ለአላህ የተሰጡ ሰዋዊ ባህርያት

M.J Fisher, M.Div.

ቅንብር በአዘጋጁ

ማብራሪያና ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ንፅፅር

ሙስሊሞች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ካላቸው አንዱና ዋናው ነቀፌታ ለእግዚአብሔር ተሰጠ የሚሉት አካላዊ ገለጣን የተመለከተ ነው፡፡ እነሱም መጽሐፍ ቅዱስ ለእግዚአብሔር አካላዊ ገለጣ መስጠቱን በተመለከተ እጅግ በጣም በስህተት የተሞላ ነው ይላሉ፣ ምክንያቱም ታላቁን እግዚአብሔርን የሰው ባሕርይ እንዳለው አድርጎ መግለጥ ትክክል አይደለምና፡፡ ብዙዎቹም ሙስሊሞች መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ መልኩ እግዚአብሔርን ይሳደባል በማለት ይናገራሉ፡፡

ቁርዓን እራሱ የተገነባው በመጽሐፍ ቅዱስ ታማኝነት ላይ ቢሆንም እንኳን ብዙዎቹ ሙስሊሞች መጽሐፍ ቅዱስን የሚነቅፉት እንደተቀየረ በማድረግም ጭምር ነው፡፡ ማለትም ተለውጧል እያሉ ነው፡፡ አንዳንዶቹም ክርስትያኖች በብሉይ ኪዳን ላይ ተጨማሪ ነገሮችን አድርገዋል ከዚህም የተነሳ እግዚአብሔርን ሰው አስመስለውታል እስከ ማለት ድረስ ሄደዋል፡፡ ይህንንም የሚያስረዱት፡- ክርስትያኖች ይህንን ያደረጉት ኢየሱስ ሰው የሆነ እግዚአብሔር ነው የሚሉትን ‹ስህተት› ለማስረዳት ነው በማለት ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ ቁርዓን አላህን ስጋዊ (ወይንም ሰዋዊ) በሆነ የመግለጫ መንገድ አይገልጠውም ብለው ያስረዳሉ፡፡ ይህ አባባል እና ክርክራቸው ሦስት መሠረታዊ ችግሮች አሉበት፡፡

አንደኛ ሎጂካዊ አይደለም፤ ለምንድነው አይሁዶች በክርስትያኖች የተፈጠረን ነገር በቅዱስ መጽሐፋቸው ውስጥ የሚጨምሩት? አይሁዶችም ሆኑ ክርስትያኖች አንዱን የብሉይ ኪዳንን መጽሐፍ የእግዚአብሔር ቃል ነው ብለው እንደሚያከብሩ ትክክለኛ እውነት ነው፡፡

ሁለተኛ ታሪካዊ አይደለም፤ ይህ የሙስሊሞች ክስና ውንጀላ ያለው ተስፋ በሙሉ አስደናቂ በሆኑ የጥንት ማኑስክሪፕቶች (ጥንታዊ ዋና የቅዱስ መጽሐፍት ጽሑፎች) ግኝት ፈርሷል፡፡ በ1947 የበዱዊን ጎሳ የሆኑ እረኞች ክርስትና ከመጀመሩ በፊት የተጻፉትን የብሉይ ኪዳንን ኮፒዎች አግኝተዋል፡፡ እነዚህም የቀይ ባሕር ጥቅል ወይንም የሬድ ሲ ስክሮልስ በመባል ይታወቃሉ፡፡ እነሱም ከመጀመሪያው መቶ ምዕት ዓመት ጀምሮ ከሮማውያን እጅ በዋሻ ውስጥ ተጠብቀው የተገኙ ናቸው፡፡ የተገኙት እነዚህ ጥቅሎች ክርስትያኖች በምንም ዓይነት መንገድ ብሉይ ኪዳንን እንዳልቀየሩት የሚያረጋግጥን እውነተኛ ማስረጃን ያሳያሉ፡፡

ሦስተኛ ዋጋ የለውም፤ ክርክሩ የተገነባው ቁርአን ለአላህ የሰዋዊ ባህርይን አይሰጠውም በሚል ሐሳብ ላይ ነው፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ሠላሳ ሶስት የሚሆኑት የቁርአን ጥቅሶች የሚያሳዩት ነገር ቢኖር ቁርአን ለአላህ ሰዋዊ መግለጫን እንደሚሰጥ ነው፡፡ አላህ ስምንት መላእክት ተሸክመውት በዙፋኑ ላይ ነው፡፡ የአላህ ፊትና እጆች እንዲሁም የስሜት ሕዋሳቶቹን እንደሚጠቀምም ጭምር ገለጣ ተሰጥቷል፡፡ የእሱም ድርጊት መቁጠርን መፍረድን እና መፈተንንም እንደሚጨምር ተገልጧል፡፡ ሙስሊም ያልሆኑትን እስከሚፀየፍ ድረስ (እስከሚጠላ) ድረስ ስሜት እንዳለው ተደርጎ ተገልጧል፡፡ የእሱም ስራ የሚጨምረው ሰማይን ከመውደቅ መደገፍንም ጭምር ነው፡፡ በእርግጥ ሙስሊሞች እነዚህን ሁሉ ምሳሌያዊ አነጋገሮች ናቸው በማለት ያቀርቧቸዋል፡፡ ክርስትያኖችም እንደዚህ ዓይነት አነጋገሮችን የሚያቀርቧቸው በተመሳሳይ መንገድ ነው፡፡

ክርስትያኖች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱትን እንደዚህ ዓይነት ነገሮችን በተመለከተ ምንም ችግር የለባቸውም ይህም ከብዙ ተጨማሪ ምክንያቶች የተነሳ ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለው የምስራቹ ዜና ሰዎች በእግዚአብሔር መልክ እንደተፈጠሩ ነው የሚያሳየው ማለትም ተመሳሳይ የሆነ ስሜት፣ ሐሳብ፣ እና ምኞት ልክ እንደ ታላቁ አምላክ እንዳላቸው ነው ነገር ግን የእሱ መንገድና አሰራር ዘላለማዊና እጅግ ክቡር ነው (ኢሳያስ 55.8፣9)፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያውጀው እግዚአብሔር የሩቅ አምላክ አይደለም በማለት ነው፡፡ በአንፃሩም ደግሞ እሱ የእኛን ትግሎች እና ችግሮቻችንን ሙሉ ለሙሉ ያውቃቸዋል፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ የሚገልጠው እግዚአብሔር ሰው ሆኖ በኢየሱስ ውስጥ ወደ ምድር እንደመጣ ነው ይህም በሁሉ ነገር ለመፈተንና ነገር ግን ፍፁም ያለ ኃጢአት ሆኖ ለመኖር ነው፡፡ ኢየሱስ ልክ እንደ እግዚአብሔር ቃል ሆኖ ስጋን ለብሶ መጣ ይህም በእሱ የሚያምኑትን ሁሉ በመሰቀሉና በትንሳኤው ኃይል ለማዳን ነው፡፡ ቁርአን ለአላህ አንዳንድ ሰዋዊ ባሕርያትን ቢሰጠውም እንኳን የቁርአኑ አላህ ከሰው ጋር የቀረበ ግንኙነትን ወደ ማድረግ አይመጣም፤ ማለትም የመጽሐፍ ቅዱሱ እግዚአብሔር ከፍጥረቱ ጋር ሊያደርግ እንደሚችለው አያደርግም፡፡

ስለዚህም የሚከተሉት የቁርአን ጥቅሶች አላህ በሰዋዊ መግለጫ መገለጡን የሚያሳዩ ናቸው፡፡

ዙፋን፡- ሰማያት ከተፈፀሙ በኋላ እነሱን የገነባቸው ወደ ሰማይ ወደዙፋኑ ወጣ ከዚያም ሆኖ ሰማይና ምድርን ከመጥፋት መጠበቁን ቀጠለ (13.2፣57.4፣ 35.41)፡፡ በፍርድ ቀንም ሰማይ ይቀደዳል የአላህንም ዙፋን በጭንቅላቶቻቸው ተሸክመው ስምንት መላእክት ይታያሉ (69.15-17፣ 39.75)፡፡ እነዚያ የአላህን ዙፋን የደገፉት እና ያለማቋረጥ ዙሪያውን የሚዞሩት ይቅርታ የሚገባቸው ሙስሊሞች ይቅር እንዲባሉ ይፀልያሉ 40.7-9፡፡

ሰማይን ከመውደቅ ደግፏል፡- አላህ ሰማይን ደግፏል፡፡ ሰማይም እሱ እንዲወድቅ ካልፈለገ በስተቀር አይወድቅም 22.65፡፡

ፊት፡- እያንዳንዱ በምድር ላይ ሕይወት ያለው ፍጡር ይሞታል ነገር ግን የጌታህ ፊቱ ለዘላለሙ ቀሪ ይሆናል 55.26-27፡፡

ዳኛ፡- እሱ አላህ ከዳኞች ሁሉ በጣም የተሻለ ነው 95.8፣ 10.109፡፡

መሐላ መማል፡- አላህ በጠዋትና በአስር ምሽቶች ምሏል፣ በጎዶሎና በሙሉ፣ ምሽት በሚመጣበትና በሚጠፋበት ጊዜያት .. ይህም አዕምሮ ላለው ሰው በእርግጥ ታላቅ መሐላ ነው 92.1-5፡፡ እሱም በፀሐይና በጨረቃ ይምላል በቀንና በሌሊት ይምላል 91.1፣2፡፡

ስሜትን ስለመለማመድ፡- አላህ ደስ አለው 98.8፡፡ እስልምናን የማይቀበሉትን እሱ ይጠላል 40.10፡፡ አላህ እስልምናን የማይቀበሉትን ይጠላል 30.45፡፡

የቀኝና የግራ እጅ አቅጣቻዎች፡- በመጨረሻው ፍርድ ሰዓት ሙስሊሞች በቀኝ እጁ በኩል ይቆማሉ እነዚያ የቁርዓንን ትምህርት የካዱት ደግሞ በግራ እጁ በኩል ይቆማሉ 90.17-19፡፡

ቆጠራ፡- አላህ ሰዎችን ሁሉ በጥንቃቄ ይቆጥራል ይህም እነሱ በፍርድ ቀን ብቻቸውን በፊቱ እንዲቆሙ ነው 19.94-95፡፡

ፈተናዎች፡- አላህ አማኞችን ይፈትናቸዋል ይህም የሚሆነው ከእነሱ መካከል ማን እንደሚፀና ለማወቅ ነው 47.31፡፡

በምድር ላይ መገለጡ፡- ሙሴ ከሚቃጠለው ቁጥቋጦ ውስጥ የሰማው ድምፅ ‹ሙሴ! እኔ አላህ ነኝ ..› 28.30 የሚል ነው፡፡ አላህ በእሳቱ ውስጥና በዙሪያው ሁሉ ውስጥ ነበረ 27.8፡፡

ጥበቃ፡- አላህ በእያንዳንዱ ነፍስ ጋ ቆሞ ይጠብቃል ይህም የተሰራውን ነገር ሁሉ እያንዳንዱን ነገር ለማወቅ ነው 13.33፡፡ ሦስት ሰዎች በምስጢር ቢነጋገሩ አራተኛው አላህ ነው፡፡ አራት ሆነው ቢነጋገሩ አምስተኛው እሱ ነው፡፡ አምስት ሆነው ቢነጋገሩ ስድስተኛው እሱ ነው 58.7፡፡

ይሰማል፡- አላህ ባሏን በፈታቸው ሴትና በመሐመድ መካከል የተደረገውን ውይይት ሰምቷል 58.1፡፡ እሱ ሁሉን ነገር ይሰማል ያያልም 4.134፡፡

የአላህ እጅ፡- ለመሐመድ የሚደረግ ታማኝነት፣ ፍፁም መታዘዝ እና መሰጠት ልክ ለአላህ እንደሚደረግ ነው፡፡ እነሱም እጃቸውን በአንድ ላይ በሚያደርጉበት ጊዜ የአላህ እጅም ከእነሱ እጆች በላይ ነው 48.10፡፡ የእሱ እጆች ተዘርግታለች 5.64፡፡

የአዘጋጁ ማሳሰቢያ፡-

አንባቢዎች ሆይ ከዚህ በላይ በቁርአን ውስጥ በትክክል ከተጠቀሱት መግለጫዎች እንደምትረዱት አላህ እራሱን በሰዋዊ መግለጫዎች እንደገለጠ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ብዙዎች ሙስሊሞች እንዲህ አይነትን ነገር ቁርአን እንደሚናገር ስለማያውቁ፣ በስህተት መጽሐፍ ቅዱስን ይወነጅላሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃልና ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት የተሞላ ነው፡፡ እኛ መጽሐፍ ቅዱስን በማንበባችን ለዘላለም ሕይወት የሚጠቅመንን እውቀትና መረዳት ሰጥቶናል፡፡ የእግዚአብሔርን መንገድ አሳይቶናል፡፡ እናንተም የዚህ ታላቅ ስጦታ ተካፋዮች እንድትሆኑ እንጋብዛችኋለን፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን አንብቡ በዚህ ገፅ ላይ የሚወጡትንም ጽሑፎች በጥንቃቄ ተከታተሉ፤ ቀጥሎም የግል ሕይወታችሁን መርምሩ ከእውነተኛው እግዚአብሔር ጋር ታርቃችኋልን? ከፍርድ ቀን ፍርድ በእርግጥ ትድናላችሁን? 

 

የትርጉም ምንጭ: Human Characteristics Ascribed to Allah, Chapter 13 of "A Topical Study of the Qur'an From a Christian Perspective" by M.J Fisher, M.Div

ሙሉ መጽሐፉ በአማርኛ: ርእሳዊ የቁርአን ጥናት በክርስትና አይን ሲመረመር

 

ለእስልምና መልስ አማርኛ  ዋናው ገጽ