የቁርአን የመጀመሪያ ምንጮች

ምዕራፍ አራት ክፍል አራት

የመሐመድ የግንዛቤ ስህተትና  ክህደቶች  

REV. W. ST. CLAIR TISDALL, M.A., D.D

ትርጉምና ቅንብር በአዘጋጁ

5. ስለ ሥላሴ የመሐመድ የግንዛቤ ስህተትና የስቅለት ክህደት

በዚህ በያዝነው ምዕራፍ ቀደም ባሉት ክፍሎች ውስጥ ይህንን ሐሳብ በመጠኑ ነካ አድርገነው ነበር ነገር ግን እዚህ ላይም እንደገና የክርስትያን ሐሳብ በእስልምና ልምምዶች ላይ ያስከተለው ተፅዕኖ በአንድ በኩል በጣም ሙሉ እንደሆነ ማየት ይቻላል፡፡ መሐመድ ስለ ክርስትያኖች ስላሴ የመሰረተው ፅንሰ ሐሳብ ልክ እንዳለፉት ጥቂት አንቀፆች ስለ ጌታ እራት ምስረታን እንዴት እንዳየው እንዳሳዩት እዚህም ላይ ልክ እንደዚያው ትክክል ነው፡፡ ይህም በትክክል የሚረጋገጠው ከሚከተሉት አንቀፆች ላይ ነው፡-

‹አላህም፡- የመርየም ልጅ ዒሳ ሆይ አንተ ለሰዎቹ እኔንና እናቴን ከአላህ ሌላ ሁለት አምላኮች አድርጋችሁ ያዙ ብለሃልን? በሚለው ጊዜ (አስታውስ) ጥራት ይገባህ ለኔ ተገቢዬ ያልኾነን ነገር ማለት ለኔ አይገባኝም ብዬው እንደ ኾነም በእርግጥ ዐውቀኸዋል በነፍሴ ውስጥ ያለውን ሁሉ አንተ ታውቃለህ ግን አንተ ዘንድ ያለውን አላውቅም አንተ ሩቆችን ሁሉበጣም አዋቂ አንተ ብቻ ነህና ይላል፡፡› (ቁርአን 5. 116)

‹እላንተ የመጽሐፉ ሰዎች ሆይ! በሃይማኖታችሁ ወሰንን አትለፉ በአላህም ላይ እውነትን እንጂ አትናገሩ የመርየም ልጅ አልመሲሕ ዒሳ የአላህ መልክተኛ ወደ መርየም የጣላት (የኹን) ቃሙል ከርሱ የኾነ መንፈስም ብቻ ነው፣ በአላህና በመልክተኞቹም እመኑ (አማልክት) ሦስት ናቸው አትበሉም ተከልከሉ ለናንተ የተሸለ ይኾናልና አላህ አንድ አምላክ ብቻ ነው፡፡ ለርሱ ልጅ ያለው ከመኆን የጠራ ነው፡፡ በሰማያትና በምድር ያለ ሁሉ የርሱ ነው፡፡ መመኪያም በአላህ በቃ፡፡› (ቁርአን 4.171)

‹እነዚያ አላህ የሦስት ሦስተኛ ነው ያሉ በእርግጥ ካዱ ከአምላክም አንድ አምላክ እንጂ ሌላ የለም ከሚሉትም ነገር ባይከለከሉ ከነሱ እነዚያን የካዱትን አሳማሚ ቕጣት በእርግጥ ይነካቸዋል፡፡› (ቁርአን 5.73)

እነዚህ ጥቅሶች በተንታኞቹ በጃላሉዲን እና ያህያ አማካኝነት አንዳንድ ክርስትያኖች ሦስት አማልክት እንዳሉ ሲናገሩ መሐመድ መስማቱን በተመለከተ የተሰጡ መልሶቸ ናቸው በማለት ተብራርተዋል፡፡ ማለትም እግዚአብሔር አብ፣ ማርያም እና ኢየሱስ፡፡ ስለዚህም ከእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ በግልፅ መመልከት እንደሚቻለው መሐመድ በእርግጥ ያመነው የክርስትያን አስተምህሮ ሦስት የተለያዩ አማልክትን ያምን እንደነበረና ኢየሱስና ማርያም ደግሞ ሁለቱ እንደሆኑ ነበር፡፡ ነገር ግን ሦስተኛው ጥቅሳችን የሚያሳየው ከክርስትያኖች አምልኮ ላይ እንደተመለከተው ምናልባትም ያሰበው ቅደም ተከተል ኢየሱስ ማርያም እና እግዚአብሔር አብ ወይንም ማርያም ኢየሱስና እግዚአብሔር አብ እንደሆኑ ነው፡፡ መሐመድ በእግዚአብሔር ስም እንዲህ ዓይነት የክህደት ስድበ መለኮትን በማምጣቱ አንድ ሰው ቢናደድ ጤነኛ የሆነ ሰው ሊደነቅ አይገባም፡፡ ለማርያም ጣዖታዊ አምልኮ መሰጠቱና እሷን የሰማይ ንግስት እና የእግዚአብሔር እናት በማለት የጠሯት ሰዎች  እርሷ መለኮታዊ ባህርያት እንዳላት እንዲያምን መሐመድን ስላደረጉት እኛ ሁላችንም እናዝናለን፡፡ እርሱም በትክክል የተረዳው እግዚአብሔር በተግባር እርሷን ወዶ ከዙፋኑ እንደወረደ ነው፡፡ የእግዚአብሔር አንድነት የክርስትያን እምነት መሰረት መሆኑን ቢማር ኖሮ (በዘዳግም 6.4 እና ማርቆስ 12.4) መሰረት ምናልባትም የክርስትያን ተሃድሶ መሪ ሊሆን ይችል ነበር፡፡ የሦስትነትና አንድነትን ትክክለኛ አስተምህሮ ገለፀ ሊሰማ አልቻለም ነበር፣ እንደዚያ ባይሆን ኖሮ ክርስትያን ስነ መለኮት አስተማሪዎች እግዚአብሔር አብን ‹የሦስት ሦስተኛ› ወይንም ‹የመለኮት ምንጭ› ተብሎ እንደተገለፀው እንዳልሆነ ሲናገሩ ይሰማ ነበር እንደ፡፡

ስለዚህም እዚህ ላይ ገንዛቤ ውስጥ መግባት ያለበት ነገር ምንም እንኳን ለድንግል ማርያም የተሰጠው ትልቅ ክብር መሐመድን ከእውነተኛው የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ ቢያወጣውም እንኳን ሐሳቡ ከክርስትና እምነት ጋር የተቃረነ ነው፡፡  ይህንን የጠቀስነው ከዚህ ችግር ውስጥ ለመውጣት በመገመት ወይንም በማሰብ ማንኛውም መሐመዳዊ አንባቢ እንደሚከተሉት ዓይነት መጽሐፍት ማለትም ‹የማርያም መውለድ› ‹የትንሹ ያዕቆብ ቅድመ ወንጌል› እና የአረብኛው ‹የሕፃንነት ወንጌል› በክርስቶስ ትምህርት ከተሰጠባቸውና አዲስ ኪዳን ውስጥ ካሉት ቅዱሳን የተረጋገጡ መጻሕፍት የተሻሉ ናቸው በማለት ማስረጃ ለመፈለግ እንዳይደክሙ ነው፡፡ የመሐመዳውያን ክርክሮች እንደዚህ ዓይነት ማስጠንቀቂያዎችን መስጠት አስፈላጊ ሆኖ ያገኙታል፡፡

6. የክርስቶስን መሰቀል መካድ

መሐመዳውያን በሙሉ ከጥንት ጀምሮ የክርስቶስን በመስቀል ላይ መሞት መካዳቸው በጣም የታወቀ ነገር ነው፡፡ ለዚህም እነሱ የተደገፉበት በቁርአን 4 ቁጥር 156 ላይ ባለው ጥቅስ ነው አይሁዶች እንዳሉት በሚወክለው ላይ፡ ‹እኛ የአላህን መልእክተኛ የመርየምን ልጅ አልመሲሕ ዒሳን ገደልን በማለታቸውም (ረገምናቸው) አልገደሉትምም ግን ለነሱ (የተገደለው ሰው በዒሳ) ተመሰለ፣ እነዚያም በርሱ ነገር የተለያዩት ከርሱ (መገደል) በመጠራጠር ውስጥ ናቸው ጥርጣሬን ከመከተል በስተቀር በርሱ ነገር ምንም ዕውቀት የላቸውም በእርግጥም አልገደሉትም፡፡›

የክርስቶስን የመስቀል ሞት መሐመድ መካዱ እርሱ ከመረጣቸውና ምንም ዋጋ ከሌላቸው አፖክሪፋል ወንጌሎች ውስጥ እንኳን ሊገኝ አይቻልም፡፡ እርሱ የብሉይ ኪዳንንም ነቢያትና የአዲስ ኪዳንን ሐዋርያት የሚቃረን መሆኑ መናገር እስከማያስፈልግ ድረስ ግልፅ ነው፡፡ ከአለማወቅ የተነሳ መሆኑ የሚያጠራጥር ቢሆንም፤ ክርስቶስ በጠላቶቹ በራሱ በመሐመድም ጠላቶች በአይሁድ ተይዞ መሰቀሉና እንዲሞት መደረጉና አይሁድም ክርስቶስን ስለገደሉት ሲፈነጥዙ ባገኘበት ጊዜ ክብረ ነክ የሆነ ነገር መስሎትና በጣም አምኖበት ነበር፡፡ ስለዚህም በሌሎች ነገሮች አኳያ ከእርሱ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸውን የአንዳንድ የሐሰት አስተማሪዎችን ጭማሬ በደስታ ወስዷል፡፡ ብዙዎቹም እነዚህ የሐሰት አስተማሪዎች መሐመድ ከመምጣቱ ከብዙ ጊዜ በፊት የነበሩ ሲሆን የክርስቶስን ስቃይ ክደው ነበር፡፡ የኖስቲክ ኑፋቄ አስተማሪና በ120 ዓ.ም አካባቢ በጣም ታዋቂ ሆኖ ስለነበር ባሲሊደስ የተባለው ሰው ለተምታታባቸው ተከታዮቹ ስለ ኢየሱስ ሲናገር ያስተምር የነበረውን ኢሬንየስ እንደሚከተለው ነግሮናል፡- ‹እርሱም አልተሰቃየም ነገር ግን  የሴሬኒው ስምዖን የተባለው አንድ ሰው የእርሱን መስቀል ለእርሱ ለመሸከም ተገድዶ ምንም ነገርን ሳያውቅ በስህተት ተሰቀለ፣ እርሱም እርሱን መስሎ በእርሱ ተለውጦ ነበር፣ ስለዚህም እርሱ እራሱ ኢየሱስ ነው ተበሎ ታስቦ ነበር›፡፡ ይህ አባባል ቁርአን በዚህ ጉዳይ ላይ ከሚሰጠው ጋር በጣም አብሮ የሚሄድ ነው፡፡ ነገር ግን በኢሬንየስ መሰረት የባሲሊደስ አመለካከት የተመሰረተበትን መርሆ መሐመድ አልተቀበለውም፡፡ ምክንያቱም ባሲሊደስ ያምን የነበረው ኢየሱስ ከ nouv  ወይንም አዕምሮ ጋር አንድ እንደነበር፤ ይህም ከማይታወቅ አምላክ የወጣው የመጀመሪያው ነገር ነው፣ ስለዚህም እርሱ ሊሰቃይ አይችልም ነበር ምክንያቱም እርሱ እውነተኛ የሆነ የሰው አካል፣ ከሰው እናት የተወለደ በአንድ ወቅት ወይንም በሌላ ጊዜ ለመሞት የተመደበ አካል አልነበረውም፡፡ ስለዚህም እዚህ ላይ የምናየው አንድ ሐሳብን ወይንም ነገርን ያመጣበትን መርሆ (ሐሳቡ ወይንም ነገሩ የተመሰረተበትን መርሆ) መሐመድ ይቃወመዋል ይሁን እንጂ ውጤቱን ተቀብሎት በቁርአን ውስጥ አስቀምጦታል፡፡ ይህም ሙሉ ለሙሉ ሎጂካዊ ያልሆነ አካሄድ ሲሆን ሊታይ የሚችለውም እጅግ በጣም ከፍተኛ የሆነ የተፈጥሮ ድንቁርና ወይንም አለማወቅ ተደርጎ ብቻ ነው፡፡

ነገር ግን ይህ ክርስቶስ በእይታ እንጂ በእውነት አልሞተም የሚለው አመለካከት በባሲሊደስ ላይ የተመሰረተ ብቻ አይደለም፡፡ ፎቲየስ (920-91 ሲርካ) በራሱ ቢቢሎቲካ (ኮድ 114) የጠቀሰው ነገር በኦፖክሪፋው መጽሐፍ ‹የሐዋርያት ጉዞ› በተባለው ውስጥ ‹ክርስቶስ አልተሰቀለም ነገር ግን ሌላው በእርሱ ፋንታ ተሰቅሎ ነበር› የሚል ተጠቅሶ ተገኝቷል፡፡ ማነስ ወይንም ማኒ የተባለው እና በፐርሺያ ውስጥ ከፍተኛ ተፅዕኖን አትርፎ የነበረውና የተከበረው የሐሰት ነቢይ በተመሳሳይ መንገድ ያምን የነበረው ‹በመስቀሉ ላይ የጨለማው ገዢ ተሰቅሎ ነበር እንዲሁም እራሱም የእሾክ አክሊል አድርጎ ነበር› ብሏል፡፡ መሐመድ በጥሩና ታማኝ ምንጭ ላይ ተመስርቶ የክርስቶስን መሞት ካደ ተብሎ ሊነገር አይቻልም ወይንም እንዲህም በማድረጉ እርሱ መልካም (ትክክለኛ) ህብረት ነበረው ማለትም አይቻልም፡፡

ይሁን እንጂ በብዙ የቁርአን ጥቅሶች ላይ ግልጥ የተደረገው እውነታ ልክ እንደሌሎቹ የሰው ልጆች ሁሉ ኢየሱስ ሊሞት እንደነበር ነው፡፡ ለምሳሌም ያህል በቁርአን 3.55 ላይ እንደሚከተለው ተጽፏል፡- ‹አላህም ባለ ጊዜ (አስታውስ) ዒሳ ሆይ እኔ ወሳጅህ ወደ እኔም አንሺህ ነኝ ከነዚያም ከካዱት ሰዎች አጥሪህ ነኝ እነዚያንም የተከተሉህን እስከ ትንሳኤ ቀን ድረስ ከነዚያ ከካዱት በለይ አድራጊ ነኝ ከዚያም መመለሻችሁ ወደኔ ነው በርሱ ትለያዩበትም በነበራችሁት ነገር በመካከላችሁ እፈርዳለሁ› እንዲሁም በቁርአን 19.33 ላይ ኢየሱስ በአንቀልባ ላይ እንደሚከተለው እንዳለ ተደርጎ ተነግሯል፡- ‹ሰላምም በኔ ላይ ነው በተወለድሁ ቀን በምሞትበትም ቀን ሕው ኾኘ በምቀሰቀስበትም ቀን› ተንታኞች የእነዚህ አንቀፆች ትክክለኛ ትርጉም ምንድነው? በሚለው ላይ በፍፁም አልተስማሙም፡፡ አንዳንዶች የሚያምኑት አይሁዶች ክርስቶስን ለመስቀል በፈለጉ ጊዜ እርሱንና ደቀመዛምርቱን ያዙና አሰሯቸው የፋሲካ በዓል ከመሆኑ በፊት ባለው ሌሊት (ዋዜማ)፣ ይህም በሚቀጥለው ቀን ጠዋት ሊገድሉት አቅደው ነበር፡፡ ነገር ግን በማታው እግዚአብሔር ለእርሱ መልእክትን ላከለት ‹አንተ በእኔ ውስጥ ትሞታለህ ነገር ግን ወዲያውኑ አንተ ወደ እኔ ትወሰድና ከማያምኑት ኃይል (እጅ) ነፃ ትሆናለህ›፡፡ በዚህ መሰረት ኢየሱስ ተገደለና በሞት ውስጥ ለሦስት ሰዓታት ያህል ቆየ፤ ሌሎች ግን የጠቀሱት ረጅምን ጊዜ ነው፡፡  ይሁን እንጂ በመጨረሻ ገብርኤል ተገለጠና ተሸክሞት በመስኮት ውስጥ ይዞት ወደሰማይ ሄደ ይህ በማንም ሰው አልታየም፡፡ የማያምን አይሁዳዊ ሰላይም እሱን መስሏቸው በእርሱ ምትክ ተሰቀለ፡፡ ነገር ግን በጣም የታወቀው በሁሉምና በዓለም አቀፍ ሙስሊም አማኞች ዘንድ በአሁኑ ጊዜ በልማድ በተደገፈው ስራ ውስጥ እንደ ቂሳዑል አናቢያና አራይሱት ቲጃን ስራ ውስጥ ያለው ነው፡፡ በእነዚህ መጽሐፍት ውስጥ የተነገረን ነገር አይሁዶቹ ኢየሱስና ደቀመዛምርቱ ያለበትን ቤት በከበቡበት ጊዜ ገብርኤል ኢየሱስን በጣራው በኩል ወይንም በመስኮት ተሸክሞ  በሕይወት እንዳለ እስከ አራተኛው ሰማይ ድረስ ወሰደው፡፡ ሹይግ ‹የአይሁድ ንጉስ› ወይንም ፋልቲያነስ የሚባለው የእርሱ ጓደኛ ኢየሱስን ለመግደል ቤቱ ውስጥ ገብተው እርሱ መስሏቸው ገደሉት፡፡ የሆነው ሆኖ ጌታ ኢየሱስ መሞት አለበት ለዚህም ወደ ምድርም መመለስ ይኖርበታል ይህ ነው በቁርአን 3.55 ላይና በቁርአን 19.33 ላይና እንዲሁም በ4.159 ላይ እንዲታይ የተደረገው፣ በኋለኛው አንቀፅ ውስጥ ያለው (‹ከመጽሐፉም ሰዎች ከመሞቱ በፊት በእርሱ (በዒሳ) በእርግጥ የሚያምን እንጂ (አንድም) የለም በትንሳኤም ቀን በነሱ ላይ መስካሪ ይሆናል› ብዙዎች እንደሚያስቡት ሐሳቡ ለክርስቶስ ሞት የሚያመለክት ነው (ከዚህ በላይ የተጠቀሰው የአማርኛው ቁርአን በተለይም ጥሩ ፍንጭን ይሰጠናል ይህም በቅንፍ ‹ዒሳን› በማለት ስላስቀመጠው ነው)፡፡ የተረገመው ‹ዳጃል› መጥቶ ሰዎችን በማሳት ከሃዲዎች በሚያደርግበት ጊዜ ኢማሙ መሕዲ ከብዙ ሙስሊሞች ጋር በኢየሩሳሌም ይሆናል፣ ከዚያም ኢየሱስ መጥቶ ከዳጃል ጋር ይዋጋና ይገድለዋል ከዚያም የራሱን ተከታዮች የመሐመዳውያንን እምነት እንዲከተሉ ይጋብዛል፡፡ ኢየሱስም የመሐመዳውያን እምነት ይኖረዋል እርሱም በእስላም ለሚያምኑት ለእያንዳንዳቸው የተለየ ስፍራን ይሰጣቸዋል፤ ነገር ግን በእስላም የማያምኑትን ደግሞ እያንዳንዳቸውን ይገድላቸዋል፡፡ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ እርሱ ዓለምን በሙሉ ያስገዛል እና ሕዝቡን በሙሉ ሙስሉማን ያደርጋቸዋል እርሱም የሙሐመዳንን ሃይማኖት ጠቀሜታ ወደዚህ ደረጃ ከፍ ያደርገዋል ስለዚህም በመላው ዓለም ውስጥ የማያምን የሚባል ምንም ነገር አይኖርም ዓለምም በሙሉ ሙሉ ለሙሉ የሰለጠነችና ሙሉ ለሙሉ የተባረከች ትሆናለች፡፡ እርሱም ፍትህን ፍፁም ያደርጋል ስለዚህም ተኩላና አጋዘን አብረው ውሃን ይጠጣሉ እንዲሁም እርሱ ከክፉ አድራጊዎች ጋር በጣም ይጣላል፡፡ ከዚያም በዚህ መንገድ ለአርባ ዓመታት ከቀጠለ በኋላ ዓለምን ያሻሽላል እርሱም የሞትን መራራነት ይቀምስና ዓለምን ይተዋል፡፡ ከዚያ ሙስሊማኖች በተመረጠው በመሐመድ አጠገብ ይቀብሩታል፡፡›

ስለ ክርስቶስ መመለስና ስለ መንግስቱ በዓለም ሁሉ ላይ መመስረት የተነገረው ነገር በትክክል ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተወሰደና የሚመሳሰለውም ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ነው፡፡ በተለይም ከሐዋርያት 1.11፣ ራዕይ 1.7 ኢሳያስ 11.1-10 ጋር ነው፡፡ ነገር ግን ‹የእባቡ ፈለግ በሁሉም ቦታ ላይ ይታያል› ምክንያቱም ክርስቶስ እስልምናን በዓለም ሁሉ ውስጥ በሰይፉ ያስፋፋል ይላልና፡፡ የሐሰተኛው ክርስቶስ መወርወርና መጣል ሐሳብ የተመሰረተው በ2ተሰሎንቄ 2.8-10 ላይና በሌሎችም ተመሳሳይ ክፍሎች ላይ ነው፡፡ ነገር ግን ክርስቶስ ተመልሶ ከመጣ በኋላ ይሞታል የሚለውን ሐሳቡን መሐመድ ያመጣው ከምን ዓይነት ምንጭ  ነው በማለት እኛ መጠየቅ አለብን፡፡ ከዚህ ከጠቀስነው የቁርአን ክፍል ትርጉም እንዲሁም ከማንኛውም ታማኝነት ከተሰጣቸው ልማዶች ላይ ማለትም ባይሃቂ እና ሌሎች እንደመዘገቡትና ከመሐመድ አንደበት የመጣ ነው በማለት እንዳሳዩት ነውን? ለዚያ ውጤት እያንዳንዱ ክርስትያን ማወቅ ያለበት እንደዚህ ዓይነት ግምት ሙሉ ለሙሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የተቃረነ መሆኑን ነው (ራዕይ 1.17-18)፡፡

እዚህም ላይ እንደገና የአፖክሪፋዊ ስራዎች እኛን ለመርዳት እየመጡልን ነው፡፡ በአረብኛ መጽሐፍ ውስጥ (ምልባትም የኮፕቲካዊ ምንጭ ላይ የሚገኘው)፤ ‹የቅዱስ አባታችን የሽማግሌው ሰው አናጢው ዮሴፍ› ተብሎ የሚታወቀው ጽሑፍ አለ፡፡ እዚያም ውስጥ ሳይሞቱ ወደሰማይ ስለወጡት ስለ ሄኖክና ስለ ኤልያስ ተነግሮናል፡፡ ያም ‹እነዚህ ሰዎች በመጨረሻው ጊዜ ወደ ዓለም መምጣት እንዳለባቸው፣ እርሱም የሚሆነው በችግርና በፍርሃት፣ በትልቅ ትርምስና እና ጭንቀት ወቅት መጥተው መሞት አለባቸው፡፡› ‹ምዕራፍ 21›፡፡ ተመሳሳይ በመሰለ የኮፕቲካዊ ስራና ‹የማርያም ማንቀላፋት (ሞት) ታሪክ› የሚል ርዕስ በተሰጠው መጽሐፍ ውስጥ ተመሳሳይ የሆኑ፤ ‹ነገር ግን ስለ ሌሎቹ ስለ እነዚህ› (ሄኖክና ኤልያስ)፤ ‹ለእነሱም ሞትን መቅመሳቸው በጣም አስፈላጊ ነው› የሚሉ ቃላትን እናነባለን፡፡ መሐመድ እንደዚህ ዓይነት አባባሎችን ሰምቶ መሆን አለበት ምክንያቱም እነዚህን በቁርአን ውስጥ ሁለት ጊዜ ተናግሯቸዋልና ቁርአን 3.185 ላይና 29.57 ላይ፣ ‹ነፍስ ሁሉ ሞትን ቀማሽ ናት ከዚያም ወደኛ ትመለሳለች›፣ በእርግጥ እርሱ እንዳደረገው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ወጣ ቁርአን 3.55 የሚለው ይህንን ሐሳብ ነው፣ ከዚያም በመሐመድ አዕምሮው ውስጥ የፈሰሰው ክርስቶስም እንደ ሄኖክና እንደ ኤልያስ እና በእርግጥ በሁለተኛው (ዳግም መጥቶ) እንደሚሞት ነው፡፡ ስለዚህም የክርስቶስ ባዶው መቃብር አሁን በመዲና ውስጥ ለእርሱ ዝግጁ ሆኖ ተቀምጧል ይህም በመሐመድና በአቡበከር መቃብሮች መካከል ነው፡፡

የመሐመዳውያን ልማድ ደግሞ የሚነግረን ክርስቶስ ከተመለሰ በኋላ ሚስትን እንደሚያገባ ነው፡፡ ይህም የሚከተሉትን ዓይነት አንቀፆችን በተሳሳተ መንገድ ከመረዳት የመነጨ ነው፡- ራዕይ 19.7-9 ‹የበጉ ሰርግ ስለ ደረሰ ሚስቱም ራስዋን ስላዘጋጀች ደስ ይበለን ሐሤትም እናድርግ ክብርንም ለእርሱ እናቅርብ። ያጌጠና የተጣራ ቀጭን የተልባ እግር ልብስ እንድትጐናጸፍ ተሰጥቶአታል። ቀጭኑ የተልባ እግር የቅዱሳን ጽድቅ ሥራ ነውና። እርሱም። ወደ በጉ ሰርግ እራት የተጠሩ ብፁዓን ናቸው ብለህ ጻፍ አለኝ። ደግሞም። ይህ የእግዚአብሔር እውነተኛ ቃል ነው አለኝ።› በእርግጥ የዚህ አምሳሌያዊ ክፍል ሐሳብ በሌላ ቦታ ላይ ትርጉም ተሰጥቶታል ይህንንም ለማየት ራዕይ 21.2 እና ኤፌሶን 5.22-23 ላይ ያሉትን መመልከት መልካም ነው፡፡ ይህም በአዳኙና በእርሱ በተቀደሰው፤ በዳነው ሕዝቡ መካከል ሊኖር ስለሚገባው ፍፁም ፍቅርና ሙሉ አንድነት የሚያመለክት ነው፡፡

ክርስቶስ ወደ ምድር ከተመለሰ በኋላ ለአርባ ዓመታት ይኖራል የሚለው ቃል የመነጨው የሐዋርያት ስራ 1.3ን በተሳሳተ መንገድ ከመረዳት ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ ሞቶ ከተነሳ በኋላ ከማረጉ በፊት ለአርባ ቀናት ከደቀመዛምርቱ ጋር እንደቆየ የምንማርበት ክፍል ነው፡፡

7. ስለ መሐመድ መምጣት ክርስቶስ ተንብዮአል የተባለው

የመሐመዳውያን ተከራካሪዎች ስለመሐመድ ስለተነገረ ትንቢት የሚያነሷቸውና ለማረጋገጥ የሚጥሩባቸው ብዙ ጥቅሶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን እኛ እዚህ ላይ ማንሳት የምንፈልገው ጥቂት ተከታታይ ጥቅሶችን ነው፤ ምክንያቱም በቁርአን ውስጥ ስለመሐመድ መምጣት ክርስቶስ ለደቀመዛምርቱ ተናገረ የሚል ቃል በግልጥ ያለው አንድ ጥቅስ ላይ ብቻ ነውና እንዲሁም እርሱ በዮሐንስ ወንጌል ላይ ያሉትን ጥቅሶች ላይ የሚመለከት ነው፡፡ በቁርአን 61.6 ላይ የሚከተለውን መሐመድ ጽፏል፡-

‹የመርየም ልጅ ዒሳም፡- የእስራኤል ልጆች ሆይ እኔ ከተውራት በፊት ያለውን የማረጋግጥና ከኔ በኋላ በሚመጣው መልክተኛ ስሙ አሕመድ በኾነው የማበስር ስኾን ወደናንተ (የተላክሁ) የአላህ መልክተኛ ነኝ ባለ ጊዜ (አስታውስ) በግልጽ ታምራቶች በመጣቸውም ጊዜ ይህ ግልፅ ድግምት ነው አሉ፡፡›

እዚህ ላይ ያለው ማገናዘቢያ በዮሐንስ 14.16ና 26 በዮሐንስ 15.26ና በዮሐንስ 16.7 ላይ የሚገኘው ነው፡፡ መሐመድ ምንም በማያውቁ ነገር ግን ወደ ክርስትና በተቀየሩና ቅናት ባላቸው ወይንም በሌሎች ደቀመዛምርት ተሳስቶ እንደነበረ አመልክተናል፡፡ እነርሱም እነዚህ ጥቅሶች ላይ ያለውን ‹ጰራቅሊጦስ› Paravklhtov የሚለውን የግሪክ ቃል በሌላ የግሪክ ቃል ማለትም ‹ጰሪክሉቶስ› Perikluto በሚለው ቀይረውት እንደነበረ ነው፡፡ ይህም ያለምንም ትልቅ የቃላት ልጠጣ ግምት በአረብኛ ‹አሕመድ› ወደሚለው ቃል ሊተረጎምና ትርጉሙም ‹በጣም የተመሰገነው› ብቻ የሚል ሊሆን ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ ለመሐመድ የተሰጠ ነው ተብሎ የተጠቀሰው ቃል ‹ጰሪክሉቶስ› የሚለው አይደለም፣ ከዚህም ባሻገር ጌታችን የተጠቀመበት ቃል በምንም ዓይነት ጥረት አሕመድ ተብሎ ሊተረጎም አይችልም፡፡ ‹ትንሽ እውቀት› የግሪክ ቋንቋም እንኳን ቢሆን ‹አደገኛ ነገር› ሊሆን ይችላል፣ በእርግጥም ይህ ምሳሌ ከቁርአን ውጪ በሌላ በምንም ነገር በጥሩ ሁኔታ ሊተረጎም አይችልም፡፡ በእርግጥ በዮሐንስ ወንጌል ላይ ያሉትን እነዚህን ክፍሎች የሚያነብ ማንም ቢኖር በእነርሱ ውስጥ ወደፊት ስለሚመጣ ምንም ዓይነት ነቢይ በፍፁም እንደማይናገሩ፤ እንዲሁም በምንም ዓይነት መንገድ ለምንም ዓይነት ሰው ሊሆኑ እንደማይችሉ ያስተውላል፡፡ ከዚህም በላይ እያንዳንዱ ክርስትያን የሚያውቀው ይህ ቃል ኪዳን እንዴት እንደተሟላ ነው (ሐዋርያት 2.1-11)፡፡ መሐመድ መንፈስ ቅዱስ ነኝ ማለቱ በሌላ ጎኑ ስህተት ነው ምክንያቱም ሙስሊሞች እርሱን ገብርኤል ነው ይሉታልና፡፡

እንዲህ ዓይነትን ጥያቄ ለእራሱ በማቅረብ በኩል መሐመድ የመጀመሪያው እንዳልሆነ ይህንን ክፍል (ርዕስ) ከመተዋችን በፊት ለአንባቢዎች ማስታወስ በጣም መልካም ይሆናል፡፡ ማኒ ወይንም ማነስ በፐርሺያውያን ተረት ውስጥ እንደ አስደናቂው ሰዓሊ ተደርጎ በጣም የሚታወቀው የነበረው ሰው በክርስቶስ የተነገረው ሰው ነኝ በማለት ተመሳሳይን ጥያቄ አድርጎ ነበር፡፡ ማኒ ብቻ በተለይም ‹ጰራቅሊጦስ› ነኝ በማለት እራሱን ጠርቶ ነበር፣ ምልባትም (ልክ እንደ መሐመድ) ምንም ያልተማሩትን ክርስትያኖች በራሱ ጎን ለማሰለፍ አስቦ ይሆናል፡፡ ይህ አስደናቂ ነው እርሱ ታሪካዊውን ኢየሱስን ተቃውሞ (አልቀበልም ብሎ) ለራሱ ሌላ (ኢየሱስን) ፈጥሮ ነበር፣ የእርሱም ኢየሱስ ያልተሰቃየና ያልሞተ ኢየሱስ ነበር፡፡ ሦስተኛው ነጥብ መሐመድን የሚመስልበት ነገር እርሱ የመጨረሻውና ከነቢያትም ሁሉ ታላቁና ‹የብርሃን አምባሳደር› ነኝ ማለቱም ነበር፤ በዚህም እራሱን ከመለኮት ጋር አንድ አድርጎ ነበር፡፡ ነገር ግን እርሱ ከመሐመድ ይልቅ ዕድለ ቢስ ነበር ምክንያቱም በፐርሺያዊው ቀዳማዊ ባህራም ትዕዛዝ መሰረት በ276 ዓ.ም አካባቢ ተወግቷል፡፡ በመጨረሻም ‹አርታንግ› የሚባልን መጽሐፍ በኦርየንታል ጸሐፊዎች አዘጋጅቷል፣ እዚያም ከሰማይ እንደተላከና ለሰዎችም ከተላኩት ውስጥ የመጨረሻው መገለጥን ያመጣ ነቢይ እንደሆነ ተናግሯል፡፡ እርሱም የክርስቶስን ስቃይ የካደበት ሐሳቡ የመነጨው ማንኛውም ‹ቁሳዊ ነገር› ሁሉ በመሰረቱ ክፉ ነው የሚለውን የኖስቲክን ሐሳብ በመቀበሉ ነው፡፡ ስለዚህም ይህ እምነቱ እውነተኛው ኢየሱስ የሰው አካል ነበረው የሚለውን እንዲክድ አድርጎታል፡፡ በዚህ በኩል የባሲሊደስን ሐሳብ በመከተሉ እንዳየነው ሁሉ ከመሐመድ ይልቅ የተሻለ ሎጂካዊ የነበረ አድርጎታል፡፡

የአዘጋጁ ማሳሰቢያ፡

ከዚህ በላይ በቀረበው ሰፊ ትንተና ውስጥ መሐመድ የስላሴን ትምህርት፣ የክርስቶስ ኢየሱስን መሰቀልና ለሰው ልጅ የዘላለም ሕይወት የሚሆነውን የደኅንነት መሰረት መካዱ፣ ምንጫቸው የእግዚአብሔር መገለጥ ማለትም ከእግዚአብሔር የመጡ ትምህርቶች ሳይሆኑ ከመሐመድ በፊት በነበሩ የሐሰት አስተማሪዎች የተሰራጩ ስህተቶች መሆናቸውን በግልፅ መገንዘብ ይቻላል፡፡

አዲስ ኪዳንም ሆነ የብሉይ ኪዳን መጽሐፍት ስለ መሐመድ ነቢይ ሆኖ መምጣት ትንቢትን ይናገራሉ የሚለውንም ለማረጋገጥ የሚደረግ ብዙ ጥረት ይደረጋል፡፡ ይሁን እንጂ ከመሐመድ በፊት የተነሱ የሐሰት አስተማሪዎችም ልክ እንደ መሐመድ ተናግረው እንደነበረ ይህም በታሪክ እንደተረጋገጠ መገንዘብም አስደናቂ ነው፡፡

የዚህ ገፅ አዘጋጆች ለሙስሊም አንባቢዎች የሚያስገነዝቡት እነዚህን ማስረጃዎች በቅንነት እንዲመለከቷቸውና ስለዘላለማዊ ሕይወታቸው በትኩረት እንዲያስቡ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የዘላለምን ሕይወት ለመውረስ የሚቻለው በደኅንነት በኩል እንደሆነ መዳን የሚባለውንም እውነት ማግኘት የሚቻለው በአንድ መንገድ ብቻ እንደሆነ ያስረዳል፡፡ ይህንንም ያለምንም የእርስ በእርስ ቅራኔ ግልፅ በሆነ መንገድ ከብሉይ ኪዳን ጀምሮ አዲስ ኪዳን መጨረሻ ድረስ ያቀርባል፡፡

‹መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና።› ሐዋርያት 4.12፡፡ ይህንን የመዳን መንገድ እንድታገኙ ወንጌል በሚሰበክበት ቦታ በመሄድ የጌታን ቃል ስሙ ኃጢአታችሁንም ተናዛችሁ በጌታ ማዳን ታመኑ እግዚአብሔርም ይቀበላችኋል አዲስንም ሕይወት ይሰጣችኋል፡፡ ጌታ እግዚአብሔር ይርዳችሁ አሜን፡፡

የትርጉም ምንጭ: THE ORIGINAL SOURCES OF THE QUR'AN 

ሙሉ መጽሐፉ በአማርኛ:  የቁርአን የመጀመሪያ ምንጮች

ለእስልምና መልስ አማርኛ  ዋናው ገጽ