፀለየ ፀሎት በአሚር ኢብን አላስ መስጊድ ከሚፀለየው ፀሎት ያንሳል። ሁለት መንገዶችን ተሻግሮ ካለው መስጊድ ይልቅ የሰዒዳ ዘይነብ የተሻለ ጥቅም አለው።

አንድ መስጊድ ጠቃሚ ሆኖ እንዲቆጠር ጥንታዊ መሆኑ አይጠበቅበትም። ጠቃሚነቱ የሚለካው ከብዙ ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ምክንያቶች አንፃር እንዲሁም ከአስተምህሮውና ከስብከቱና ምን እና ማን እንደ ሠራው ከመመዘን አንፃር ነው። ለምሳሌም ያህል “ጃምአት ታብሊጊ” ከፓኪስታን ሀገር-አቀፍ እና ዓለም-አቀፍ ዋና ጽሕፈት ቤቱን ወደ ለንደን፣ ፓሪስ ወይም የትኛውም ቦታ ቢያዘዋውር ያለበት መስጊድ ሃይማኖታዊም ሆነ ፖለቲካዊ ጥቅሙ በእስልምናው ዓለም ውስጥ ይጨምራል። ለዚህም ምክንያቱ የመስጊዱ መሥራቾችና ምእመናን ቀጥተኛ የእስላማዊ ሚስዮናዊ ማሰልጠኛ ተቋም በማደራጀታቸውና የተልዕኮ ወኪልመሆናቸው ትኩረት እንዲሰጣቸው ያደረገ መሆኑና 7ኛውን ክፍለ ዘመን ቀላል ኑሮ፤ ሀሳባዊና ስነ-መለኮታዊ ንፅህና ሳያሰልስ በመስበኩ ነው።

“ጃምአት ታብሊጊ” በሙስሊሙ ማኅበረሰብ መካከል ያተረፈውን አክብሮትና አድንቆት ያገኘው በዓለም-አቀፉ እስላማዊ ማንሰራራት ውስጥ ዋነኛው ኃይል ስለሆነ ነው።

የእስልምና መሠረተ እምነት አካሄድ ከጅማሬ እስከ አጠቃቀምና በመስጊድ ውስጥ እስከ መተግበር፡ የሚከተለውን ዝርዝራዊ ቅደም ተከተል ያካተተ ይሆናል፡

  • መልዕክተኛ፣ መምህር፣ ተምሳሌት፣ እና የነብያት ሁሉ ቁንጮ
  • በቀጥታ የተነገረ የአላህ ቃል
  • ለሰው ዘር ፍጹም አርአያ (ተምሳሌት) የሆኑት የመሐመድ የቃልና የሥራ ምሳሌዎች፤ እነርሱም የሙስሊሙን ሕይወትና አምልኮ ለመቆጣጠር የሚውሉ ናቸው፡፡
  • የመስጊዶች ተግባራትና ሚናዎች የሚገኙት በእስላማዊ በሆነ ወይም ባልሆነ ስፍራ በመሆኑ ላይ ይወሰናል። እስላማዊ ባልሆኑ ስፍራዎች የጀሐድ ድንጋጌ እና የተቂያ ስልት በመስጊድ አማካይነት ተግባራዊ ወደ መሆን ይመጣሉ።
  • መሐመድ፤ አላህ፤   ቁርኣን፤ ሱና እና የሸሪዓ ሕግ አካላት ሕግ አስፈጻሚዎች (ኡላማ)
  • አብሮ የሚሆን የሌለው አንድ አምላክ (ሱረቱ 112)
  • ሙሉ በሙሉ በቁርኣን፣ በሱና በሐዲስ ላይ የተመሠረተ ሲሆን ከአለባበስ ስርዓት አንስቶ ጋብቻን፣ ውርስን፣ እንዲሁም እንደ አጥፍቶ መጥፋትና የቦምብ ጥቃት ያሉ ወቅታዊ ጉዳዮችን ይዳስሳል
  • ሕግ አስፈጻሚዎች (ኡላማ) ዕውቀት ያላቸውና የሸሪዓ ሕግ በወቅታዊው ሁኔታና ጉዳይ ላይ እንዴት እንደሚውል የመተርጎም ሥልጣን ያላቸው ናቸው። ሕጎቹ በአዋጅ ወይም ፋትዋ መልክ የሚወጡ ሲሆኑ በሁሉም ስፍራ ባሉ ሙስሊሞች ላይ ተፈጻሚነት ይኖራቸዋል።

ስለዚህም መስጊድ በተቀዳሚነት ከቁርኣን እና ከሱና የተውጣጣው የእስላማዊ ሕግ (ሸሪዓ) አዋጅ የሚሰራጭበትና የሚተገበርበት ማዕከላዊ ቦታ ነው።

 

የመስጊዶች ተግባርና ሚና

ሁሉም መስጊዶች በመሐመድ ትዕዛዝ ስር በመዲና መጀመሪያ የተገነባውን መስጊድ እንደ ምሳሌ በማየት የተገነቡ ናቸው። የመጀመሪያው መስጊድ በመጀመሪያው የሙስሊም ማኅበረሰብ መካከል የነበረውን ሚና እና አገዛዝ ሳናውቅ የመስጊድ ተግባራት ምን እንደሆኑ ለመረዳት ያስቸግራል።

መሐመድ አሁን ሂጅራ ተብሎ በሚታወቀውና በእስልምና ውስጥ ታላቅ መንፈሳዊና ፖለቲካዊ ጠቀሜታ ባለው ከመካ ወደ መዲና ባደረገውስደት ጉዞ ወቅት ከመዲና ነዋሪዎች አብዛኞቹ ሙስሊሞች አልነበሩም። ብዙ አይሁዳውያን፣ ሃይማኖታቸውን የለወጡ አረቦች፣ እና ክርስቲያኖች እንዲሁም ብዙምንም እምነት የሌላቸው” አረቦች በመዲና ከተማ ውስጥ ይገኙ ነበር።

አስፈላጊነቱ አንገብጋቢ እንደሆነ ለማሳየት ሲል መሐመድ መዲና እንደ ደረሰ ለራሱ እንኳ ቤት ሳይሠራ መስጊድ ገነባ።

ሸሪዓ በመዲና በተገለጠ ጊዜ መስጊድ ሃይማኖታዊ ትምህርቶች የሚሰጡበት ብቻ ሳይሆን ሌሎች አያሌ ተግባራት የሚከናወኑበት ስፍራ መሆኑን ገለፀ፡፡ ስለዚህም መስጊድ፡

1.     እስላማዊ መሠረተ-እምነት የሚነገርበትና አጋሮች በመሐመድ ስር እያደጉ የሚማሩበት የመጀመሪያው እስላማዊ ትምህርት ቤት (መድረሳ) ነበረ።

2.     መንፈሳዊ ግሳፄዎች የሚተላለፉበት እና እስላማዊ ያልሆነን ተፅዕኖ በጀሐድ አማካይነት የሚቃወሙበት ማደፋፈሪያ የሚነገርበት መድረክ ሆኖ አገለገለ።

3.     የጀሐድ ዘመቻዎች በመሐመድም ሆነ ከሞቱ በኋላ በተከታዮቹ ለውይይት የሚቀርቡት፣ ስልት የሚነደፍላቸው እና የጦር አዛዦች የሚመደቡላቸው በመስጊድ ነው።

4.     በመሐመድም ሆነ በተከታዮቹ እስላማዊ ተወካዮች የሚሾሙበትና የሚላኩበት ስፍራ መስጊድ ነው።

5.     የጎሳ ሹሞችና ተወካዮች ይሾሙበታል።

6.     የአረብ ነገዶች ለመሐመድ እና ለእስላም ያላቸውን የታማኝነት ቃለ መሐላ የሚያቀርቡት በዚሁ ስፍራ ነው።

7.     የእስላማዊው አገዛዝ ጉዳዮች የሚከናወኑበትና እንዲህ ባለው ጊዜ የመጀመሪያው የእስልምና አገዛዝ ዋና ጽሕፈት ቤት እንዲሁም መስጊድ ሆኖ ያገለገለ ነው።

8.     ጀሀድ የሚታወጀውና ሙስሊም ጦር ሰራዊቶች ዓለምን ድል ለመንሳት የሚሰማሩት ከመስጊድ ነው።

9.     የመሐመድ አጋሮች በሠሯቸው ሥራዎች ዕውቅና እና ማዕረግ የሚያገኙትና የእስላምን ጠላቶች ለማስወገድና ተቃውሞን ሁሉ ፀጥ ለማሰኘት የሚበረታቱት በዚሁ ስፍራ ነው።

10.  መሐመድ እንዲሁም የእርሱን ቦታ ተክተው የሠሩ ተከታዮቹ አቡ በከር፣ ኡመር፣ ኡስማን እንዲሁም አሊ ለተለያዩ ክልሎች ዳኛዎችን፣ ለጦር ሰራዊታቸው አዛዦችን የሚሾሙበትና ለጀሀድ የተዘጋጀው ጦር ወደ ዘመቻ የሚሰናበተው እንዲሁም ከፍተኛው ደረጃ ያላቸው ባለሥልጣናት እና ቀረጥ ሰብሳቢዎች የሚላኩት ከዚሁ ከመስጊድ ነበር።

11.  ኮንትራቶችና ልዩ ልዩ ስምምነቶችም ፈቃድ የሚያገኙት በዚሁ ስፍራ ነው።

12.  እስላማዊው ሸሪዓ የሚነገረውና መፍታትና ማሰር፣ መፍቀድና መከልከል የሚታወጀው በመስጊድ ነው።

13.  በዚሁ ስፍራ የሙስሊሞች የበላይነትና ሙስሊም ያልሆኑ ዜጎች የበታችነት ይታወጃል።

14.  ወንድ በሴት ላይ ያለው የበላይነትና ሰዎች እኩል አለመሆናቸው ይሰበክበታል።

15.  ከሁሉም በላይ የሚያሳዝው ጉዳይ መሐመድን የተቃወሙ ወይም እርሱን በመልካም ሁኔታ ያላነጋገሩ ሰዎች የሞት  ፍርድ የሚፈረድባቸውና ቀናዒዎቹ ወታደሮች ቅጣቱን ለመፈጸም የሚንቀሳቀሱት ከመስጊድ ነው።

16.  የመሐመድን ጠላቶች ያጠፉ ወንጀለኞች በነብያቸው ከፍ ከፍ የሚደረጉትና የሚወደሱትም በመስጊድ ውስጥ ነው። የሚከተሉት ዓይነተኛ ማሳያዎች ይሆኑናል፦

) አስማ ቢንት ማርዋን ልጇን ጡት እያጠባች በነበረችበት ወቅት ኦመየር ቢን አል ካህቴም በጭካኔ የገደላት

) ሱፍያን ቢን ካሊድን አብደላ ቢን አኒስ የገደለው፤

) አይሁዳዊውን አቡ አፋቅን ሳሌም ቢን አማየር የገደለው፤

) ኢብን አቢ ሐቂቅ የተባለውን አይሁዳዊ አብደላ ቢን አቲቅ የገደለው፤

) ናዴር ኢብን ሀሪትን አሊ ቢን አቡ ጧሊብ የገደለው።

17.  በመጨረሻም የሙስሊም ሰራዊቶች ለማጥቃትና የዓለምን ገፅታ ለመቀየር የሚነሱት ከመስጊድ ነበር።

ዘመናዊው መስጊድ እና ሚናዎቹ

ሁሉም ሙስሊሞች የመታዘዝ እንዲሁም በቃል እና በሥራ መሐመድን የመምሰል ግዴታ አለባቸው።

መሐመድ በተልዕኮ ካሳለፋቸው 23 ዓመታት ውስጥ አሥራ ሶስቱን ያሳለፈው በመካ ነው። በእነኚህ 13 ዓመታት ውስጥ መስጊድ ካለመገንባቱም በላይ መስጊዶች ስለሚጫወቱት ሚና አንዳችም አልተናገረም።

በቁርአኑ የመካን ክፍል ውስጥ ስለ ፀሎት የተነሳ ቢሆንም ዛሬ በመካ እንደምናውቀው ያለ እስላማዊ ፀሎት በዚያ ጊዜ አይታወቅም ነበር። ይህ ሁሉ የመጣው በመዲናው ክፍል ወቅት ነው። 

ይህ ሁኔታ ጥያቄዎችን እንድንጠይቅ ያስገድደናል፤ በእስልምና የመጀመሪያዎቹ 13 ዓመታት ውስጥ ሙስሊሙ ማኅበረሰብ የሚፀልየው የት እና እንዴት ነበር?

ሙስሊሞች እስልምና በመካ በተጀመረበት ወቅት ስለ ነበረው የመስጊድ ሁኔታ አያውቁም፤ ካወቁም ጉዳዩ እጅግ ጥብቅ ምስጢር ስለ ሆነ የሚያውቁት ጥቂት ነገር ብቻ ይሆናል።

ሙስሊም ምሁራን በእስልምና ጅማሬ ወቅት መስጊድ ያልነበረበትን ምክንያት ለመግለፅ ሲሞክሩ፣ ካዓባ መስጊድ እንደ ነበረ ነገር ግን በወቅቱ በእምነት የለሾቹ አረቦች ቁጥጥር ስር ስለ ነበረ መሐመድ እና አጋሮቹ ስፍራው በውስጡ እና በዙሪያው ከነበሩ ጣዖታት ፀድቶና ነፅቶ እስከሚጨርስ ድረስ ሊፀልዩበት እንዳልቻሉ ይናገራሉ። በሰዓቱ እምነት የለሾቹን ሰዎች ለማስገዛት ፖለቲካዊ አቅም እንዲሁም ወታደራዊ ኃይል አልነበረውም። ስለዚህ በእነርሱ አመለካከት መሐመድ በመዲና የገጠመው መገለጥ፣ የመጀመሪያውን መስጊድ መገንባቱ፣ በወታደራዊ አቅም አማካይነት ፖለቲካዊ ኃይል ማግኘቱ እና ከዚያ በመቀጠል መካን በቁጥጥር ስር ማዋሉ እንደየቅደም ተከተላቸው መምጣታቸው ግዴታ ነበር።

በመዲና የተገነባው የመጀመሪያው መስጊድ አንደኛና ቀዳሚ የፖለቲካ ቢሮ እንደ ነበረ ግልፅ ነው፤ የተጣመረው ተግባሩ ማኅበራዊ-ሃይማኖታዊና፤ ማኅበራዊ-ፖለቲካዊ መንገድ መክፈቻ ነበረ።

በዚህ መሠረትና መሐመድ የመጀመሪያውን መስጊዱን ሲገነባ ካስቀመጠው አካሄድ የተነሳ ዘመናዊዎቹ መስጊዶችም በመዲና የነበረውን የመጀመሪያ መስጊድ ፈለግ መከተል ነበረባቸው።

የአዘጋጁ ማሳሰቢያ

ከዚህ በላይ የተዘረዘሩት የመስጊዶች የደረጃ ልዩነቶች፣ ማለትም በአንድ መስጊድ የሚፀለየው ፀሎት በሌላ መስጊድ ከሚደረገው ፀሎት ጋር የሚኖረው የተቀባይነት መበላለጥ አስገራሚ ነው፡፡ ከእስልምና ጅማሬ ጀምሮ የመስጊዶች ሚናና በመስጊዶች ውስጥ የሚከናወኑት አስራ ሰባት የሚሆኑት ዝርዝር ተግባራትም ሌሎቹ አስገራሚዎች ነገሮች ናቸው፡፡

መስጊድ ከክርስትያኖች ቤተ ክርስትያን ጋር ተመሳሳይ አገልግሎት የነበረውና ያለው ቢመስልም እንኳን አሁን በቀረበልን ጥናት እንደምናየው ከሆነ በጣም የተለየ ነው፡፡ ከዚህ መሰረታዊ እውቀት የተነሳ አንድ ሰው የሚደርስበት የመጀመሪያ ጥያቄ መስጊዶች ለዘላለማዊዋ የሰው ልጆች ነፍስ የሚሰጡት ጠቀሜታ ምንድነው? የሚል ይሆናል፡፡

የክርስትያን ቤተ ክርስትያኖች ከመጀመሪያ ጀምሮ የተመሰረቱበት ትልቁ ዋና ዓላማ ክቡር የሆነችው ነፍስ፡

አንደኛ: ከአምላኳ ጋር ለመታረቅ የምትችልበትን አገልግሎት ማከናወን፤

ሁለተኛ፡ በመንፈሳዊ እውቀት እንድትበለፅግና በአምላኳ ፈቃድ እንድትመራ፡፡

ሦስተኛ፡ የአምላኳን ደግነትና ፍቅር በችግርም ውስጥ በማለፍ ለሌሎች ማዳረስ እንድትችል መርዳት ብቻ ነው፡፡ ከነዚህ ውጭ ሌላ ዓላማ የላቸውም እነዚህን ዓላማዎች ማከናወን ካልቻሉ ደግሞ በእግዚአብሔር ፊት ቤተክርስትያን ተብለው መጠራት አይችሉም መስፈርቱን አያሟሉምና፡፡

በየትኛውም ቦታና በየትኛውም ዘመን የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ስለ ነፍሳቸውና ዘለዓለምን የት እንደሚያሳልፉት በጥልቅ ማሰብ ይገባቸዋል፡፡ ለዘላለማዊዋ ነፍሳቸው የሚጠቅም፤ የሕይወትን ትርጉም እንዲሁም ዓላማ የሚሰጣቸውን እውነታ መቀበል አለባቸው፡፡ ለዚህ ነው የክርስትና መልእክት በጣም ጠቃሚ የሚሆነው፡፡ የሰዎች ነፍስ ከአምላኳ ጋር የምትታረቅበትን፣ እዚህ ምድር ላይ ሰላምና እርካታ ሊኖራት የሚችልበትን መንገድ በግልፅ የሚያስቀምጠውን መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ያስፈልጋል፡፡

የዚህ ገፅ አንባቢዎች ሆይ መጽሐፍ ቅዱስን አግኙና ከዮሐንስ ወንጌል ጀምሮ በዝግታ አንብቡ እግዚአብሔርም በቃሉ የሚናገራችሁን ነገር አስተውሉ፤ ክቡር ነፍሳችሁ የምትድንበትን የነፃ መልእክት ታገኛላችሁና፡፡ እግዚአብሔር ይርዳችሁ፡፡

 

 

ወደ ማውጫው መመለሻ

ለእስልምና መልስ አማርኛ  ዋናው ገጽ