የቁርዓኑ አላህ የመጽሐፍ ቅዱሱ እግዚአብሔር ነውን?

Sam Shamoun

[ክፍል አንድ[ክፍል ሁለት] [ክፍል ሦስትክፍል አራት

በአዘጋጁ የተቀናበረ

አላህ የታሪካዊ ስህተቶችን ፈጣሪ

ቁርዓን ብዙ የሆኑ ታሪካዊ ስህተቶችን የያዘ መጽሐፍ ነው፡፡ ይህም የሚያሳየው የሙስሊሞች አላህ ‹ሁሉን አዋቂ› አለመሆኑን ነው፣ ምክንያቱም ሁሉን የሚያውቅ አምላክ ታሪካዊ ክስተቶችን በትክክል መናገር ይችላልና፡፡ ከዚህ በታች ያሉት በቁርዓን ውስጥ ከተገኙት ስህተቶቸ በጣም ጥቂቶቹ ናቸው፡-

በቁርዓን 17.1 ላይ መሐመድ እሩቅ ወደ ሆነው መስጊድ እንደተወሰደ ነው የተነገረው። መስጊዱም ‹ማሲድ አል-አክሳ› ነው፡፡ ይህ የተጠቀሰው መስጊድ በ691 ዓ.ም አብደላ ማሊክ እስገነባው ድረስ በመሐመድ ወቅት ያልነበረ መሆኑ ላይ ነው ችግሩ፡፡ እንዲሁም ደግሞ የኢየሩሳሌም ቤተመቅደስ ነው በማለትም መናገርም አይቻልም ምክንያቱም በ70 ዓ.ም በሮማውያን ጦር ሰራዊት ሙሉ ለሙሉ ፈርሶ ነበርና፡፡

በቁርዓን 18.9-26 ደግሞ ብዙ ሰዎችና ውሻ በግምት ለሦስት መቶ ዘጠኝ ዓመታት ያህል በዋሻ ውስጥ እንዳንቀላፉና በነበሩበት ሁኔታ እንደነቁ ነው፡፡

በቁርዓን 18.83-98 ላይ ደግሞ ታላቁ አሌክሳንደር ዙልቀርነይን ‹ሁለት ቀንድ ያለው ሰው› ተብሎ እንደተጠራና እሱም ሙስሊም የነበረ ሰውና ፀሐይ በአካል በጭቃማ ምንጭ ውስጥ ስትጠልቅ እንዳየ ተዘግቧል፡፡ ‹ሁለት ቀንድ ያለው ሰው› የሚለውን በአዕምሮአችን ስናስብ ይህ መጠሪያ ከቅድመ እስልምና በፊት ለታላቁ አሌክደሳደር ተሰጥቶ የነበረ ስም መሆኑን እናስተውላለን፣ ብዙዎቹ ሙስሊሞችም ይህንን እውነት ለመካድ ያደረጉት ጥረት ሙሉ ለሙሉ ከሽፏል፡፡

በቁርዓን 4.157 መሠረት የማያምኑት አይሁዶች ‹የመርየምን ልጅ የአላህን ሐዋርያ አልመሲህን ኢሳን ገደልነው› ብለው እንደፎከሩ ተገልጧል። በዚህም ላይ ያለው ችግር አይሁዶች ኢየሱስን መሲህ ነው ብለው ያልተቀበሉ መሆናቸው ነው፡፡ እንዲሁም እሱን መሲህ ነው ብለው ቢያምኑ ኖሮ ሊገድሉት አይችሉም ነበር፡፡ ለብዙ ጊዜ ይጠብቁት የነበረው እሱን አዳኛቸውን ነበርና፡፡ የማያምኑት አይሁዶቸ ኢየሱስን የገደሉት የሐሰት ነቢይ ነው ብለው አስበው ነበርና ነው፡፡ ለዚህም ማስረጃው የከሰሱት ክስ ነው፡፡ ‹ይህ ሕዝባችንን ሲያጣምም ለቄሣርም ግብር እንዳይሰጥ ሲከለክል ደግሞም። እኔ ክርስቶስ ንጉሥ ነኝ ሲል አገኘነው ብለው ይከሱት ጀመር።› ሉቃስ 23.2

ክርስትያኖች ማርያምንና ኢየሱስን ከእውነተኛው አምላክ ጋር እንደ ተጨማሪ ሁለት አምላኮች እንደሚያመልኩ ተወንጅለው ነበር፡፡ ‹አላህም፡- የመርየም ልጅ ዒሳ ሆይ አንተ ለሰዎቹ እኔንና እናቴን ከአላህ ሌላ ሁለት አምላኮች አድርጋችሁ ያዙ ብለሀልን? በሚለው ጊዜ (አስታውስ) ጥራት ይገባህ ለኔ ተገቢዬ ያልኾነን ነገር ማለት ለኔ አይገባኝም ብዬው እንደ ኾነም በእርግጥ ዐውቀኸዋል በነፍሴ ውስጥ ያለውን ሁሉ ታውቃለህ ግን አንተ ዘንድ ያለውን አላውቅም አንተ ሩቆችን ሁሉ በጣም ዐዋቂ አንተ ብቻ ነህና ይላል› 5.116፡፡ እንዲሁም በ 5.75፤ 5.17፡፡

ይህም የተገመተው ማርያም ምግብን ስለበላችና በአላህ ስለምትጠፋ በምንም መንገድ መለኮት አትሆንም በሚል ሐሳብ ነው፡፡ ይህም ደግሞ ሙስሊሞች ክርስትያኖች እሷን ከሰው በላይ አድርገው ይገምቷታል ከሚል አመለካከት ያመነጩት ሐሳብ ነው፡፡

በእርግጥ ቁርዓን ክርስትያኖችን ሦስት አምላክን ያመልካሉ ብሎ መክሰሱን ቀጥሎበታል፡፡ ‹እነዚያ አላህ የሦስት ሦስተኛ ነው ያሉ በእርግጥ ካዱ ከአምላክም አንድ አምላክ እንጂ ሌላ የለም ከሚሉትም ነገር ባይከለከሉ ከነሱ እነዚያን የካዱትን አሳማሚ ቅጣት በእርግጥ ይነካቸዋል› 5.73፡፡ በተጨማሪም 4.171፡፡  

በሙስሊሞች የግለሰብ ታሪክ ጸሐፊ ኢብን ኢሻክ መሰረት በ Sirat Rasulullah በተባለው ስራው ውስጥ ናጅራን የተባለ የክርስትያኖች ተወካይ ከመሐመድ ጋር ስለ ኢየሱስ ስብዕና ሊከራከር መጣ፡፡ በጽሑፉም ውስጥ እነዚህ ክርስትያኖች እንደሚያምኑ የተጠቀሰው ኢየሱስ አምላክ እንደሆነ እንዲሁም የእግዚብሔር ልጅ እንደሆነ፤ እንዲሁም እሱ የስላሴ ሦስተኛው እንደሆነና ይህም የክርስትያኖች ዶክትሪን ነው በማለት ነው፡፡ Alfred Guilliame trans., The Life of Muhammad [Oxford University Press, Karachi], p. 271)፡፡ በመቀጠልም የተናገረው ‹እነሱም የሚናገሩት እሱ በነዚያ አምላክ ውስጥ የሦስቱ ሦስተኛ ነው፡ እኛ አድርገነዋል እኛ አዘናል እኛ ፈጥረናል እኛ ደንግገናል በማለት ነው፡፡ እነሆም እነሱ ያሉት እሱ አንድ ቢሆን ኖሮ እኔ አደረግሁት እኔ ፈጠርሁት ወ.ዘ.ተ ይል ነበር በማለት ነው፡፡ ነገር ግን እሱ፤ እሱ ነው፡፡ ኢየሱስ እና ማርያም (የሉበትም)፡፡ ስለዚህም ለእነዚህ ሁሉ ጭማሬዎች ነው ቁርዓን የመጣው የሚል ገለፃ ነው፡፡ (በተመሳሳይ መጽሐፍ ገፅ 271-272)፡፡

በቁርዓን ውስጥ ያሉት የትምህርት ስህተቶች የክርስትና እምነትን መሠረታዊ ትምህርቶችን ለሚያውቅ ማንም ሰው ግልፅ ናቸው፡፡

በመጀመሪያም፡ ክርስትያኖች ማርያምን ከእግዚአብሔር ጎን እንደ ሴት አምላክ በፍፁም ወስደዋት አያውቁም፡፡

በሁለተኛ ደረጃም፡ ክርስትያኖች እግዚአብሔር ሦስት ነው ወይንም የሦስት ሦስተኛ ነው በማለት በፍፁም ተናግረው አያውቁም ምክንያቱም ያንን ማለት በሦስት የተለያዩ አማልክት ማመን ነውና ይህም ‹ተሪይቲዝም› የሚባለው ሲሆን ሦስት የተለያዩ አማልክት አንድነትን መስርተው አንድ ሆነዋል እንደ ማለት ነው፡፡ ይህም የሥላሴን እምነት ሙሉ ለሙሉ የሚቃረን ነው፡፡ የስላሴ ትምህርት አንድ እግዚአብሔር አለ እሱም በውስጡ የማይለያዩ ግን እራሳቸውን የቻሉ ሶስት ስብዕናዎች አሉት የሚል ነው፤ እነሱም አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ናቸው፡፡

በሦስተኛ ደረጃ፡ ደግሞ ክርስትና በአስተምህሮው ውስጥ ኢየሱስን የሥላሴ ሦስተኛ አድርጎ ተናግሮ አያውቅም፡፡ ነገር ግን ሁልጊዜ የሚናገረው ኢየሱስ የሥላሴ ሁለተኛው እንደሆነና መንፈስ ቅዱስ ደግሞ ሦስተኛ እንደሆነ ነው ማቴዎስ 28.19፡፡

በአራተኛ ደረጃ ደግሞ፡ ሙስሊሞች የሚያምኑት የቁርዓኑ አላህ የመጽሐፍ ቅዱሱ እግዚአብሔር አብ ጋር አንድ እንደሆነ በመቁጠር ነው፡፡ ይህም እነሱ በእግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ ስለማያምኑ እንዲሁም ደግሞ በመንፈስ ቅዱስም አምላክነት ስለማያምኑ ነው፡፡ ምክንያቱም መንፈስ ቅዱስ ለእነሱ መልአኩ ገብርኤል ነውና፡፡ ይህም እንደገና ችግርን ያስከትላል ምክንያቱም አላህ በእርግጥ እግዚአብሔር አብን ከሆነ ቁርዓን በጣም ተሳስቶ ነው የሚገኘው ምክንያቱም በእነሱ አባባል መሠረት ክርስትያኖች እግዚአብሔር የሦስት ሦሰተኛ ነው ብለው ስለሚያስተምሩ ነው፡፡ ክርስትያኖች የሚያስተምሩት አብ የሥላሴ የአንዱና የእውነተኛ ሕያው እግዚአብሔር አንደኛው እንደሆነ ነው እንጂ የሦስት አማልክት ሦስተኛ አምላክ ነው አይሉም፡፡

በመጨረሻም፡ ደግሞ ክርስትያኖች አላህ መሲህ ነው ወይንም እግዚአብሔር መሲህ ነው ብለው አያምኑም ምክንያቱም ይህን ብሎ ማለት ኢየሱስ እራሱ ሥላሴ ነው እንደማለት ነውና፡፡ ይህም የኦንሊ ጅሰስ ዓይነት ‹ሞዳሊዝም› የተባለው የስህተት ትምህርት ነው፡፡ ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ አባባል ኢየሱስ አምላክ ነው፣ ይህም ማለት ኢየሱስ በተፈጥሮው ሙሉ አምላክም ቢሆን ነገር ግን የአምላክነትን ወይም መለኮትነት የሚይዘው እሱ ብቻውን አይደለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ አብና መንፈስ ቅዱስም እንደዚሁ ሙሉ መለኮትነት እንዳላቸው በግልጥ ያስተምራልና፡፡

ሌላው ደግሞ የኢየሱስ እናት ማርያም ከአሮን እና ከሙሴ እህት ማርያም ጋር የአምራም ልጅ ተብላ ተጠርታለች፡ 3.35.36፡፡ 66.12፡፡ 19.27-28፡፡

የአሮንና የሙሴ እንዲሁም የእህታቸው የማርያም ታሪክ ያለው በዘፀዓት 15.20ና በዘኁልቁ 27.59 ውስጥ ነው፡፡ ይህ የ1400 ዓመታትን ታሪክ የዘለለ ስህተት ነው! እንዴት ሆኖ ነው የሙሴ እህት ማርያም የኢየሱስ እናት ሆና ሙሴን የኢየሱስ አጎት የምታደርገው?

ለዚህም ውስብስብ የስህተት ጥያቄ ሙስሊሞች ሁለት ዓይነትን ምላሽ ይሰጣሉ፡፡ አንደኛ የአሮን እህት የሚለው አባባል እና የአምራም ልጅ የማርያምን የዘር ሐረግ ነው የሚያመለክተው ማለትም ማርያም የአሮንና የአምራም ዘር የሌዊ ነገድ ናት ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ለሙስሊሞች በምንም መንገድ ሊያኬድ አይችልም ምክንያቱም ማርያም የይሁዳ ልጅ የዳዊት ዘር ናትና ሉቃስ 3.23፣31፣33፡፡

እንደመሰላቸውም የሚለው ቃል የተሰጠው የማርያምን ዘር ለማብራራት ነው ይህም በዮሴፍ የወንድ ዘር ወኪል ተደርጎ ነው የቀረበው፡፡ ይህም ደግሞ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ በሆኑ ማስረጃዎች በሚገባ ድጋፍ ያለው ነው ለምሳሌም እንደ አይሁድ የታልሙድ ጽሑፎች ውስጥ በግልጥ ይገኛልና፡፡ በዕብራውያን መጽሐፍ ውስጥ ደግሞ የነገረን ነገር ‹ጌታችን ከይሁዳ ነገድ እንደወጣ የተገለጠ ነውና፥ ስለዚህም ነገድ ሙሴ ምንም እንኳ ስለ ክህነት አልተናገረም፡፡› ዕብራውያን 7.14፡፡ እንዲሁም ደግሞ ራዕይ 22.16፡፡ ስለዚህም ማርያም የሌዊ ዝርያ በፍፁም ልትሆን አትችልም፡፡ የእውነተኞች የአይሁድ አረዳድ በአዲስ ኪዳን እንደተጻፈው ከመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ጋር ሙሉ በሙሉ ይስማማልና፡፡ ዘፍጥረት 49.10-12 እና ማቴ 22.42-45፡፡

አንድ ሰው በዚህ ነጥብ ላይ ኤልዛቤጥ የማርያም ዘመድ ተብላ አልነበረምን? በማለት ጣልቃ ገብቶ ጥያቄን ሊያነሳ ይችል ይሆናል ሉቃስ 1.36፡፡ ይህም ማርያም የሌዊ ዝርያ ያላት ያስመስላል ምክንያቱም የኤልዛቤጥ ዝርያ ሌዋዊ እንደሆነ ተጠቅሷልና በሉቃስ 1.5፡፡ እዚህ ጋ ለዘመድ የተጠቀሰው የግሪክ ቃል ትርጓሜ፡

ሀ. ቅፅል ሲሆን፡- የሚያሳየው የአንድን ሰው ተመሳሳይ ፍጥረት ነው ማለትም ከተመሳሳይ ቤተሰብ መምጣትን ዘር ጎሳ ወይንም ሕዝብን ማለትን ነው፡፡ ስለዚህም ሊተረጎም የሚችለው በተፈጥሮ ዝምድናን ወይንም አንድ ዓይነት ወይም ተመሳሳይ ማለትን ነው፡፡

ለ. ስም ሲሆን፡- ደግሞ የሚያመለክተው በዝምድና ዝርያን ወይንም በተፈጥሮም ማለት ሲሆን ሰፋ ያለ መመሳሰልን ነው (ለምሳሌም ያህል አምላክነትና ሰውነትን ወይንም ሐሳብንና ስሜትን ወይንም የከዋክብትንና የሰውን ፍፃሜን) ይህም በፊሎሶፊና በታዋቂ እምነት ጥቅም ላይ እንደዋለው ነው፡፡ (Theological Dictionary of the New Testament,)

ስለዚህም ኤልዛቤጥ እና ማርያም ዝምድናቸው በተመሳሳይ ሕዝብ ውስጥ በመሆን ስሜት ውስጥ ነው ማለትም እስራኤላዊ በመሆን ነው፡፡ ነገር ግን ይህ አካሄድ የሚያዋጣ አይመስልም ምክንያቱም የማንኛዋንም እስራኤላዊት ሴት ከማርያም ጋር ዝምድናን የሚጠቁም ይመስላልና፡፡ ነገር ግን በጣም አሳማኝ የሚመስለው ኤልሳቤጥና ማርያም የስጋ ዝምድና እንዳላቸው ነው፡፡ ይህም ማለት ደግሞ ማርያም የሌዊ ነገድ ደግሞም የአሮን ዘር ናት ወደሚል መደምደሚያ ሊያመጣን አይችልም፡፡ ይህ ሁሉ የሚያስረዳው ኤልሳቤጥ የአይሁዳዊ ደም በዘሯ እንደነበራት ነው ምክንያቱም ሌዋውያን ከየትኛወም የእስራኤል ነገድ እንዲጋቡ ይፈቀድላቸው ስለነበር ሌዋውያን 21.13-14፡፡ የሕዝቅኤል የካህናቱ እና የቤተመቅደሱ መታደስ ራዕይ ይህንን በበለጠ ያብራራዋል ሕዝቅኤል 44.22፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህም ምሳሌ የሚሆንን የአንድን ካህን ከዳዊት ዘር ከሆነች አይሁዳዊ ሴት ጋር መጋባትን ይሰጠናል 2ዜና 22.10-11፡፡

ስለዚህም ይህ አካሄድ የሚያሳየው የኤልሳቤጥ እናት ከዳዊት ወገን ሆና ከይሁዳ ነገድ ከማርያም ጋር ዝምድና አገኙ ማለት ነው፡፡ ኤልሳቤጥ ስለዚህም የማርያም አክስት ነበረች፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ስለ ሉቃስ 1.36 የተሰጡ ማብራሪያዎችን ብትመልከቱ ነገሩም ግልጥ ይሆናል፡፡

ሙስሊሞች ‹የ - ወንድም› የሚለውን ሐረግ በመውሰድና በመጠቀማቸው በጣም ሊወቀሱ አይገባቸወም ምክንያቱም መሐመድም የእራሱን ስህተት ለመሸፈን ተመሳሳይን መከራከሪያ ይጠቀም ነበርና ይህንንም በ Sahih Muslim Mughirah ibn Shu'bah ላይ እንደሚከተለው ተርኮታል

‹ወደ ናጅራን በመጣሁ ጊዜ (የናጅራን ክርስትያኖች) እንዲህ ብለው ጠየቁኝ፡ አንተ የአሮንን እህት ማርያምን በቁርዓን ውስጥ አነበብካት ነገር ግን ሙሴ ከኢየሱስ እጅግ በጣም ድሮ ነው የተወለደው፡፡ እኔም ወደ አላህ መልክተኛ ተመልሼ ስመጣ ይህንኑ ጥያቄ ጠየቅሁት እሱም ‹(የጥንት ሰዎች) ስምን ይሰጡ የነበረው (ለእራሳቸው ሰዎች) ነበር ይህም በሐዋርያት ስም እና በጣም ሃይማኖተኛ ለነበሩትና በፊት በኖሩት ነው፡፡ (በማለት መለሰ)፡፡ ቁጥር 5326፡፡

እንደገናም ደግሞ፡ ‹የእግዚአብሔር ነቢይ ወደ ናጅራን ሰዎች ላከኝ፡፡ እነሱም ምን እንዳነበብክ ታያለህን አሉኝ? ሙሴ ከኢየሱስ እጅግ ብዙ ዓመት በፊት የነበረ ሲሆን የአሮን እህት ሆይ ብለህ አነበብህ? እሱም (አል ሙጂራህ) እንዲህ አለ፡ እኔም ወደ ነቢ ተመልሼ ይህንኑ ነገርኩት፡፡ እሱም ‹ሰዎች ከነቢያቶቻቸውና ከእነሱ በፊት በነበሩት ቅዱሳን ሰዎች ስም እንደሚጠሩ ንገራቸው አለኝ› Jalaaluddeen As-Suyuti, Ad-durr Al-Manthur፡፡

በመሐመድ ዓረፍተ ነገር ውስጥ ያለው ችግር በክርስቶስ ጊዜና በፊት የነበሩት እንደዚህ እሱ እንደሚለው ዓይነትን ሐረግ በፍፁም ተጠቅመው እንደማያውቁ ነው፡፡ የዚህን የመሐመድን አባባል የሚደግፍ ምንም ዓይነት የሆነ ብሉይ ኪዳናዊ ወይም አዲስ ኪዳናዊ ወይንም የትኛውም የአይሁድ ስነ-ጽሑፍ የለም፡፡ ይህም ወዲያ የሚጣል እጅግ ጭፍን ስህተት ነው፡፡

ሁለተኛው መከራከሪያ ደግሞ የመጀመሪያው ማብራሪያ ሆኖ የሚያገለግል ሲሆን በቁርዓንም በመጽሐፍ ቅዱስም ውስጥ ‹የ - እህት› የሚለው የሚያሳየው ዝምድናን ነው የሚል ነው፡፡ ሉቃስ 1.5፡፡ በእርግጥ ‹ሴት ልጆች› የሚለው የኤልሳቤጥን ሐረግ ያሳያል ነገር ግን የእሷ አባት የሙሴ ወንድም አሮን ነው ማለት ግን አይደለም፡፡ አሁንም ይህ ለሙስሊሞች የማያዋጣ ነው የሚሆነው እንዲያውም ሐሳባቸውን የበለጠ የሚያዳክም ነው እንጂ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ‹የ - ልጆች› ወይንም ‹የ - ሴት ልጆች› የሚለውን ዘርን ለመጥቀስ ቢጠቀምበትም እንኳን ነገር ግን ‹የ - ወንድም› ወይንም ‹የ - እህት› የሚለውን ይህንን እውነት ለማስረዳት በጭራሽ ተጠቅሞበት አያውቅም፡፡ ለዚህም የሚሆኑ የመጀመሪያው ዓይነት አጠቃቀሞች የሚከተሉት ናቸው፡- ሉቃስ 13.16፣ 19.9 ማቴዎስ 20.30፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ የአንድን ሰው ዘር በሚጠቅስበት ጊዜ ‹የአብርሃም ወንድም› ወይንም ‹የዳዊት እህት› በማለት ተናግሮ በፍፁም አያውቅም፡፡ ስለዚህም የሙስሊሞች አባባል በመጽሐፍ ቅዱስ ምንም ዓይነት የድጋፍ ማስረጃ አይኖረውም፡፡ ሁለተኛው ምሳሌ ደግሞ ያለው በቁርአን ውስጥ ሷሊሕ፣ የሠሙድ ወንድም ተብሎ በተጠራበት ቦታ ላይ ነው 27.45፡፡ እዚህ ጋ ያለው ወንድም የሚለው ቃል የሚያሳየው የቅርብ ዘመድን እንጂ የደም ዝምድናን አይደለም ይህም ቃሉ በብዙ የተለያየ መልክ ጥቅም ላይ ይውል የነበረ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ አሁንም እንደገና ችግሩ በምንም መንገድ ሊቃለል አልቻለም ምክንያቱም ‹ወንድም› የሚለው ቃል በሷሊሕ የነበረበትን ዘመን ይኖሩ የነበሩትን ሰዎች የሚያመለክት እንጂ ዝምድናንም አለመሆኑ ጭምር ነው፡፡ ይህም የሚያሳየው ማርያም የአሮን እህት ናት ብሎ ማለት ማርያምና አሮን በአንድ ወቅት የነበሩ ናቸው ማለት ነው፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ ግን ከቁርአን በተለየ መልኩ ምንም የታሪክ ስህተትን በፍፁም አታገኙበትም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን የማጥቃት ብዙዎቹ ዘመቻዎች የሚደረጉት መጽሐፍ ቅዱስ ስለማይናገራቸው ነገሮች ‹የዝምታ ክርክር› ከሚባሉት አቀራረብ ነው፡፡ ማለትም አንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዘገባዎችን የሚያረጋግጥ ገለልተኛ የሆነ የአርኪዎሎጂ ማስረጃ የለም የሚባለው ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህም መከራከሪያዎች የሚነሱት ልክ አርኪዎሎጂ ማስረጃ መስጠትን እንዳልቻለ ተቆጥሮ ነው፡፡ .ሌላው ጥቃት ደግሞ ያነጣጠረው በአርኪዎሎጂ ግኝቶች የቀናት ትክክለኛነት ላይ ነው ይህም አንዳንዶች ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪካዊ ቅደም ተከተል ጋር አብሮ አይሄድም ለማለት የሚሞክሩበት ነው ማለት ነው፡፡ አሁንም እንደገና አርኪዎሎጂስቶች በራሳቸው አተረጓጎም መለያየታቸውና እርስ በእርስ መከፋፈላቸው አንድን ሰው መጽሐፍ ቅዱስ ስህተት አለው ወደ ማለት ሊያመጣው አይችልም፡፡ ይህም በልዩ ሁኔታ እውነት ነው፤ በተለይም አንዳንድ አርኪዎሎጂስቶች ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪካዊ ዘገባ ቅደም ተከተል ጋር በትክክል ይሄዳል የሚልን ማስረጃዎቻቸው ጋር ስናስተውለው ነው፡፡

ይህ ደግሞ ከአርኪዎሎጂ ከሚያቀርበው ማስረጃ እጅግ በጣም የተለየ ነገር ነው ማለትም መጽሐፍ ቅዱስ ነገሮችን እንደሆኑ ከሚያሳያቸው ማስረጃ የተለየ ነገርን ላለማሳየት ወይንም ለማየት የሚደረገው ሙከራ ነው፡፡ በእርግጥ እስከ አሁን ድረስ መጽሐፍ ቅዱስ ትክክል አይደለም የሚልን ነገር ያሳየ አንድም የአርኪዎሎጂ ማስረጃ የለም፡፡ ነገር ግን ግኝት በግኝት ላይ ያረጋገጠው መጽሐፍ ቅዱስ በአስደናቂ ሁኔታ ታሪካዊ ትክክለኛነቱ ምንም ጥርጥር የሌለው መሆኑን ነው፡፡ የሚከተለው እና በዓለም ላይ ካሉት ታዋቂ አርኪዎሎጂስቶች የቀረበው ጥቅስ ይህንን እውነታ ያረጋግጣል፡- ‹‹መጽሐፍ ቅዱስን ታሪክነት ስህተት ነው ያለ የአርኪዎሎጂ ግኝት የትም የለም› John Elder, Prophets, Idols and Diggers [New York; Bobs Merrill, 1960], p. 16

‹የቅርብ ምስራቅ አርኪዎሎጂ በብዙ ጠቃሚ ነገሮች ላይ ያሳየው የመጽሐፍ ቅዱስን መልክዓ ምድራዊና ታሪካዊ ታማኝነት ነው፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስን ጸሐፊዎች የጭብጥ ትክክለኛነት በማብራራት (በማረጋገጥ) አርኪዎሎጂ እንደዚሁ የረዳው ነገር መጽሐፍ ቅደስ በወገናዊነት በሰዎች አመለካከት ላይ የተመሰረተ ነው የሚለውን አመለካከት በማረም ነው፡፡ አሁን በግልፅ ታውቋል ለምሳሌም ያህል ከከጢያውያን ጋር የሂብሩ ፀሐፊዎች በአጠቃላይ የጥንት የቅርብ ምስራቅ ታሪክ ውስጥ እጅግ በጣም የተሻሉ እንደነበር ነው፡፡ ይህም በግብፅ በአሶር እና በሌላም ቦታ ከሚቀርበው ተቃራኒ ፕሮፓጋንዳ በተቃራኒ ነው፡፡ E. M. Blaiklock, editor's preface, New International Dictionary of Biblical Archeology [Grand Rapids, MI; Regency Reference Library/ Zondervan, 1983], pp. vii-viii)

‹አርኪዎሎጂ የብሉይ ኪዳንን አስፈላጊ ዋና ታሪክ ለማረጋገጡ ምንም ጥርጥር የለም› በማለት ነው በዓለም ላይ ቀዳሚውና ዋናው አርኪዎሎጂስት ዊልያም ኤፍ አልበራይት የተናገረው፡፡ J. A. Thompson, The Bible and Archeology [Grand Rapids, MI; Eerdmans, 1975], p. 5)፡፡ እንዲሁም ኔልሰን ግሉክ የዓለም ታዋቂ አርኪዎሎጂስት የሚከራከረው ‹እንደ እውነቱ ከሆነ በትክክል እንናገር ከተባለ የመጽሐፍ ቅዱስን ዘገባ የሚቃረን አንድም የአርኪዎሎጂ ግኝት የለም፡፡ እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ የአርኪዎሎጂ ግኝቶች ግልፅ በሆነ ዝርዝር ወይንም በትክክል ዝርዝር የመጽሐፍ ቅዱስን ዘገባ የሚያረጋግጡ ሆነዋል፡፡›( Norman Geisler & Ron Brooks, When Skeptics Ask; A Handbook on Christian Evidences [Wheaton, IL; Victor, 1990], p. 179)

ከዚህ ከላይ የተጠቀሱት ሁለቱም አርኪዎሎጂስቶች ጥብቅ ክርስትያኖች አለመሆናቸው መታወቅ አለበት፣ ማለትም በመጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃልነት አያምኑም፡፡ የእነሱም መደምደሚያ የተመሠረተው ባገኙት የአርኪዎሎጂ የጥናት ግኝት ማስረጃ ላይ ብቻ ነው፡፡ ይህ ነው ከላይ ያሉትን ዓረፍተ ነገሮች እንዲናገሩ ያስገደዳቸው፡፡

ነገር ግን እንዲህ ዓይነቱ ለመጽሐፍ ቅዱስ የቀረበው እርግጠኛ ነገር በውስጡ ላሉት እጅግ በጣም ብዙ ስለሆኑት ታሪካዊና ሳይንሳዊ የቁርአን ስህተቶቹ ሊነገርለት አይችልም፡፡

የአዘጋጁ ማሳሰቢያ፡-

አንባቢዎች ሆይ! ከዚህ በላይ ያሉትን ታሪካዊ ንፅፅሮች በሚገባ አይታችኋል፡፡ ንፅፅሮቹ በግልፅ የሚያሳዩት በክርስትያኖች አምላክና በሙስሊሞች አላህ መካከል ከፍተኛ ልዩነት የመኖሩን እውነታ ነው፡፡ ልዩነቱ ደግሞ ለሚያስተውል ሰው፣ አሁን ማንን እና የቱን መከተል አለብኝ ወደሚል ጥያቄ ውስጥ የሚያመጡ ናቸው፡፡ የመጽሐፍ ቅዱሱ እግዚአብሔር የታሪክ ስህተትን ተመዝግቦ እንዲቀመጥ አላደረገም፡፡ እርሱ እውነተኛና የእውነት ሁሉ ምንጭ ነውና፡፡ ስለዚህም አንባቢን የምንጋብዘው የእውነተኛው አምላክ መገለጥ ያለበትን የሰውን ሕይወት እውነታ የሚያሳየውን መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያነብ ነው፡፡ በእርሱም ትዕዛዝ መሠረት ኃጢአታችሁን በመናዘዝ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ወደ ዘላለም ሕይወት እንድትመጡ ነው፡፡ ጌታ እግዚአብሔር ይርዳችሁ፡፡

 

የትርጉም ምንጭ: IS ALLAH THE GOD OF BIBLE?

 ለእስልምና መልስ አማርኛ  ዋናው ገጽ