የቁርዓኑ አላህ የመጽሐፍ ቅዱሱ እግዚአብሔር ነውን?

Sam Shamoun

ክፍል አንድ  [ክፍል ሁለት] [ክፍል ሦስት] [ክፍል አራት]

በአዘጋጁ የተቀናበረ

ይህ ጥናት እጅግ በጣም ጠቃሚ የሆነውን ጥያቄ የሚመለከት ነው:: በቁርዓን ላይ የሙስሊሞች አላህ የክርስትያኖቹ እግዚአብሔር ተደርጎ ነው የቀረበው፡፡ ታዲያ ጥያቄው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተገለጠው እግዚአብሔር የሙስሊሞቹ አላህ ነው ወይ? የሚል ነው፡፡ ቁርአን የሚናገረው የእስላም አምላክ አላህ፣ በእርግጥ የአብርሃም አምላክ እንደሆነ ነው፡፡ ስለዚህም በቁርዓን አመለካከት መሰረት የሙስሊሞች አላህ የመጽሐፍ ቅዱሱ አምላክ ማለትም ያህዌ - ኤሎሂም ነው ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ይህ እርግጥ ነውን?

አላህ የመጽሐፍ ቅዱሱ ያህዌ ነው በማለት ቁርዓን ስለሚናገር አይሁዶችና ክርስትያኖች ይህ እውነት ነው በማለት መቀበል እንዳለባቸው ማሰብ ይኖርብናልን? ወይንስ የአላህን ተፈጥሮና አስተዋፅዖ (ባህርያት) በመመርመርና በማጥናት ከመጽሐፍ ቅዱሱ እግዚአብሔር ባህርያትና ተፈጥሮ ገለፃ ጋር እናነፃፅረዋለንን? ከዚያም ትክክል መሆን አለመሆኑን እናረጋግጣለንን?

የዚህ የምርመራ ሂደት እጅግ በጣም አስፈላጊና ጠቃሚም ነው ምክንያቱም የእኛ ዓላማ የእውነተኛውን የእግዚአብሔርን ባህርያት ማወቅና መረዳት ነውና፡፡ የዚህም ጥናት ውጤት በትክክል የሚያሳየን ከዚህ ዓለም የሕይወት ፍፃሜ በኋላ የሚሆነውን የሰውን ዘላለማዊ መጨረሻን የሚወስን ሆኖ ነው፡፡ ለማንኛውም አላህ የአብርሃም አምላክ ሆኖ ከተገኘ አይሁዶችና ክርስትያኖች ሁለቱም ስህተት ስለሆኑ እስልምናን መቀበል ይኖርባቸዋል፡፡ ነገር ግን አላህ የመጽሐፍ ቅዱሱ እግዚአብሔር ካልሆነ ደግሞ ሙስሊሞች አላህ በሚል ስም የሚያመልኩት የመጽሐፍ ቅዱሱን አምላክ ሳይሆን ሌላ ነው ማለት ነው፡፡

ስለዚህም በቁርዓን ውስጥ ስለ አላህ የተጠቀሱትን ባህርያት እንመረምርና ከመጽሐፍ ቅዱሱ ያህዌ ጋር በማነፃፀር ማስረጃው ወዴት እንደሚመራን እናያለን፡፡ እዚህ ጋ የምናደርገው ነገር በቁርዓን ላይ እንደተጻፈው፤ አላህን ከመጽሐፍ ቅዱሱ እግዚአብሔር ጋር ማነፃፀር ነው እንጂ የመጽሐፍ ቅዱሱን እግዚአብሔርን በቁርዓን ላይ ከተጻፈው አላህ ጋር ማነፃፀር አይደለም፡፡ ምክንያቱም ከመጽሐፍ ቅዱሱ እግዚአብሔር ጋር ተመሳሳይ የሆነን አምላክ እንደሚያመልክ የሚናገረው እስልምና ነውና፡፡ ስለዚህም (በዚህ አካሄድ) ሙስሊሞች (እንዲያደርጉ) የሚጋበዙት የዚህን አቀራረብ አካሄድ በማስተዋል የመጽሐፍ ቅዱሱ እግዚአብሔር የእነሱ አምላክ መሆኑን በቂ ማስረጃን ማቅረብ ማስረዳት ነው፡፡ የዚህም ሃላፊነቱ የሚወድቀው በራሳቸው ላይ ነው፡፡

(የአዘጋጁማስታዎሻ፡- ይህ የሳም ሻሞን ጽሑፍ ለአማርኛ አንባቢዎች በተለያዩ ክፍሎች ተከፋፍሎ ነው የቀረበው፡፡ ስለሆነም አጠቃላይ ትምህርቱን ለማግኘት አንባቢ ተከታታይ ከፍሎቹን በሙሉ ማንበብ ይኖርበታል)፡፡

አላህ የክፉ ምንጭ ወይንም ጀማሪ ነው፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ማንንም በክፉ እንደማይፈትን ያስተምራል ክፉ የሚለውም ቃል ሞራላዊ ያልሆነ ነገርንና ኃጢአትን የሚያስረዳ ነገር ነው፡፡ ለምሳሌም በያዕቆብ 1.13 ‹ማንም ሲፈተን፤ በእግዚአብሔር እፈተናለሁ አይበል፤ እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንምና፤ እርሱ ራሱስ ማንንም አይፈትንም።› እንዲሁም በተመሳሳይ ጥቅሶች በመዝሙር 5.4-5 ‹አንተ በደልን የማትወድድ አምላክ ነህና፤ ክፉ ከአንተ ጋር አያድርም። በከንቱ የሚመኩ በዓይኖችህ ፊት አይኖሩም፤ ክፉ አድራጊዎችን ሁሉ ጠላህ።› በዕንባቆም 1.13 ላይ ደግሞ ‹ዓይኖችህ ክፉ እንዳያዩ ንጹሐን ናቸው፥ ጠማምነትንም ትመለከት ዘንድ አትችልም፤ አታላዮችንስ ለምን ትመለከታለህ? ኃጢአተኛውስ ከእርሱ ይልቅ ጻድቅ የሆነውን ሲውጠው ስለ ምን ዝም ትላለህ?› የሚሉትን እና የእግዚአብሔርን ድንቅ ባህርይ የሚያሳዩትን ጥቅሶች እናነባለን፡፡

ነገር ግን በአንፃሩ ቁርዓን የሚያስተምረው አላህ የሚባለው አምላክ የክፋት ምንጭ እንደሆነ ነው፡፡ ይህም በሚከተሉት ሰባት ጥቅሶች ውስጥ ይገኛል፡ ‹መናፍቃን አላህን ያታልላሉ እርሱም አታላያቸው ነው፡፡ (ይቀጣቸዋል) ወደ ሶላትም በቆሙ ጊዜ ታካቾች ሰዎችን የሚያሳዩ ኾነው ይቆማሉ አላህንም ጥቂትን እንጂ አያወሱም› 4.142፤ ‹(አይሁዶችም) አደሙ አላህም አድማቸውን መለሰባቸው አላህም ከአድመኞች ሁሉ በላጭ ነው› 3.54፤ ‹የአላህንም ማዘናጋት አይፈሩምን? የአላህንም ማዘናጋት ከከሳሪዎች ሕዝቦች በስተቀር የሚተማመን የለም፡፡› 7.99፡፡ ‹እነዚያም የካዱት ሊያስሩህ ወይም ሊገድሉህ ወይም (ከመካ) ሊያስወጡህ ባንተ ላይ በመከሩብህ ጊዜ (አስታውስ) ይመክራሉም አላህም ተንኮላቸውን ይመልስባቸዋል አላህም ከመካሪዎቹ በላይ ነው› 8.30፡፡ ‹ሰዎችንም ካገኛቸው ጉዳት በኋላ እዝነትን (ዝናምና ምቾትን) ባቀመስናቸው ጊዜ ወዲያውኑ ለነሱ በታምራቶቻችን (በማላገጥ) ተንኮል ይኖራቸዋል አላህ ቅጣተ ፈጣን ነው መልክተኞቻችን የምትመክሩትን ነገር በእርግጥ ይጽፋሉ በላቸው› 10.21፡፡ ‹እነዚያም ከነሱ በፊት የነበሩት በእርግጥ መከሩ አዘንግቶም የመያዙ ዘዴ በሙሉ የአላህ ነው ነፍስ ሁሉ የምትሠራውን ያውቃል ከሐዲዎችም የመጨረሻይቱ አገር ለማን እንደምትኾን ወደፊት ያውቃሉ› 13.42፡፡ ‹ተንኮልንም መከሩ እነርሱም የማያውቁ ሲኾን በተንኮላቸው አጠፋናቸው› 27.50፡፡ በአረብኛ ማታለል የሚለው ቃል ‹ማካራ› የሚል ሲሆን ትርጉሙም የሚያሳየው አሳሳችነት ነው፣ ማለትም አንድ በምስጢር ክፉን ስራ ለመስራት የሚቀምር ማለት ነው፡፡ ቃሉም ሁልጊዜ የሚያገለግለው ለክፉ ነገር ብቻ ነው፡፡ ስለዚህም በቁርዓን ውስጥ አላህ የሚታየው እንደ ተዋጣለት አታላይ የአጭበርባሪዎች ወይንም የአታላዮች ጀማሪ ወይንም የማታለል ምንጭ እንደሆነ ነው፡፡

እንዲህ ዓይነቱ አገላለጥ ለእግዚአብሔር ሲሰጥ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በምንም መልኩ ተቀባይነት የሌለው ነገር ነው፡፡ ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ ያሉትም የሙስሊም ሊቃውንት ይህንን እውነታ ይቀበሉታል፡፡ ለምሳሌም የሚከተለውን እንመልከት፡-

ዶ/ር መሐመድ አዩብ [Dr. Mahmoud M. Ayoub in his book, The Quran and Its Interpreters, Vol. II The House of Imran,] በሚለው መጽሐፉ ውስጥ የሚከተለውን ጥያቄ አነሳ ‹ማካር የሚለውና (ማጭበርበር ወይንም ክፉን ነገር ማቀድ) ክፉነትን ወይንም አለመታመንን የሚያመለክተው ቃል ለእግዚአብሔር ሊሰጥ ይችላልን? (Ibid. [1992 State University of New York Press, Albany], p. 165)፡፡ ቀጥሎም እጅግ ብዙ የሚሆኑ የሙስሊም ምንጮችን ከዘረዘረ በኋላ የጠቀሰው ‹መዶለት (መካር) በእርግጥ የማታለል ስራ (ድርጊት) ሲሆን ያነጣጠረውም ክፉን ነገር በማምጣት ላይ ነው፣ በመሆኑም እንደዚህ ዓይነትን ባህርይ ለእግዚአብሔር መስጠት ደግሞ በፍፁም የማይቻል ነው፡፡ ስለዚህም መሆን የሚችለው ቃሉ ብዙ ትርጉም ያለው መሆኑ ነው› በማለት ገለጣ ሰጥቶበታል፡፡ ይህንንም በተመለከተ በመጽሐፉ በገጽ 166 ውስጥ የሰፈረው የአር-ራዚን አባባል ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የሚቀጥለው የቁርዓን 8.30 የቀደመ ትርጉም የሚናገረው እንደሚከተለው ነው ‹እነዚያም የካዱት ሊያሴሩብህ ወይም ሊገድሉህ ወይም (ከመካ) ሊያስወጡህ ባንተ ላይ በመከሩ ጊዜ (አስታውስ) ይመክራሉም አላህም ተንኮላቸውን ይመልስባቸዋል አላህም ከመካሪዎቹ ሁሉ በላይ ነው› ከዚያም ሕዝቡ እሱን ሊገድሉት በመከሩበት ጊዜ አላህ ለሐዋርያው እንደሚያደላ አስታውሶት የተናገረው ነገር እነሱ በእሱ ላይ ሊገድሉት ወይንም ሊያቆስሉት ወይንም ከከተማ ሊያሰውወጡት ማሴራቸውን ነገር ግን አላህ ደግሞ አሴረባቸው እሱም ከሚያሴሩ ሁሉ የበለጠ ሴረኛ ነው በማለት ነው፡፡ ማለትም አላህ የሚለው፡- ‹እኔ እነሱን በእኔ የበለጠ ተንኮል አታልያቸዋለሁ ይህም ከእነሱ እጅ አንተን አድንህ ዘንድ ነው፡፡› ሕዝቡ ሊገድሉት በተማከሩበትና ባሴሩበት ጊዜ፡፡ (The Life of Muhammad: A Translation of Ibn Ishaq's Sirat Rasul Allah, with introduction and notes by Alfred Guillaume [Oxford University Press, Karachi, Tenth impression 1995], p. 323;)

በእርግጥ አላህ ክፉን ነገር ለመስራት የተጠቀመባቸውን እጅግ ብዙ ምሳሌዎችን እና አንዳንድ መንገዶችን ቁርዓን በትክክል ይሰጣል፡፡ በቁርአን 8.43 ላይ አላህ እስላሞችን የሚዋጉትን ተዋጊዎች ቁጥር ለመሸወድ በሕልም ጥቂት አድርጎ በማሳየት ጠላቶቻቸውን እንዳይፈሩ አድርጓቸዋል እንዲህ ዓይነትም ማታለል (መሸወድ) አላህ የተጠቀመው ሙስሊሞች ስለ እሱ ሳይፈሩ እንዲዋጉ ነበር፡፡ ቀጥሎም ደግሞ በ17.16 ውስጥ ደግሞ ‹ከተማንም ለማጥፋት በፈለግን ጊዜ ባለ ጸጋዎችዋን እናዛለን በውስጧም ያምጣሉ በርሷም ላይ ቃሉ (ቅጣቱ) ይፈጸምባታል ማጥፋትንም እናጠፋታለን› ይህም የሚያሳየው አንድ ከተማን ሙሉ ለሙሉ ለማጥፋት አላህ ሆነ ብሎ ሕዝቡን ኃጢአትን እንዲሰሩ እንደሚያዛቸው ነው፡፡ ቀጥሎም በ34.13-14 ላይ ደግሞ አላህ ጅኒዎችን ለሰለሞን ስራ እንዲሰሩ እንዳደረጋቸው እሱም በሞተ ጊዜ ሞቱን ሳያውቁ ስራውን እንዲቀጥሉ እንዳታለላቸው ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አይሁድንም ክርስትያኖችንም እንኳን ኢየሱስ ሞተ ብለው እንዲያምኑ ያታለላቸው አላህ ነው፡፡ 4.157 ‹እኛ የአላህን መልክተኛ መርየምን ልጅ አልመሲህ ዒሳን ገደልን በማለታቸው (ረገምናቸው) አልገደሉትም አልሰቀሉትም ግን ለነሱ (የተገደለው ሰው በዒሳ) ተመሰለ እነዚያንም በርሱ ነገር የተለያዩትን ከርሱ (መገደል) በመጠራጠር ውስጥ ናቸው ጥርጣሬን ከመከተል በስተቀር በርሱ ነገር ምንም ዕውቀት የላቸውም በእርግጥ አልገደሉትም›፡፡ በ9.51 መሰረት ደግሞ የተነገረን ነገር ‹አላህ ለኛ የጻፈልን (ጥቅም) እንጂ ሌላ አይነካንም እርሱ ረዳታችን ነው፡፡ በአላህ ላይም ምእምናን ይመኩ በላቸው›፡፡ ይላል እንዲሁም ደግሞ በ14.4 ላይ ‹ከመልክተኛም ማንኛውንም ለነርሱ ያብራራላቸው ዘንድ በወገኖቹ ቋንቋ እንጂ በሌላ አልላክንም አላህም የሚሻውን ያጠማል (ጠማማ ያደርጋል) የሚሻውንም ያቀናል አሸናፊም ጥበበኛም ነው፡፡› ይላል፡፡

እንዲሁም ደግሞ በ7.178-179 እና 186 ላይ የሚከተለውን እናነባለን ‹አላህ የሚያቀናው ሰው ቅን እርሱ ነው የሚያጠመውም ሰው እነዚያ ከሳሪዎቹ እነሱ ናቸው፡፡ ከጋኔንም ከሰዎችም ብዙዎችን ለገሃነም በእርግጥ ፈጠርን ለነርሱ በርሳቸው የማያውቁባቸው ልቦች አሏቸው ለነሱም በሳቸው የማያዩባቸው ዓይኖች አሏቸው ለነሱም በሳቸው የማይሰሙባቸው ጆሮዎች አሉዋቸው እነዚያ እንደ እንስሳዎች ናቸው ይልቁንም እነርሱ በጣም የተሳሳቱ ናቸው እነዚያ ዘንጊዎቹ እነርሱ ናቸው፡፡› ደግሞም በቁጥር 186 ‹አላህ የሚያጠመው ሰው ለርሱ ምንም አቅኝ የለውም በጥመታቸውም ውስጥ እየዋለሉ ይተዋቸዋል›፡፡ ደግሞም 11.118-119 ላይ ‹ጌታህም በሻ ኖሮ ሰዎችን ሁሉ አንድ ሕዝብ ባደረጋቸው ነበር የተለያየም ከመኾን አይወገዱም፡፡ ጌታህ ያዘነለት ብቻ ሲቀር (ከመለያየት አይወገዱም) ለዚሁም ፈጠራቸው የጌታህም ቃል ገሃነምን ከአጋንንትና ከሰዎች ከሁሉም በእርግጥ እሞላታለሁ በማለት ተፈጸመች፡፡› እነዚህ ነገሮች በሙስሊም ባሕላዊ አገላለጥ የሚከተለው ትንታኔ ተሰጥቷቸዋል፡ በተለይም ከዚህ በላይ የተጠቀሰውን 17.16 በተመለከተ ተንታኝ አቡ ሁራይራ የሚከተለውን ተናግሯል፡ በእርግጥ አላህ የወሰነው ሰው የሚገባበት ዝሙት ስራ እሱ የግድ የሚያደርገው ነው (ወይንም ከዚያም ምንም ማምለጫ አይኖርም) ሳሂህ ሙስሊም፡፡ አላህ ሰዎችን ዝሙትን እንዲያደርጉ ያደርጋል ብሎ መገመት እጅግ አስፀያፊ ብቻ ሳይሆን የአላህን ደረጃ የሙሴ አምላክ ከመሆን በጣም ዝቅ ያደርገዋል፡፡

አንድ አስተዋይ የሆነ አንባቢ እዚህ ጋ መጽሐፍ ቅዱስም እራሱ በተለያዩ ቦታዎች ላይ በአንዳንድ ሰዎች ለምሳሌም አቤሴሎም ላይ 2ሳሙኤል 17.14 እና አገሮች ላይ ክፉን ነገር ለማድረግ እንዳቀደ ኤርምያስ 20.7 ሊጠቅስና ሊቃወም ይችላል፡፡ ቀደም በማለት እንደተናገርነው እግዚአብሔር ማንንም በክፉ ወይንም በሞራል ኃጢአት አይፈትንም ነገር ግን ሰዎችን በኃጢአታቸው የተነሳ ይፈርድባቸዋል ወይንም ያጠፋቸዋል ይህ ነው በአቤሴሎምም ላይ በግልጥ ሲሆን የምንመለከተው 2ሳሙኤል 17.14 ስለዚህም ‹ክፉ ያመጣ ዘንድ› በሚለው ውስጥ ያለው ቃል ‹ክፉ› በሒብሩ ቋንቋ ትርጉም ‹መስበር፣ ማድቀቅ› የሚል ነው፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር በእነዚህ ሰዎች ላይ ያመጣው ክፉ በቁርአን ላይ እንደተጠቀሰው ዓይነት የስነ ምግባር ጉድለት እንደ ዝሙት ዓይነት ሳይሆን እነሱ ወደ ንስሀ ለመምጣት በመቃወማቸው መሠረት ስለሚያመጣባቸው ፍርድና ቅጣት የሚናገር ነው፡፡ ኤርምያስ 20.7 ላይ ያለው ደግሞ አሁንም ቃሉ ከመነጨበት ከሒብሩ ቋንቋ ስናስተውለው የሚለው ‹ማባበል፣ ማሳደግ፣ መሳብ፣ ማታለል፣ ማሳመን፣ ማሞኘት› ሁሉ የሚያካትት ነው፡፡ በእነዚህም እጅግ በጣም ብዙ በሆኑት የቃሉ ትርጉሞች እውነታ አኳያ ኤርምያስ እግዚአብሔር አታለለኝ ማለቱ ሊሆን እንደማይችል መገመት አያስቸግርም፡፡ በእርግጥ ዓውዱ የሚያሳየው እውነታ የሚሆነው ‹ማሳመን› ማለት እንደሆነ ነው ምክንያቱም ኤርምያስ እያጉረመረመ ነው፡፡ ኤርምያስ ባይፈልግም እግዚአብሔር ግን አገልግሎቱን እንዲቀጥል ስላሳመነው ነው፡፡ ይህም ከሚቀጥለው 8-9 ቁጥሮች ላይ ግልፅ ነው የሚሆነው፡፡ አዎ! እግዚአብሔር ኤርምያስ አገልግሎቱን እንዲቀጥል እንዳሳመነው ግልጥ ነው፡፡ ስለዚህም ይህ ክፍል እግዚአብሔር አታላይ ነው ይላል ብሎ ለመናገር በፍፁም አያስኬደንም፡፡

ሌላው ተቃውሞ ደግሞ ሕዝቅኤል 20. 25 ላይ ያለው ነው ‹ደግሞም መልካም ያልሆነውን ሥርዓት በሕይወት የማይኖሩበትንም ፍርድ ሰጠኋቸው›፡ ይህ ቃል እግዚአብሔር የክፋት ጀማሪ እንደሆነ በጣም የሚጠቁም ይመስላል፡፡ ነገር ግን የቃሉ ዓውድ ሲታይ እስራኤል የእግዚአብሔርን ቅዱስ ትዕዛዛት ላለማድረግ እጅግ በጣም የሚያመነቱበት ጊዜ ነበር ይህም እግዚአብሔር ለሚመኙት ነገር አሳልፎ እንዲሰጣቸው አድርጎታል፡፡ በመሆኑም ምዕራፍ 20 በሙሉ የሚያሳየው ይህንን ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጥ የሚያስተምረው አንድ ሕዝብ የተገለጠለትን እውነት ተቀብሎ መኖርን እንቢ ባሉበት ጊዜ ልባቸው እንዲጠነክር እና በእርኩሰታቸው ቀጥለው ፍርድን እንዲቀበሉ እግዚአብሔር እንደሚተዋቸው ነው፡፡ ይህም በእነሱ ላይ የሚያመጣው ፍርድ በክፉ ስራቸው የሚገባቸው መሆኑን ለማሳየት ነው፣ እንዲህ ዓይነቱ እውነት በሮሜ 1.18-32 በ2ተሰሎንቄ 2.9-12 ላይ በግልጥ ተጠቅሷል፡፡

ስለዚህም ለሰዎች እንዲኖሩበት ያልተቀደሰ ትዕዛዝን እና ሕግን ክፉንም ነገር እግዚአብሔር በፍፁም አልሰጣቸውም፡፡

ነገር ግን የአረብኛው ‹ማካራ› ሌሎች ትርጉሞችን እንድናስብ የሚፈቅድ ቃል አይደለም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ቁርአን እራሱ አላህ ፈቃዱን ለማሟላት ማጭበርበርን እንደሚጠቀም ብዙ ምሳሌዎችን ይሰጣል፡፡ ታዲያ የቁርአኑ አላህ የመጽሐፍ ቅዱሱ እግዚአብሔር ነው ለማለት ይቻላልን? በፍፁም የሚቻል አይደለም፡፡ በራሱ በቁርአን መሰረት አላህ ከመጽሐፍ ቅዱሱ እግዚአብሔር የተለየ ባህሪ ያለው ነው፡፡

የአዘጋጁ ማሳሰቢያ፡-

ከዚህ በላይ በሳም ሻሞን በቀረበው ጥናት መሰረት በአላህ ባህርይና በእግዚአብሔር ባህርያት መካከል ከፍተኛ ልዩነት መኖሩን በትክክል አይተናል፡፡ በመሆኑም የመጽሐፍ ቅዱሱ እግዚአብሔር የቁርአኑን አላህ ሊሆን እንደማይችል ነው፡፡ አንባቢ ሆይ! ከዚህ በላይ ያሉትን እውነተኛ ንፅፅሮች በሚገባ አይተሃል፡፡ የመጽሐፍ ቅዱሱና እውነተኛው እግዚአብሔር፣ እውነተኛ አምላክ ነው እሱ ለሰዎች ልጆች የሚያስብና ቅዱስ ደግሞም እውነተኛ ነው፡፡ ሰዎች በኃጢአታቸው የተነሳ የሚጠብቃቸውን ቅጣት ተሸክሞ ስለ ሰዎች ምትክ ሆኖ እንዲሞት በላከው በጌታ በኢየሱስ ላይ ቅዱስ የፍርድ ቁጣውን አፈሰሰው፡፡ ጌታ ኢየሱስም ለሰዎች ኃጢአት መስዋዕትን ከፈለ፡፡ ኃጢአተኝነት የዘላለም የገሃነም ፍርድ የሚጠብቀው ነው፡፡ ነገር ግን ዛሬ ሳይዘገይ ወደ ጌታ ኢየሱስ መምጣት እና ንስሐ በመግባት በእርሱም ላይ በመታመን የኃጢአት ይቅርታ ማግኘት ይቻላል፡፡ ይህንንም ያደረጉ ከዘላለም ሞት ወደ ዘላለም ሕይወት የተሻገሩበትን ለውጥና ይቅርታ በተግባር በሕይወታቸው ውስጥ ሲፈልቅ አይተዋል፡፡ አንተም የዚህ እውነት ተካፋይ መሆን ትችላለህ፣ ተከታታይ ጽሑፎችን አንብብና በማስተዋል አስበህ ወደ ጌታ ኢየሱስ በንስሐ እንድትመጣ እንጋብዝሃለን፣ እግዚአብሔር ይርዳህ አሜን፡፡

ወደ ክፍል ሁለት ይቀጥሉ::

 

የትርጉም ምንጭ: IS ALLAH THE GOD OF BIBLE?

 ለእስልምና መልስ አማርኛ  ዋናው ገጽ