መስጊድ እና በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለው ሚና

በባልታዛር እና አብደናጎ

ክፍል አራት

ጅሐድ እንደ አንቀሳቃሽ መርኅ

በሕንድ ሀገር ካሉት ቀዳሚ እስላማዊ ምሁሮች አንዱና ዘመናዊው አቡ አላ ማውዱዲ በአፕሪል 13/1939 በኢቅባል ቀን የሚከተለውን ንግግር ያደረገ ሲሆን በቀጣይነት ጀሐድ ኢን ዘ ኮዝ ኦቭ አላህ (አሁን በቤይሩት በሚገኘው በሆሊ ቁርአን ፐብሊሺንግ ሀውስ ታትሟል።) በተሰኘው መጽሐፉ ውስጥም ደግሞታል፦

እስልምና ልክ እንደማንኛውም የዘንባባ ዛፍ ቢሆን እና ሙስሊሞችም ልክ እንደ ሌላው የዓለም ሕዝብ ያሉ ሕዝቦች ቢሆኑ ኖሮ፣ እስላማዊ ጀሀድ መታደሏን እና ጀሀድ የአምልኮ ሁሉ ቁንጮ እና የዘውዷ ጌጥ የሆነችበትን ልዩነት ብታጣ ወንጀል ባልሆነም ነበር። ነገር ግን፤ እውነታው እስላም ልክ እንደ ማንኛውም የዘንባባ ዛፍ አለመሆኗና ሙስሊሞችም በምድር ላይ እንዳሉት እንደ የትኛውም ዓይነት ሕዝቦች ያለመሆናቸው ነው።

በመሠረቱ እስልምና የመላውን ዓለም ማኅበራዊ አስተዳደር ለመለወጥና ለእርሱ እሴትና እምነት ስምም እንዲሆን ለመገንባት የተነሳ አብዮታዊ ፍልስፍናና አብዮታዊ መርሀ ግብር (አጀንዳ) ነው።

“ሙስሊም” አብዮታዊ መርሀ ግብሩን ለማስፈፀም የዚያ በእስልምና የተዘጋጀ ዓለም-አቀፍ አብዮታዊ ንቅናቄ ፓርቲ ስያሜ ነው። ጀሀድ ደግሞ እስላማዊው ፓርቲ ይህንን ግብ ለማሳካት ወደ ጨዋታው የሚያመጣው የዚያ አብዮታዊ ትግል አካል እና የመጨረሻ ጥረት ነው።

እስልምና በየትኛውም የምድር ገፅ ላይ ያሉና የእስላምን መርሀ ግብር እና ፍልስፍና የሚቃወሙትን ሀገራት እና መንግስታት ሁሉ የትኛውንም ሀገር ወይም ሕዝብ ያስተዳድሩ ሊያጠፋቸው ሲናፍቅ ኖሯል። የእስልምና ዓላማ - የትኛውም ሕዝብ እስላማዊ  ቅጣትን መቀበል ቢኖርበት እና ምናባዊውን እስላማዊ አገዛዝ ለማቆም ሲባል የየትኛውም ሕዝብ አገዛዝ ተገርስሶ - በራሱ እስልምናዊ ፍልስፍና እና መርሀ ግብር ላይ የተመሠረተ አገዛዝን ማቋቋም ነው።

ማንም ቢሆን ራሱን በሰዎች ላይ ሹሞ በራሱ ምርጫና ሥልጣን ስርዓት እና ሕገ-ደንብ እንዲፀናለት ሊያደርግ አይችልም። የሰው ልጅ ትዕዛዛትን እና ሕገ ደንቦችን ለማውጣት በራሱ ላይ ያለውን ሥልጣን አምነን የተቀበልንለት እንደ ሆነ የእግዚአብሔርን ኃይል እና ሥልጣን እንደሚጋራ እየተስማማን ነው ማለት ነው። በዚህ ዓለም የሚታየው የክፋቱ ሁሉ ስር ደግሞ ይኼ ነው።

እስልምና እንዲያው የሃይማኖት እወጃ ወይም ለተወሰኑ የአምልኮ ዘይቤዎች የተሰጠ የወል ስም ሳይሆን፣ በዓለም ዙሪያ ያሉትን አምባገነናዊና የክፋት ዘይቤዎች ለማስወገድ የታለመና ለሰው ዘር ጠቃሚ እንደ ሆነ ለሚያምንበት ተሓድሶ የራሱን መርሀ ግብር ተግባራዊ የሚያደርግ አጠቃላይ መስተጋብር ነው።

ከዚህ ገለፃ በመነሳት እስላማዊ ጀሀድ እስላማዊ ያልሆነውን አስተዳደራዊ ስርዓት አስወግዶ በምትኩ የእስላማዊ አገዛዝን መፍጠር ዓላማው ያደረገ መሆኑ ሳይታያችሁ አይቀርም። እስልምና ይህንን አብዮት በአንድ ሀገር ወይም በጥቂት ሀገራት ብቻ የመገደብ ሐሳብ የለውም፤ የእስልምና ዓላማ ዓለም-አቀፍ አብዮት ማስነሳት ነው።

እስላማዊ ጀሀድ በእምነት ፍልስፍና፣ የአምልኮ ስነ-ስርአቶች እንዲሁም በሰዎች ባህል ውስጥ የመግባቱ መሻት የለውም። ሆኖም፣ እስላማዊ ጀሀድ እስልምና ክፉ እንደሆነ ለሚያስቡ ስርዓቶች ሁሉ ማኅበራዊ ጉዳዮችን ለማስተዳደር መብት እንዳላቸው እውቅና አይሰጥም። በተጨማሪም፣ ከእስልምና አመለካከት አንፃር የሕዝብን ፍላጎት ስለሚፃረሩ እንዲህ ያሉትን ልምምዶች በማድረግ የመቀጠል ልምድ እንዲኖራቸው አይፈቅድም።

ጀሀድ በእስልምና ውስጥ ብዙ ገፅታ ስላለው፣ የቃሉ ፍቺ ሰራዊቶችን ተጠቅሞ ጦርነት በማወጅ ብቻ አይወሰንም። የትጥቅ ትግሉ ራሱ ሌሎች ድጋፎችን ይፈልጋል። በሸሪዓ ከተቀመጡት ብዙ የጀሀድ ዓይነቶችን እንመልከት፦

ጀሀድ ቢ አል ሊሳን፦ በምላስ/ በስብከት/ በእወጃ/ በክርክር እና በንግግር የሚገለጥ ጀሀድ።

ጀሀድ ቢ አል ቀለም፦ በእስክሪፕቶ አማካይነት፣ በጽሑፍ/በሕትመት/ በመገናኛ ብዙሀን የሚደረግ ጀሀድ።

ጀሀድ ቢል ሒጅራ፦ ከሀገር በመውጣት ወይም ከከተማ ወደ ከተማ በመሰደድ የሚደረግ ጀሀድ።

ጀሀድ ቢ አል ማል፦ በገንዘብ እንቅስቃሴዎች የሚደረግ ጀሀድ።

ጀሀድ ቢ አል ናፍስ፦ በሕይወት ላይ የሚደረግ ጀሀድ።

ጀሀድ አ ናፍስ፦ በአንድ ሰው ማንነት፣ በአጥፍቶ ጠፊነት ጊዜ እንደሚደረገው ራስን በመሰዋት የሚሆነ ጀሀድ።

እነዚህ እያንዳንዳቸው ደግሞ ልዩ ልዩ ክፍሎች አሏቸው። ነገር ግን አሁን የእኛ ዋና አጀንዳ ወደ ሆነውና በምዕራቡ ዓለም ውስጥ አንገብጋቢነት ወዳለው ጉዳይ እንዙር።

ሂጅራ (መሐመድ እና ተከታዮቹ ከመካ ወደ መዲና ያደረጉት ስደት)

በዚህኛው ርዕስ የምናተኩረው በማኅበራዊው ጀሀድ፣ በሂጅራ የስደት ጉዞ ላይ ይሆናል። ይህ መሐመድ ከመካ ወደ መዲና ያደረገው ስደት ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ጎኖች ስላሉት ጠቃሚ ነው።

ለእስልምና እንዲሁም በሌሎች ሀገራት የሚገኙ ሙስሊሞች ድል ለማስገኘት ሲባል የሚደረግ ስደት ለተለያዩ ዓይነት ጀሀዶች መንገድ ስለሚከፍት በእስልምና ውስጥ እጅግ ተቀባይነት ያለው ተግባር ነው። ይህም አቋም ተደርጎ የተወሰደው መሐመድ የሚከተለውን ስለ ተናገረ ነው፤

አላህ እኔን ያዘዘኝን እነዚህን አምስቱን፦ መሰብሰብ፣ ማድመጥ፣ መታዘዝ፣ ሂጅራና ጀሀድ እናንተም እንድታደርጉ አዝዛችኋለሁ። (ተፍሲር አል ቁርአን፣ ኢብን ካቲር፤ ዳር አል አህያ ቱራት አል አራቢ፣ ጥራዝ 1 ገፅ 103። ማስናድ አል አንሳር፣ ኢማም አሕመድ፤ ዳር አል አህያ ቱራት አል አራቢ፣ ጥራዝ 6 ገፅ 471። ሱናን ቲርምዝ፣ ዳር አል ኪታብ፣ 1994፣ ጥራዝ 8 ገፅ 35።)

ስለዚህ ሂጅራን እንደ መዘጋጃ መንገድ አድርጎ ከማሳየቱም በላይ ከጀሀድ ጋር አጣምሮታል። መሐመድ አክሎም ጀሀድ ጠላት በሚዋጋ ጊዜ ወይም እስልምናን መግፋቱን እስከ ቀጠለ ጊዜ እንደሚዘልቅ ተናግሯል። ካፊሮች ወይም ከሀዲዎች እስካሉ ድረስ ሂጅራ ግዴታ ሆኖ ይቀጥላል።

ከመጽሐፉ ባለቤቶች የኾኑ ጭፍሮችም አሉ፡- «በነዚያ በአመኑት ላይ በተወረደው (ቁርአን) በቀኑ መጀመሪያ ላይ አመኑበት። በመጨረሻውም ካዱት። እነርሱ ሊመለሱ ይከጀላልና።» (ቁርአን 8.72)

እነዚያም በኋላ ያመኑና የተሰደዱ፣ ከእናንተም ጋር ኾነው የታገሉ እነዚያ ከናንተው ናቸው። የዝምድናዎች ባለቤቶችም በአላህ መጽሐፍ ከፊሎቻቸው በከፊሉ (መውረስ) የተገቡ ናቸው። አላህ በነገሩ ሁሉ ዐዋቂ ነው። (ቁርአን 8.75)

እነዚያ ያመኑትና እነዚያም (ከአገራቸው) የተሰደዱት በአላህም መንገድ ላይ የተጋደሉት እነዚያ የአላህን እዝነት ይከጅላሉ። አላህም እጅግ መሓሪ አዛኝ ነው። (ቁርአን 2.218)

እነዚያ ያመኑት፣ ከአገራቸውም የተሰደዱት፣ በገንዘቦቻቸውና በነፍሶቻቸውም በአላህ መንገድ ላይ የታገሉት አላህ ዘንድ በደረጃ በጣም የላቁ ናቸው። እነዚያም እነሱ ፍላጎታቸውን ያገኙ ናቸው። (ቁርአን 9.20)

ስለዚህ ስደት ከጀሀድ ይቀድማል፤ ሁለቱ ደግሞ በማይነጣጠል ሁኔታ የተጣመሩ ናቸው።

የጅምላ ስደት ወይም በአንድ ስፍራ ተከማችቶ መኖር በሚያቀርባቸው ልዩ ልዩ መሻቶች እንዲሁም ላለመቀላቀልና ላለመደባለቅ እርምጃ በመውሰዳቸው ምክንያት፣ እስልምና በከሀዲዎች ሀገር እንዲስተዋል አስገዳጅ ያደርገዋል። እንደ ማዱዲ አገላለፅ ይህ አካሄድ በቀጣይነት የዚያን ኅብረተሰብ ማኅበራዊ-ፖለቲካዊ መዋቅር ለመለወጥ፣ ለማፈራረስና በመጨረሻም ለመገርሰስ ዕድል ይሰጣል።

በሌላ አገላለጽ፣ ያለ ስደት የእስልምናን ሃይማኖት ማጠናከር የሚቻል አይደለም። ያለ ሙስሊሞች እገዛና የቁጥራቸው ብዛት ካልጨመረ በከሀዲዎች ሀገር የእስልምናን ምንነት በግልፅ ማሳየት አይቻልም።

ይህ በቁጥር መጨመር ግዴታ ከአንዱ ሀገር ወደ ሌላኛው በመሰደድ ብቻ መገኘት የለበትም፤ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ በአንድ ሀገር ውስጥ ከክፍለ ሀገር ወደ ክፍለ ሀገር በመዘዋወር ሊደረግ ይችላል። ስለዚህ የሚጨመሩት ሰዎች ቁጥር ጥንካሬን የሚያስገኝ ከሆነ፣ ካፊሮች የሚሸነፉ ከሆነ ወይም ቢያንስ ቢያንስ እስልምና ከሃይማኖትና ከፖለቲካ አንፃር ጥቅም የሚያገኝ እስከሆነ ድረስ ስደቱ ከጅማ ወደ ማርቆስ ወይም ከባሌ ጎባ ወደ ጎንደር ሊሆን ይችላል።

ስለዚህ በአንድ የተወሰነ ቦታ ሊገነባ የታሰበው ታላቁ መስጊድ አስፈላጊ ላይሆን ይችላል፤ ነገር ግን እንዲህ ያሉ ህንጻዎች ከተጨባጭ ጥቅማቸው ወይም አስፈላጊነታቸው በላይ የሚያስተላልፉት መልዕክት አለ።

ይህም በልዩ ልዩ አዋጆች፣ ፋትዋዎች እና አያሌ ሙስሊም ምሁራን ባደረጓቸው ንግግሮች አፅንኦት አግኝቷል።

ሼክ ቃርዳዊ በየካቲት 27 ባቀረበው ፋትዋ የሚከተለውን ጠይቋል፦

“በሙስሊም ተዋረዶች መካከል አሉታዊ አመለካከት ቢኖርም እስልምና በመጨረሻ አሸንፎ መላውን ዓለም ይገዛል። ይህ የመሆኑ አንደኛው ምልክት ሮም መሸነፏ፣ አውሮፓ በእኛ እጅ መውደቋ፣ ክርስቲያኖች መሸነፋቸው እና የሙስሊሞች ቁጥር እጅግ ከመብዛቱ የተነሳ የአውሮፓን አህጉር በሙሉ የሚቆጣጠር ኃይል መሆኑ ነው።” www.islamonline.net/Fatwa/Arabic/FatwDisplay.asp

‘ለዘብተኛ' ተብሎ የሚታወቀው የቱርክ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስቴር ናጅመዲን ኢርባካን ለጀርመን ጋዜጠኞች መልስ በሰጠበት ጊዜ የተናገረው የሚከተለውን ነው፦

“ስለ እኛ ሙስሊም ቱርኮች የምታስቡት ወደዚህ የምንመጣው ለመቀጠር እና የእናንተን ሽርፍራፊ ሳንቲም ለመልቀም እንደ ሆነ ነው። እንደዚያ ግን አይደለም። እኛ ወደዚህ የምንመጣው ሀገራችሁን በቁጥጥር ስር ለማዋልና እዚህ ስር በመስደድ ተገቢ ነው ብለን የምናምንበትን ነገር ለመገንባት ነው። ያንንም ሁሉ የምናደርገው በገዛ ራሳችሁ ፈቃድ እና በሕጋችሁ መሠረት ነው።” www.elaph.com/ElaphWriter/2004/11/23948.htm

አብዛኞቹ በኢንግላንድ የሚገኙ መጽሔቶችም የሚያስተጋቡት ይህንኑ ነጥብ ነው። ለምሳሌ በክሁራም ሙራድ የሚዘጋጀው ኢስላሚክ ሙቭመንት ኢን ዘ ዌስት ስለዚህ ጉዳይ፡

 “እስላማዊ ንቅናቄ ምንድን ነው?” በሚለው ጥያቄ አማካይነት ያወሳል። የሚገልፀውም እንደሚከተለው ነው፦ “. . . በቁርአን እና በሱና ላይ ተመሥርቶ አሁን ያለውን ኅብረተሰብ - በተለይም ማኅበራዊ-ፖለቲካዊ ምህዳሩን - የሕይወት መመሪያና የበላይና ገዢ ወደ ሆነው እስልምና መቀየር ነው።”

ሙራድ አያይዞ እንዲህ ይላል፦

“. . . ነገር ግን፣ ዓለም-አቀፍ አብዮትና አዲስን ዘመን ማስተዋወቅን በረዥሙና በጥልቀቱ ግብ አድርጎ የተጀመረው እንቅስቃሴ እንዲያው ወደ ተራ ሃይማኖታዊና ትምህርታዊ ጉድለቶችን ወደ መሙላት ከተቀየረ እጅግ የሚያሳዝን ነገር ነው። እነዚህ ጉድለቶች ሁል ጊዜም ቢሆን፣ በተለያየ መጠንና በተለያዩ ሰዎች መሞላታቸው የማይቀር ነው። ማኅበረሰባዊ ጉድለቶችን ለመሙላት ሲባል ብቻ እስላማዊ ንቅናቄን ማነሳሳቱ ከንቱ ይሆናል።”

“. . . ምንም ያህል ለማሳካት የሚያዳግት ቢመስልም በምዕራቡ ዓለም የሚደረገው ንቅናቄ በምዕራባውያኑ ማኅበረሰብ ዘንድ ፍፁም ለውጥና የእስልምና የበላይነትን የማስፋፋቱ ፅንሰ-ሀሳብ እንደ መጨረሻ ግብ ተቆጥሮ ሊበረታታና ሊጎላ እንዲሁም በቅደም ተከተላችን ውስጥ ቅድሚያ ሊመጣ ይገባል።”

መስጊዶችና አጠቃላይ ተግባራቶቻቸው የማኅበረሰቡ ማዕከል እንደመሆናቸው የመከሩበት ነገር ሁሉ እውን የሚሆነው በአመራሮቻቸው አማካይነትና በእነርሱ አዎንታዊ ፈቃድ ነው።

የቁርአን ሕግጋት ተቀባይነት ላለው የሌላ እምነት ተከታዮች አኗኗር (ተቂያ)

ለ‘ሌሎች' በተለይም ለክርስቲያኖችና ለአይሁዶች ግልፅ ጭካኔ፣ ጨቋኝነት እና ትግዕስት አልባነት በሚታይበት ቁርአን ውስጥ እስላማዊው ማኅበረሰብ የፀረ-ሴማውያን እና የፀረ-ክርስቲያን እስላማዊ አስተምህሯቸውን ክብደትና ተአማኒነት መተው የማስመሰል፣ የማቃለል እና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም መካድ የሚቻልባቸውን ደንቦች አስቀምጦላቸዋል።

ሙስሊሞች - በሃይማኖታዊ ሁኔታቸው የተቀደሱም ይሁኑ ቁሳዊ፣ ዓለማዊም ሆኑ ሕዝባዊ - ሙስሊም ካልሆኑ ሰዎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት የሚገዛው “ተቂያ” የተባለው ሕጋቸው ነው። በመሠረቱ በእስልምና ውስጥ የተቀደሰ ወይም ዓለማዊ የሚባል ነገር እንደሌለ ተመልክተናል። 

ተቂያ

ተቂያ “ጥንቃቄ፣ ፍርሀት ወይም ማስመሰል” ተብሎ ይተረጎማል። ሙስሊም ባልሆነ ወይም ሙስሊም በሆነው ኅብረተሰብ መካከልም እንኳ ጥቃትን፣ አደጋን ወይም ማንኛውንም ዓይነት ማስገደድ የሚያስከትል ሁኔታ ውስጥ ከሆኑ እንደ አስፈላጊነቱ እምነትን ፈፅሞ መካድን ጨምሮ ማንኛውንም ወይም ሁሉንም ሃይማኖታዊ ግዴታዎች መተውን ይፈቅዳል።

ለተቂያ ቁርአን ያስቀመጠው ሕግ በቁርአን 16.106 ላይ ይገኛል፦

“ከእምነቱ በኋላ በአላህ የካደ ሰው (ብርቱ ቅጣት አልለው)። ልቡ በእምነት የረጋ ኾኖ (በክህደት ቃል በመናገር) የተገደደ ሰው ብቻ ሲቀር። ግን ልባቸውን በክሕደት የከፈቱ ሰዎች በነሱ ላይ ከአላህ ቁጣ አለባቸው። ለእነሱም ታላቅ ቅጣት አልላቸው።”

ይህ ጥቅስ ለመሐመድ የወረደው ከተከታዮቹ አንዱ የነበረው አማር ቢን ያሲር በመካ በነበሩበት ጊዜ የቆሬይሽን ጣኦቶች ተገድዶ ባመለከበት ወቅት መሐመድ ልቡ ሰላም እንዲያገኝ ባነጋገረው ወቅት ነው። እንደ ቁርአን ተርጓሚዎች አባባል ይህ ጥቅስ የተገለጠው የያሲርን ህሊና ለማረጋጋትና ለማሳረፍ ሲሆን ለሁሉም ሙስሊሞች ተግባራዊ መሆን ይችላል። ቁርአን 3.28 እንዲሁ ተመልከቱ፦

“ምእምናን ከሐዲዎችን ከምእምናን ሌላ ረዳቶች አድርገው አይያዙ። ይኼንንም የሚሠራ ሰው ከአላህ (ሃይማኖት) በምንም ውስጥ አይደለም። ከእነርሱ መጠበቅን ብትጠበቁ እንጂ። አላህም ነፍሱን (ቁጣውን) ያስጠነቅቃችኋል። መመለሻም ወደ አላህ ብቻ ነው።”

‘ከእነርሱ መጠበቅን ብትጠበቁ' በሚለው ሀረግ ውስጥ ‘ብትጠበቁ' ለሚለው ቃል የተጠቀመው ተቂያን ነው። አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ሁሉ እምነትን መካድ ከመፍቀዱም ባሻገር ከላይ በተጠቀሰው ቁርአን 3.28 ተመሥርተው ቁርኣናዊ ሕግጋቱ የተፈቀደ ማስተባበያና ግዴታ አድርገው ያስቀምጡታል።

አንድ ሰው በውስጡ ምንም ዓይነት ተቃራኒ ነገር ቢያስብና ቢያምን፤ ለምሳሌ፦ ፍቅርን አሳይቶ በልብ ግን መጥላት፣ ታማኝነትን ማሳየት ነገር ግን በውስጥ ክህደትን ማሸመቅ፤  ይህ ደንብ በ‘አስገዳጅ ሁኔታ' ውስጥ በቃላት እና በተግባር የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ተቀባይነት ያላቸው ያደርጋቸዋል።

ስለዚህ ለምሳሌ እጅግ ታዋቂ ከሆኑት እስላማዊ ምሁራን እና ቁርኣን ተርጓሚዎች አንዱ የሆነው አል ዛማከሻሪ እንዲያ እንዲያደርግ ያስገደዱት መነሾዎች እስከሚወገዱ ወይም እስላማዊው ማኅበረሰብ ግልፅ ጥቃትን ለመፈጸም የሚያስችል ዓለማዊ ብቃት እስከሚኖረው ድረስ እንዴት ላይ ላዩን ታማኝነትና ወዳጅነትን አሳይቶ ልብ ግን በጥላቻና በክህደት የተሞላ ሊሆን እንደሚችል ይገልጻል።

አንድ ሙስሊም በመካከላቸው የሚኖርባቸውን ሙስሊም ያልሆኑ ሰዎች እጅግ ከበዛ ኃይላቸው የተነሳ ቢፈራቸው እየተናገረና እያደረገ ያለውን በውስጡ እስከ ተቃወመ ድረስ ለእነርሱ ታማኝነትን እና ውጫዊ ፍቅርን ማሳየት እንደሚችል ፋክሀራዲን አራዚ ይናገራል። ይህም ማለት በውስጡ ከሚያምንበት ተቃራኒ የሆነን ነገር ሊናገር ይችላል ማለት ነው። ከተቂያ በተጨማሪም መሐመድ ውሸትን ሲያፀድቅ (ትክክል እንደሆነ ሲናገር) አንድ ሙስሊም በእነዚህ ሶስት ሁኔታዎች ውስጥ ሆኖ ቢዋሽ አላህ በተጠያቂነት አይዘውም ሲል ተናግሯል፦

  • በጦርነት፣ ስለላ፣ መሸሸግ ወይም በደካማነት ጊዜ
  • ለሚስቱ ወይም ሚስት ደግሞ ለባሏ
  • በማስታረቅ ወይም ሰላምን በማስጠበቅ ጊዜ

መሐመድ “ጦርነት ሸፍጠኝነት ነው” በማለትም ተናግሯል። በመሪዎች እና በተቋማቶቻቸው አማካይነት፣ በግለሰብ ደረጃ ወይም በማኅበረሰብ ደረጃ ይህ ሸፍጥ (መዋሸት) ሊፈጸም ይችላል።

ተቂያ ሱኒን እና ሻይቶችን ጨምሮ በሁሉም የእስልምና ዓይነቶች ውስጥ ተግባራዊ ሲሆን ከሌሎቹ ጎልቶ በሻይቶች አስተምህሮ ውስጥ ስለሚንፀባረቅ አንዳንዶች ይህ የተለየ የሻይቶች ብቻ መሠረተ-እምነት ይመስላቸዋል።

አራተኛው ከሊፋ አሊ “የሚጎዳችሁ ከሆነ ፍትሕን መምረጥ የእምነት ምልክት ሲሆን፣ ለእናንተ ምንም ዓይነት ጥቅም የማያስገኝ ከሆነ ደግሞ ኢ-ፍትሐዊነት ይሆንባችኋል” ሲል እንደ ተናገረ ይወሳል።

አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ፣ ቃለ-መሀላ ከፈፀሙ በኋላ እንኳ ቢሆን ተቂያን የመጠቀም መብት አላቸው።

በመሐላዎቻችሁ በውድቁ (ሳታስቡ በምትምሉት) አላህ አይዛችሁም። ግን ልቦቻችሁ ባሰቡት ይይዛችኋል። አላህም በጣም መሐሪ ታጋሽ ነው። (ቁርአን 2.225)

አላህ በመሐላዎቻችሁ በውድቁ አይዛችሁም። ግን መሐላዎችን (ባሰባችሁት) ይይዛችኋል። ማስተሰሪያውም ቤተሰቦቻችሁን ከምትመግቡት ከመካከለኛው (ምግብ) ዐስርን ምስኪኖች ማብላት ወይም እነሱን ማልበስ ወይም ጫንቃን ነጻ ማውጣት ነው፤ (ከተባሉት አንዱን) ያላገኘም ሰው ሦስት ቀኖችን መጾም ነው፤ ይህ በማላችሁ ጊዜ የመሐላዎቻችሁ ማካካሻ ነው። መሐላዎቻችሁንም ጠብቁ። እንደዚሁ አላህ ለናንተ አንቀጾችን ያብራራል። እናንተ ልታመሰግኑ ይከጀላልና። (ቁርአን 5.89)

ከተቂያ ጋር የተያያዙት አታላይ ወጥመዶቻቸው በተለይም የሚጠቀማቸው ሰው ፈጽሞ አዕምሮውን የዘጋ እንደ ሆነ በተጠቂዎች ላይ የሚያደርሱት ውድመትና ጥፋት የትየለሌ እንደሆነ ቀጥሏል።

ለምሳሌ፦ በፓኪስታን አያሌ ቁጥር ያላቸው ሙስሊሞች ከመስጊዶች ድጋፍ ጋር ክርስቲያኖች፣ ሒንዱዎች እና ሌሎች መሐመድን እንደተሳደቡ በማስመሰል መሀላ አድርገው ከሰዋቸዋል። ሌሎች ደግሞ ለግላዊ ጥቅማቸው ወይም ማኅበረሰባዊ ጀሀድ ሲሉ ቁርኣንን አቃጥለው ወይም ገፆቹን ቀድደው ሙስሊም ባልሆኑት ሰዎች በተለይም በክርስቲያኖች እንደ ተደረገ በማስመሰል አምላክን የመሳደብ ማስረጃ አድርገው አቅርበውታል። እንዲህ ያለው ጥቃት ከደረሰባቸው ሰዎች አብዛኛዎቹ በእስር ቤት ሆነው አስቸጋሪ ዓመታት ሲያሳልፉ፣ ቤተሰቦቸው ደግሞ ሥራቸውን እና የመተዳደሪያ መንገድ ከማጣት ጋር የተገለሉ ይሆናሉ። ሁሉም ለማለት በሚያስደፍር ሁኔታ አብዛኛዎቹ ለመደበቅ እና በመጀመሪያ ይኖሩበት ከነበረው ስፍራ ለመሸሽ ይገደዳሉ።

ቅርብ ጊዜ የዴንማርክ ካርቱን ፊልሞች ችግር ሲከሰት አንዳንድ ሙስሊሞች ራሳቸው ቁጣ ሲቀሰቅሱባቸው በነበሩት ፊልሞች ላይ መሐመድን ይብስ በከፋ መልኩ የሚገልጹ ተጨማሪ ካርቱኖች ጨምረውበታል። ከዚያም በአውሮፓውያኑ ላይ ነገር ለመጠምጠምና ጥቃት ለመፈጸም ሲሉ ፊልሙን ለሌሎች ሰዎች አሳይተዋል። በብዙ እስላማዊ ሀገራት ውስጥ ብዙ ሰዎች ተገድለዋል፣ የሥራ ቦታቸው በሙስሊሞች ከመቃጠሉ የተነሳ መተዳደሪያቸውን አጥተዋል።

አንድ ሙስሊም እንዴት ይህንን ሊያደርግ ይችላል? ምክንያቱ በተቂያ እስከተደረገ ድረስ የመሐመድ መዘለፍ አጀንዳ ሆኖ ከተነሳ ይህንን የሚፈቅድና የሚያበረታታ ፋትዋ በእስላማዊው የሕግ አዋጅ ውስጥ መካተቱ ነው። (ይህ በሕንድ ሀገር የወጣ ፋትዋ ሲሆን በፋትዋስ ኦቭ ካዲክሃን አል ፉር ጋኒ አል ሀናፊ 489 በወጣውና በቤይሩት ሀገር በዳር አል አህያ ቱራት አል አራቢ ከታተሙት የሕንድ ፋትዋዎች ውስጥ ይካተታል።)

ሙስሊሞች በተቂያ (ዘ ኮምፓይሌሽን ኦቭ ዘ ኩራኒክ ኢንጀንክሽንስ ባይ ካርታቢ፣ ሴክሽን 10.180) እስከ ሆኑ ድረስ ለጣዖት እንዲሰግዱ ይፈቅድላቸዋል፤ በተጨማሪም ተቂያን በጥቅም ላይ እስካዋሉት ድረስ የታወቀውን እና የተደነገገውን ስግደታቸውን ሳይሰግዱ መተው ይችላሉ። (ካርታቢ 10.180 ኤፍ.ኤፍ)

ተቂያ መስጊዶችን እንዴት እንደሚነካ ለመረዳት እስላማዊ የሕግ ሰዎች የተናገሩትን እና ከዚያ ጋር በተያያዘ የወጡትን ፋትዋዎች መመልከት ይኖርብናል።

 

 

የአዘጋጁ ማሳሰቢያ

በክርስትያኖች ቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ በተቀመጠው ዘመን በማይሽረው የስነ ምግባር ሕግ ማለትም በአስርቱ ቃላት ውስጥ ንግግርን በተመለከተ የተጠቀሱ ሁለት ሕግጋት ይገኛሉ፡፡ አንደኛው ዘፀዓት 20.7 ላይ ያለው፡ “የእግዚአብሔርን የአምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ፤ እግዚአብሔር ስሙን በከንቱ የሚጠራውን ከበደል አያነጻውምና።” ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በዘፀዓት 20.16 ላይ ያለው “በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር።” የሚሉት ናቸው፡፡ በመሆኑም በማንኛውም ምክንያት ሐሰት መናገር በክርስትያን አምላክ በእግዚአብሔር የተከለከለ ነው፡፡ ምክንያቱም የመጽሐፍ ቅዱሱ ሕግ የሚያንፀባርቀው የአምላክን ባህርያት፣ ማለትም ፍፁም፣ ቅዱስ፣ እውነተኛ መሆኑን ሲሆን እርሱን እናምናለን የሚሉትም የእርሱን ባህርይ እና ትዕዛዛቱን ማክበር ስላለባቸው ነው፡፡

የክርስትያን ቤተክርስትያንም የምታስተምረውና የቆመችው ለእውነት ብቻ ነው፡፡ ሰዎች እግዚአብሔርን መከተልም ያለባቸው በእውነት ቃሉ መሰረት ብቻ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል መጽሐፍ ቅዱስ ውሸትን ማውገዝ፤ ውሸት ኃጢአትና በእግዚአብሔር ላይ ማመፅ መሆኑን ከመግለፅ ባሻገር ውሸት የማንና ከማን እንደሚመነጭም ይናገራል፡፡ ይህንን ግልፅ ያደረገው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከአይሁዳውያን ጋር ሲነጋገር በነበረበት ጊዜ በዮሐንስ 8.44 ላይ ነው፡፡ እርሱም እንዳለው፡ “እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ እውነትም በእርሱ ስለ ሌለ በእውነት አልቆመም። ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፥ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና።”

በመሰረቱ መዋሸት የሰይጣን ነው እንጂ የእውነተኛው አምላክ የእግዚአብሔር አይደለም፡፡ ከዚህም የተነሳ በማንኛውም ምክንያትና ሁኔታ ሐሰትን መናገር ክርስትያናዊ አይደለም፡፡ እውነተኛ ክርስትያኖች መዋሸት አይፈቀድላቸውም፡፡ አምላካቸው እግዚአብሔር እውነተኛ አምላክ ነውና፡፡ ጌታ ኢየሱስ ግልፅ ያደረገው ሐሰት መናገር የመነጨው “ከዲያቢሎስ” እንደሆነ ነው፡፡ ዲያቢሎስ ነፍሰ ገዳይ ስለሆነ፣ እውነት በእርሱ ውስጥ ስለሌለ፣ በእውነት መቆም ስለማይችል፣ ከዚህም በላይ የሐሰት ምንጭ ስለሆነ፤ ሐሰትን ይፈቅዳል፤ ሐሰትን ያራምዳል፤ በሐሰትም ያታልላል፤ በሐሰትም ይጠቀማል፡፡

የክርስትያን መልእክት ከሐሰት ጋር ምንም የሚያገናኘው ምክንያት የለውም፣ ምክንያቱም ለግል ጥቅም፤ ለግል ዝና፤ እንዲሁም ሌሎችን ለመቆጣጠር የተጀመረ አይደለም፡፡ የክርስትያን መልእክት ዋናው ዓላማ ሰዎችን ከኃጢአት አዘቅት ውስጥ ለማዳንና ለሰው ጥልቅ የሆነ የውስጥ ችግር መልስ መስጠት ነው፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለው ደግሞ በእውነት ብቻ ነው፡፡

የዚህ ገፅ አዘጋጆች አንባቢዎችን ሁሉ አሁንም የሚጋብዟችሁ በእውነት መልእክት የተሞላውንና ጥልቅ ለሆነው መንፈሳዊ ችግር ሁሉ መልስ የሚሰጠውን፣ ወደ ዘለቄታው እውነት የሚመራችሁን መጽሐፍ ቅዱስን በማስተዋል እንድታነቡ ነው፡፡ እኛን የረዳን ቅዱስና እውነተኛው አምላክ እግዚአብሔር ይርዳችሁ አሜን፡፡

ወደ ማውጫው መመለሻ

ለእስልምና መልስ አማርኛ  ዋናው ገጽ