እስልምና በኢትዮጵያ ታሪክ

[ክፍል ሦስት] ክፍል አራት
ቅንብር በአዘጋጁ

 

የሙሶሊኒ ግመሎች

በታዋቂው የአፍሪካ ቀንድ የታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ኤሪሊች ሃጋይ በ2007 ከተጻፈውና Saudi Arabia & Ethiopia [ISLAM, CHRISTIANITY & POLITICS ENTWIND] ከተሰኘው መጽሐፍ ምዕራፍ አንድ ላይ የተቀናበረ ታሪካዊ ጽሑፍ፡፡

የክርስትያን ኢትዮጵያ መንግስት በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ጊዜ ከጣሊያን ወረራ በፊት በሰኔ 1934 ከሳውዲው ኢማም ያህያ ጋር የድሮውን ነገር ግን በጣም ጥሩ ያልነበረውን ግንኙነታዊ ድልድይ ለመመስረት ጥረት አድርገው እንደነበር ታሪኩ ይገልጣል፡፡ በአፍሪካ ቀንድ ላይ ያሉትን እስላማዊ ማህበረ ሰቦችን ያገናኘው ቀይ ባህር ከክርስትያን ኢትዮጵያ መንግስት ጋር ብዙ ግንኙነትን ለማሰራት ባለማስቻሉ፡፡ በኢትዮጵያ ነገስታትና በተለያዩ የአረብ አገር መሪዎች መካከል የነበረው የታሪካዊ ግንኙነት ታሪካዊ ዘገባ የሚመስለው ጥቂት ነበረ በማለት የታሪክ ተመራማሪው ያስረዳል፡፡ የዚህ ሰንካላ ግንኙነት እና ወዳጅነት ስምምነት መጥፋትም ዋናው ምክንያት የኢትዮጵያ መንግስት ሃይማኖት ነው፡፡

ለዚህ የወዳጅነት አለመኖር ችግር በተመለከተ የሚገኘው ታዋቂ ታሪክ በአስራ ሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ በንጉስ ፋሲለደስ የተሞከረው ሙከራ እንደነበረ ጸሐፊው ታሪካዊውን ማስረጃ ያቀርባል፡፡ ንጉሱ ከየመኑ ኢማም አል-ሙታዋኪ አላ አል-አላህ ጋር (በመልእክተኞቻቸው አማካኝነት) ውይይት አድርገው ነበር፡፡ ውይይቱም ያጠናከረው ነገር በኢትዮጵያና ከቀይ ባህር ማዶ ባሉት አጎራባች አገሮች መካከል ጥልቅ የሆነ መሰረታዊ ችግር የመኖሩን እውነታ ብቻ ነበር፡፡ የየመኑ ኢማም የኢትዮጵያ መንግስት ያቀረበውን የንግድና የፖለቲካ ትብብር ጥያቄ አልቀበልም ብሎ ነበር፡፡ ምክንያቱ ምን ነበር? የየመኑ ኢማም ከኢትዮጵያ መንግስት የጠየቀው ጥያቄ ነበር፣ ጥያቄውም የሃይማኖት ለውጥ ነበር፣ ፕሮፌሰር ኤርሊች ማስረጃውን ጠቅሶ እንደሚከተለው እንደነበር አስቀምጦታል፡ ገዢውም ያለው “የኢትዮጵያው ንጉስ” ማለትም ፋሲለደስ “በቅድሚያ የነጃሺን ፈለግ መከተል አለበት” ነበር፡፡ በመሆኑም የወዳጅነት ስምምነቱ እንዲኖር ንጉሱ በቅድሚያ ሃይማኖቱን “ወደ እስልምና መለወጥ አለበት” የሚል ሰበብ ነበር፡፡ እንደዚህ ዓይነቱ መሰረታዊ ችግር ነው ጥልቅ የሆነ ዘላቂ ችግር ከውጭ ብቻ ሳይሆን ከውስጥም አገሪቱን የከበባት መሆኑን የሚያሳየው፡፡

በ1930ዎቹም ውስጥ በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ለሳውዲው ንጉስ ለኢብን ሳውድ የቀረበው ጥያቄም በጣም የማይሆን እድል አጋጥሞት ነበር፡፡ በእርግጥ በዚያን ጊዜ ኢትዮጵያ ጠንካራ የሆነች የክርስትያን አገር ሆና ነበር፡፡ ስለዚህም በዋሃቢያ እምነት ላይ የተመሰረተው የሳውዲ መንግስት የኢትዮጵያን መንግስት የእነተባባር ትያቄ ሊቀበለው አልቻለም ነበር፡፡

ነገር ግን የአፍሪካን ቀንድና አረቦችን ቀይ ባህር ያገናኛል የሚለው ፅንሰ ሐሳብ ለጣሊያን ቅኝ ገዢዎች በጣም ጠቃሚ የነበረ ስልት ነበር፡፡ ከ1890 ዓም ጀምሮ የራሳቸውን አካባቢያዊ ማህበረ ሰብ በኤርትራ ውስጥ መስርተው የነበሩት ጣሊያኖች ማህበረሰባቸውን በቀይ ባርህ ስም ላይ የተመሰረተና “ማሬ ኤሪትርየም” የሚል ስያሜ ሰጥተውት ነበር፡፡ ጣሊያኖቹ በሁለቱም የባህሩ አካባቢ አገሮች ላይ ተፅዕኖአቸውን ለማምጣት አልመው ነበር፡፡ ስለዚህም በሙሶሎኒ ስር ይህ ረቂቅ ሃሳብ በጣም ንቁ የሆነ ፖሊሲ ሆኖ ነበር፡፡ በ1926 ሙሶሊኒ የጣሊያንን ማህበረ ሰብ በዲክታተሪያል ቁጥጥር ስር ካደረገ በኋላ ያወጀው የመጀመሪያው ነገር “የናፖሊዮናዊ ዓመትን” ነበር፣ በዚህም የፋሽስቱ መንግስት እራሱን የሚያረጋግጠው በሜዲትሬኒያን ባህር እና በቀይ ባህር ላይ እንደነበር ይፋ ሆኗል፡፡ በመሆኑም በጣም ሃይለኛ የኤርትሪያ ገዢ የነበረው ጃኮቦ ጋስፓሪኒ ሁለት መልክ ያለውን ተግባሩን ጀመረ፡፡ በአንድ በኩል ጣሊያን በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገባበትን ነገር ሲያጠብቅ በሌላ ጎኑ ደግሞ ከአረቢያኖች ጋር ትብብርን ለመመስረት ጥረትን አደረገ፡፡ በመስከረም 1926 ላይ ጋስፓሪኒ ከየመኑ ኢማም ያህያ ጋር የትብብር ስምምነትን ፈረመ ይህም ጣሊያኖች የመኖችን እንዲያስታጥቁ መንገድን ከፈተ፡፡ ምንም እንኳን ይህ አዲሱ የአስመራ-ሰንዓ የትብብር ስምምነት ለሳውዲው ኢብን ሳውድ (ከኢማሙ ጋር በወቅቱ በግጭት ላይ ለነበረው) ጥቃት ቢሆንም፣ በ1927 ደግሞ ጋስፓሪኒ ከሳውዲዎችም ጋር ዲፕሎማቲካዊ ግንኙነቶችን ጀምሮ ነበር፡፡

ጣሊያኖች ታላቋን የመንን ለመቆጣጠር እንዲችሉ፣ ይህም ብሪቲሽ በሳውዲ ላይ ያላትን ተፅዕኖ እንደያዘች እንዲሆን ለንደንን ማስገደድ እንዳለባቸው ጋስፓሪኒ ሙሶሊንን አሳመነው፡፡ ነገር ግን በ1920ዎቹ ላይ ኃያል የነበረችውን ቢሪቴንን በቀይ ባህር ላይ ዋና ኃይል ለመሆን ጣሊያኖች የነበራቸው ሕልም ተጋፍጠዋት ነበር፡፡ የብሪቲሽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኦስቲን ቻምበርሊን በየካቲት 1927 ላይ ለሙሶሊኒ በግልጥ ነግሮት የነበረው ነገር ቀደም ብሎ “የንጉሱ መንግስት በአረቢያ ዙሪያ ባለው የቀይ ባህር ላይ ማናቸውም የአውሮፓ ሃይል ምንም ነገርን እንዳያደርግና ይህ ዋና ፍላጎታቸው እንደሆነ ነግሮታል”፡፡ እንዲህ ዓይነት የሆነውን የብሪቲሽን ውሳኔ በማግኘት (ብሪቲሾች በየመን ላይ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆናቸውን ስለጠቆሙ) ሙሶሊኒ የቀይ ባህር ህልሙን (ለጊዜውም ቢሆን) መርሳት ነበረበት፡፡ ስለዚህም ጋስፓሪኒ ከኤርትራ ተነሳ የመኖች ሳውዲን ለማጥቃት ለነበራቸው ጥረትም ቀጥተኛ የሆነ የጣሊያን እገዛ አልተሰጠም፣ ከሳውዲም ጋር ይደረግ የነበረው ዲፕሎማቲካዊ እንቅስቃሴ ሙሉ ለሙሉ ቆመ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ውስጥም ይደረግ የነበረው ሰርጎ መግባት ቀዘቀዘ፡፡ ቀጥሎም በነሐሴ 1928 ጣሊያን የሃያ ሁለት ዓመት የወዳጅነት ስምምነት ከክርስትኗ መንግስት ጋር ተፈራረመች፡፡

በ1932 ዓለም አቀፉ ታላቅ ኪሳራ ጋር እንዲሁም ከጊዘያዊ የብሪቴን ድክመት ጋር ሙሶሊኒ የቀይ ባህር ሃያልነቱን ምኞት እንደገና አነሳው፡፡ ስለዚህም በሁሉቱም ወደቦች ዙሪያ እንቅስቃሴዎች እንደገና ጀመሩ፡፡ በኤርቲሪያ ውስጥ ገዢው ኮራዶ ዞሊ  የኃይለስላሴን መንግስት እንዲያዳክምለት ጋስፓሪኒን እንደገና መልምሎት ነበር፡፡ የውስጥ ማዕከላዊ ኃይሎችን የማጠናከር ፖሊሲ በኢትዮጵያ ላይ ያተኮረው በትግሬያውያን ጎሳዎች ላይ ነበር ይህም በጥንቱ የአማራ ገዢ መደብ ጥላቻ ላይ የተመሰረተ እና ስያሜውም “ፖለቲካ ትግሪኛ” የሚል ነበር፡፡ ይህም ቀስ በቀስ አሁን የተጠናከረው እስላም እንደ ማዕከላዊ ኃይል በኢትዮጵያ ውስጥ እንደገና ሊጠናከር ይችላል በሚለውም ሐሳብ ላይ ተመስርቶ ነበር፡፡ በአረቢያ ውስጥ ኢጣሊያኖቹ ከሳውዲ ጋር በመጋቢት 29 1932 “የንግድና የወዳጅነት” ስምምነትን ተፈራረሙ፡፡ ነገር ግን እንደገና ዋናው ትኩረታቸው በየመን ላይ ነበር፡፡ ጣሊያኖች በሰንዓ የነበራቸውን እንቅስቃሴ በተግባር በጣም አጠናክረውት ነበር፤ እናም ኢማም ያህያን ሳውዲዎችና የመን የሚከራከሩበትን አካባቢ “ኢርን” ሳውዲዎችን ተቃውሞ እንዲይዝ ያበረታቱት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በየመን ላይ ጣሊያኖች ይጫወቱት የነበረው ካርድ አሳፋሪ ነበር፡፡ በግንቦት 20 1934፣ እንደተጠቀሰው ያህያ በጦርነቱ ላይ ተሸነፈ ስለዚህም “በኢር”ና በአረቢያ ባህረ ሰላጤ ላይ ሳውዲ ያላትን አገዛዝ እንዲሁም የዋቢዝምን የበላይነት ገዢነት መቀበል ነበረበት፡፡ ስለዚህም የኢጣሊያኖች በአረቢያ ላይ ያላቸው ፖሊሲ የዞረው ሳውዲዎችን በማባበልና እነርሱንም ወደፊት በአካባቢው የሚመጣውን የፋሺስትን የበላይነት አንድ ጊዜ እስኪመጣ ድረስ እንዲቀበሉ በማዘጋጀት ላይ ነበር፡፡

ጣሊያኖች የአረቢያን - የመን ካርዳቸውን ካጡ ከሰባት ቀናት በኋላ የኢትዮጵያው አማራጭ መስመር መያዝን ጀመረ፡፡ ግንቦት 27 1934 የምስራቅ ትግሬ ገዢ የነበረው ኃይለ ስላሴ ጉግሳ ለጣሊያኖች በምስጢር የገባላቸው ቃል ኪዳን ሰራዊታቸው ወደ ኢትዮጵያ መካከል ወይንም እምብርት የሚገባበትን መንገድ እርሱ እንደሚከፍትላቸው ነበር፡፡ ከአራት ቀናትም በኋላ ሙሶሊኒ ሚኒስተሮቹ ኢትዮጵያን ለመውጋት እንዲዘጋጁ አዘዘ፣ ከዚያም በሐምሌ ወር እርሱ እራሱ ሙሶሊኒ ዕቅዱን መቆጣጠር ጀመረ፡፡ ታህሳስ 5 1934 በኢትዮጵያና በሶማሊያ ድንበር ላይ ግጭት ተፈጠረ (በወልወል) ያም የአቢሲኒያን መፍረክረክ የበለጠ ለማቀጣጠል (የታቀደ) ነበር፡፡ የሙሶሊኒ ዛቻና ኢትዮጵያን ለመውጋት የሚያደርገው ዝግጅት የመንግስታቱን ህብረት የአንድነት ጥበቃ ፅንሰ ሐሳብ በ1935 ዓመት ሙሉ ሲያናጋው ቆይቷል፡፡ በዚህም ጊዜ ውስጥ የሙሶሊኒን ኃይለኛ ውሳኔና እንዲሁም የጀርመኑን ሂትለርን ለመደባለቅ የሚያደርገውን ዛቻ በማየት ብሪቲሽ ሁኔታውን ዝቅ አድርጋ ልትመለከተው አልደፈረችም፡፡ ስለዚህም ቢሪቲሾች በ1935 በጋው ላይ ምንም እንኳን የዲፕሎማቲክ ጥረት ቢያደርጉም ኢትዮጵያን አሳልፎ ለመስጠት መወሰን ነበረባቸው፡፡ በዓለም ዙሪያ እየገዘፈ ካለው ሁኔታ ጋር ለመጋፈጥ እየጣሩ የብሪቲሽ ፖሊሲ አውጭዎች በቀይ ባህር ዙሪያ ላይ በጣም ጥንቃቄ ያለው እንቅስቃሴ ይወስዱ ጀመር፡፡ ፋሽስት በመጨረሻ በጥር 3 1935 ላይ ኢትዮጵያን በወረረበት ጊዜ ሙሶሊኒ አምኖ የነበረው ነገር በትክክል ከብሪቲሾች ጋር የግጭት አደጋ ውስጥ እንደማይገባ ነበር፡፡

የሙሶሎኒ ጦርነትና ትርጉሙ

በኢትዮጵያ ላይ ሙሶሊኒ የሚያሂደው ጦርነት በእርሱ እይታ የመረማመጃ ድንጋይ ብቻ ነበር፡፡ የጣሊያኑ ዲክታተር የጥንቱን የሮማን ግዛት በምስራቅ ለማምጣት ሕልም እንደነበረው በፍፁም አልሰወረም፡፡ ስለዚህም የኢትዮጵያ ጦርነት ማለት የአፍሪካ ጦርነትና ወደ መካከለኛው ምስራቅ የመግቢያ መስፈንጠሪያ ነበር፡፡ ስለዚህም ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ በኩል ወደ ሜድትራኒያን የጓሮ መግቢያ በር እንድትሆን ታስቦ ነበር፡፡ የሆነው ሆኖ ከእንግሊዝና ከፈረንሳይ ጋር ቆይቶ ጦርነት እንደማይቀር ሙሶሊኒ አውቋል፤ ይህንንም ከአካባቢው የጦር ትብብርና እርዳታ ካላገኘ እንደማይወጣውም ተገንዝቦ ነበር፡፡ ስለዚህም እርሱ የእስልምናንና የአረባዊነትን ኃይል በመጠቀም ከፈረንሳይና ከእንግሊዝ ጋር ሊመጣ ለሚችለው ጦርነት ያዘጋቻቸው ጀመር፡፡ የጣሊያን ከእስልምና ጋር መዳራት በ1920 በሊቢያ ውስጥ ከተከሰተው ችግር ጀምሮ፤ ችግር አጋጥሞታል፣ ይህም የሳኑሲ ተቃውሞ ስላጋጠመው ነበር፡፡ እነርሱንም በጭካኔ ከመጨፍጨፍ ሌላ ምንም አማራጭ ስላልነበረው አጠፋቸው እና መሪያቸውን ኡማር አል-ሙክታርን በ1931 መስከረም ወር ላይ በአደባባይ ሰቀለው፡፡ ይህ ጭካኔ የሙሶሊኒን ስም በአጠቃላይ ሙስሞሊሞች ዘንድ መጥፎ አድርጎትና አዋርዶት ነበር፡፡ ይህንን ስሙን እንደገና ለማንሳት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረገው ጦርነት ወሳኝ ነበር፡፡ ስለዚህም በ1932፣ ስሙን “የእስልምና አዳኝ” ለማድረግ የሚቻለው ኢትዮጵያን በመውረርና በ1896 በአድዋ ጣሊያንን ድል ያደረገችውን ኢትዮጵያን ከመበቀል ውጭ፣ እና ስልታዊ መካከለኛ ምስራቅን ለመቆጣጠር መግቢያ ከማድረግ ውጭ ኢትዮጵያን መውጋት መስሎ የቀረበው ስለ እስልምና መዋጋት ተደርጎ ነበር፡፡

በ1934 ውስጥ ጣሊያን የእስልምና ደጋፊ፣ የአረብ ደጋፊ ናት የሚለው የቅስቀሳ ጥረት በጣሊያን መር ምስራቃውያን ዘንድ በትልቅ ቅናት ተቀጣጥሎ ነበር፡፡ የዚህም እንቅስቃሴ ዋና መልእክት ኢትዮጵያ የምትባለው አገር፡ ከፊል አረመኔያዊ የክርስትያን መንግስት ስትሆን በታሪኳ ሁሉ ውስጥ ሙስሊሞችን የጨቆነች አገር ናት የሚለው ነበር፡፡ ይህ የጥላቻ አነጋገር በዚያን ጊዜ በነበረው የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች እስላማዊ ደጋፊ አገሮች ሁሉ ውስጥ ተሰራጭቶ ነበር፡፡ በመሆኑም በአረቡ አገር ሁሉ ውስጥ ታላቅ ክርክርንና ልዩነቶችን ፈጥሮ ነበር፡፡ አሁንም በአገሪቱ ውስጥ ባሉት የዋሃቢያ ተከታዮች ዘንድ የሚሰራጨው ቅስቀሳ ተመሳሳይ ነው ማለትም ኢትዮጵያ እስልምናን የጨቆነች አገር ናት እንዲያውም የእስልምና ጠላት ናት የሚለው ነው፡፡ በሚቀጥለው የፕሮፌሰር ኤሊሪች ጽሑፍ በኢትዮጵያ ውስጥ የዋሃቢያን እንቅስቃሴ በጥልቅ የምንመለከተው ይሆናል፡፡  

ኃይለስላሴ እና እስልምና፡

ሙሶሊኒ የእስልምና ጠባቂና ነፃ አውጪ ነው የሚለውና ልጅ ኢያሱ ደግሞ ሕጋዊ የኢትዮጵያ ንጉስ ነው የሚሉት መልእክቶች ለኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በስፋት ተነገሩ፡፡ በአጣሊያን የመረጃ ምንጮች መሰረት ሙሶሊኒ ኃይለስላሴን አስወግዶ እስልምናን የአገሪቱ የፖለቲካ መሳሪያ የማድረጉ ጉዳይ በጥሩ ሁኔታ በሐረር፣ በኦጋዴን፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ኦሮሞዎች ዘንድና እንዲሁም በአዲስ አበባ ባሉት አረብ-እስላም ነጋዴዎች ዙሪያ  በስፋትና በብቃት ተሰራጨ፡፡ ፋሺስቶች ለሁሉም ዓላማና ፍላጎቶቻቸው ወኪሎቻቸው ሁሉ የኢትዮጵያን መከላከያ ለማዳከም የሚያስችልን ስራ ለመስራት በሙስሊሞች ማህበረ ሰቦች ሁሉ ውስጥ በስፋት ተንቀሳቀሱ፡፡ ስለዚህም ወረራውን ለማድረግ ሲዘጋጁ ጣሊያኖች ሰባ ሺ የሙስሊም ወታደሮችን (ተዋጊዎችን) “አስካሪስ” የሚሏቸውን መልምለውና ቀጥረው ነበር፡፡ እነርሱንም የመለመሉት ከኤርትሪያ፣ ከሶማሊያ የነበረ ሲሆን ከአረቢያም እንደዚሁም ከሌሎች የአረብ አገሮችም ጭምር ነበር፡፡ በራሱ በጦርነቱ ወቅትም እጅግ ብዙ የኦሮሞ ሙስሊም ተዋጊዎች የጣሊያንን ወራሪ ጦር ሰራዊት ተደባልቀውት ነበር፡፡

የኃይለስላሴ ጥረት፡

በጊዜው በውጥረት ላይ የነበረው የኃይለስላሴ መንግስት በተለያዩ መንገዶች ልዩ ልዩ ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ለወታደራዊው ዝግጅት በአውሮፓውያን መንግስታት በኩል እርዳታ ለማግኘት ጥረት ቢደረግም የሙስሊሞች ነገር ግን ችላ ሊባል የሚገባ ነገር አልነበረም፡፡ ግራኝ መሐመድ ያስቀመጠው ታሪካዊ ጠባሳ እንዳለ ነበርና ስለዚህም በአፍሪካ ቀንድ ላይ ያሉትን ሙስሊሞች የውጭ ኃይላት አንቀሳቅሰዋቸውና ድጋፍም አድርገውላቸው በአገሪቱ ውስጥ የሙስሊም መንግስት ለመመስረት ትግል ያደርጋሉ የሚለው ፍርሃት አሁንም እንዳለ ነው፡፡ የሆነው ሆኖ ፕሮፌሰር ታሪክን አጣቅሶ ያስቀመጠው የኃይለስላሴ መንግስት ለዚህ ሶስት ዘርፍ ያለው ምላሽን እንዳደረገ ነበር እነዚህም፡

አንደኛው፡

የጥንቱ የመጨቆንና የማንቋሸሽ መንገድ እንደገና ተጀመረ፣ እነዚህ መንገዶች ከጣሊያን ወረራ ጥቂት ቀደም ብሎ በተከሰተው ምስጢራዊው የልጅ ኢያሱ ሞት አበቁ፡፡

ሁለተኛው፡

ሙሉ ለሙሉ አዲስ ወደ ሆነ አቀራረብ በድንገት ቀልበስ ማለት ነበር፡፡ ስለዚህም በ1935 በመጀመሪያዎቹ አካባቢ ንጉሱ ኃይለስላሴ እራሱን የተለያየ ማህበረ ሰብ አካላት መሪ አድርጎ ማቅረብ ጀመረ፡፡ እርሱም በተለያዩ ቦታዎች ላይ በታላቋ ኢትዮጵያ ውስጥ የሃይማኖት እኩልነት እንደሚኖር ንግግር አደረገ፡፡ አያይዞም በግንቦት 22 1935 ለሐረር የማህረሰብ መሪዎች ንግግርን አደረገ፡፡

የንጉስ ኃይለስላሴም ዋና መልእክት የነበረው ሁሉንም ሃይማኖቶች፣ ሁሉንም ጎሳዎች፣ በአዲሲቱ የኢትዮጵያ ሞዴል ማለትም “ክርስትያን ባልሆነው ነገር ግን ከልዩ ልዩ አካል በተውጣጣው የኢትዮጵያ ሞዴል” ውስጥ ለማካተት መሞከር ነበር፡፡ እርሱም የሁሉም ሃይማኖት እኩልነት ያለበት ህገ መንግስትን እንደሚያወጣ ቃል ኪዳንን ገባ፡፡ ሙስሊሞችን የማባበሉ የእርሱ አዲሱ ጥረት ያካተተው በአዲስ አበባ ውስጥ የአረብ ቋንቋ ጆርናል እንዲታተም እና በሚኒልክ ትምህርት ቤት ውስጥ አስተማሪ በነበረው ግብፃዊ አማካኝነት እንዲዘጋጅ የተደረገው እርምጃ ነበረበት፡፡ በመጨረሻም ቀደም ሲል በአፄ ሚኒሊክ በ1904 ቃል የተገባበትን የታላቁ መስጊድን ግንባታ ፈቀደ፡፡ በዚህም መሰረት እና በመሐመድ አሊ ኩባንያ ተፅዕኖ መሰረት የአረብ-እስላማዊ የንግድ ማዕከል በአዲስ አበባ መርካቶ ኢትዮጵያን በመደገፍ የድጋፍ መግለጫን አወጣ፡፡ በግንቦት 30 1935 በመሐመድ አል ሳዲቅ “የአገሪቱ የሙስሊም ኮሙኒቲ መሪ” በነበረው የተሰጠውን መግለጫ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት በጋዜጣው ላይ አውጥቶታል፡፡

ሦስተኛው፡

በኃይለስላሴ ተደርጎ የነበረው ሦስተኛው እርምጃ በአረብ አገሮች ውስጥ እርዳታን መፈለግ ነበር፡፡ በ1935 ውስጥ ወደ ግብፅ፣ ሊቢያና አረቢያ መልእክተኞችን ላከ፡፡ የእርሱም ዓላማ የወታደርና ሌላም ዓይነት የቁሳቁስ እርዳታን ለመጠየቅ አልነበረም፡፡ እርሱ ፈልጎ የነበረው ለእርሱ የኢትዮጵያ አዲስ ሞዴል ማለትም የሐበሻ ሕዝቦች መንግስት የስምምነት (የተቀባይነት) ምልክት እንዲሁም ከሙሶሊኒ ጋር ለሚያደርገው ትግል የሙስሊም ሕዝቦችን ድጋፍ ለማግኘት ነበር፡፡ እርሱም የተደባለቀ ውጤት ነበረው፡፡ በሊቢያ የነበረው ሚሽን ያልተሳካ ነበር ምክንያቱም የሳኑሲ የፀረ ጣሊያን እንቅስቃሴ ተደምስሶ ነበርና፡፡ በጣም ጠቃሚው ደግሞ የግብፅ ሕዝብ ነበረ፡፡ በእርግጥ ግብፃውያን በሙሶሊኒ በኩል ሊከፈት ስላለው ጦርነት ያን ጊዜ አስታዋሽ አያስፈልጋቸውም ነበር፡፡ በ1935 የኢትዮጵያና የእርሷ እጣ ፈንታ፣ በግብፅ፣ እንዲሁም በሶርያ በኢራቅና በፍልስጥዔም ውስጥ የሕዝብን አመለካከት በመካፋፈል ዋና ጉዳይና አጀንዳ ነበር፡፡

በአጠቃላይ የመካከለኛው ምስራቅ የፓን አረብ አገሮች አገር ወዳድነት እንዲሁም የእስልምና በፖለቲካው መድረክ ውስጥ መነቃቃት፤ “የኢትዮጵያ ጥያቄ” እንዲሁም ከእርሱ ጋር አብሮ ያለው ያልጠራ አመለካከት ከዚህ እንቅስቃሴ ማዕከል ውስጥ እና የማንነት ትርጉም ውስጥ ገብቶ፤ የፖለቲካ መረጋጋት በሌለበት ሰዓት እንደገና ሊተረጎም ነበር፡፡ እጅግ ብዙ የሚሆኑት ግብፃውያን ብሪቴንን ከሚያዳክም ማንኛውም ነገር ጋር ተባብረው ነበር፡፡ ብዙዎች ሌሎች ደግሞ ሙሶሊንን በመደገፍ ዝግጁዎች ሆነው በክርስትያን ኢትዮጵያ ላይ መጥፎውን ሁሉ ይመኙ ነበር፡፡ መጽሐፎችና ጽሑፎች የኢትዮጵያን ወንጀል በመግለፅ ተጻፉና በጊዜው የነበረውን የንጉሱን የኃይለስላሴ የመጨረሻ ደቂቃ ንቃት ላይ ማላገጣቸውን ቀጠሉ፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያን ይደግፉ የነበሩትም ቀላል ቁጥር አልነበራቸውም በተለይም ሳይጠቀስ የማይቀረው እና የአገሪቱን ጠቃሚ እገዛ ያመጣው በግብፅ ውስጥ “ኢትጵያን የሚመክት ኮሚቴ” መቋቋሙና መንቀሳቀሱ ነበር፣ እርሱም ሊበራሎችና አክራሪ ያልሆኑ የካይሮ ሙስሊሞች አንድነት ድርጅት ነበር፡፡  

ኢትዮጵያን ይደግፉ ከነበሩት ውስጥ የሳላፊያ እንቅስቃሴ መሪ የነበረው ሼክ መሐመድ ራሺድ ሪዳ፣ የፀረ ኮሎኒያሊስቶች አመለካከት ስለነበረው አፄ ሚኒሊክ በጣሊያን ላይ የነበራቸውን ድል በጣም የሚያደንቅና እንደምሳሌ ይመለከት የነበረ ሰው ነው፡፡ ይህ ሰው የሳውዲው ንጉስ ወዳጅ ስለነበረ ፕሮፌሰሩ እንደጠቀሰው የሳውዲው ንጉስ ግብፅን በጎበኘበት ወቅት ኢትዮጵያን መደገፍና ጣሊያንን መቃወም እንዳለበት እንደወተወተው ደብዳቤዎችንም በጥር 1935 እንደጻፈለት ጠቅሷል፡፡ ከዚያም ባሻገር ለሶርያዊው ድሩዝ ለአሚር ሻኪብ አርስላ በጥር 24 1935 በጻፈው ደብዳቤ ላይ ኢትዮጵያን ለማጥቃት ለሚሄደው ለሙሶሊኒ ምንም ድጋፍን ከማድረግ እንዲቆጠብ አሳስቧል፡፡ በኋላ ቆይተን እንደምናየው ይህ አርስላ ከፍተኛ የሆነ ፀረ ኢትዮጵያ አቋም የነበረውና ኢትዮጵያ እንድትጠቃ ቢቻልም እንድትወድም ቅስቀሳ ያደረጉ ብዙ ጽሑፉችን የጻፈ ሰው ነው፡፡

በዚያን አንገብጋቢ ወቅት ቀዳማዊ ኃይለስላሴ በተለያየ ጊዜ ወደ ሳውዲው ንጉስ የተከበሩ የመንግስት ልዑካንን ቢልኩም ያገኙት የቀናነት ምንም ትብብር እንዳልነበረ ጥናቱ ዝርዝር ሁኔታዎችን እና መልእክተኞችን በመጥቀስ ያስረዳል፡፡ በሚያዝያ 7 1935 የኢትዮጵያ ልኡካን ወደ ጅዳ በመሄድ ንጉሱን እንዲያነጋግሩና ከኃይለስላሴ የተላከውን ደብዳቤ እንዲያቀርቡ ተልከው ነበር፣ በሚያዝያ 10 1935 የኃይለስላሴም ጥያቄ ሆኖ የቀረበው “በነቢዩ በነጃሺ መንፈስ የወዳጅነት ምስረታን” መጠየቅ ብቻ ነበር፡፡ ንጉሱ የመለሰው ይህንን ለማድረግ ጊዜው አሁን እንዳይደለ ምንም ዓይነት ስምምነትም እንደማይደረግ ነበር፡፡ ኢብን ሳውድ ለጥያቄው በተጨማሪ የመለሰው እርሱ ለኢትዮጵያም ለጣሊያንም ወዳጅ እንደሆነና የእነርሱ ግጭት የሆነ ደረጃ ላይ ሳይደርስ ወይንም ፍፃሜ ላይ ሳይደርስ ማንኛውንም ሊወግን እንደማይችል ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በወቅቱ ከልዑካኑ መካከል ለነበረው ለኢትዮጵያዊው ሙስሊም ለአህመድ ሳሊክ ንጉሱ ሳውድ የተናገረው፣ “ኢትዮጵያ ለራሷ ሙስሊሞች የምታደርገውን ሁሉ እንደሚያውቅ ነበር፡ ቀጥሎም ለልዑኩ የነገረው “አባ ጅፋር ተወግዷል ልጁም ተሰዷል፡፡ በጅማ ለብዙ መቶ ዓመታት የነበረው እስላማዊ መንግስት ተደምስሷል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ጠቃሚ ቦታ ላይ የተቀመጠ ወይንም ጠቃሚ ቦታ የያዘ ማንም ሙስሊም የለም፡፡ እኔ ለኢትዮጵያ ምንም ነገርን ላደርግ አልችልም” ነበር ያለው፡፡ ስለዚህም ሚያዝያ 15 ልዑካኑ ባዶ እጃቸውን ተመለሱ፡፡ ይህም ነገር ሙሶሊንን በከፍተኛ ደረጃ አስደስቶት ነበር፡፡

የአርሰላን እጅ በታሪኩ ውስጥ

በኢትዮ-ጣሊያን ጦርነት ላይ የሳውዲ አረቢያውን ንጉስ ኢብን ሳውድን ከጣሊያኖች ጋር እንዲተባበርና የኢትዮጵያን ጥያቄ ችላ እንዲል እንዲያውም እንዲዘጋ እንዲያውም በጠላትነት እንዲቆም ለማድረግ መሳሪያ በመሆን የቆሙ ሁለት ግለሰቦች እንደነበሩ የፕሮፌሰሩ ጥናታዊ ጽሑፍ ያሳያል፡፡

ከ1920 ጀምሮ የኢብን ሳውድ የውጭ ጉዳይ አማካሪዎች የነበሩት አንደኛው ግብዊው ሃፊዝ ዋህባ፣ ሁለተኛው ሶርያዊው ዩሱፍ ያሲን እና ሦስተኛው ደግሞ ሊባኖሳዊው ድሩዝ ሃምዛ ነበሩ፡፡ ግብፃዊው ዋህባ የሳውዲ የብሪቴን አምባሳደር ስለ ነበር ከኢትዮጵያ ሳውዲ ጉዳይ ውጭ ሲሆን ሁለቱ ማለትም ሶሪያዊውና ሊባኖሳዊው ግን በጥልቅ ተሳትፈውበታል፡፡ ሁለቱም በርዕዮተ ዓለማዊ አቋማቸው ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ከተቋቋመው ከ”ሶርያ ፍልስጥኤም ኮንግረስ” የአረቦች ህብረት ጋር ግንኙነት ነበራቸው፡፡ የዚያም ኮንግረስ መሪዎች ውስጥ አርስላንና ቀደም ብሎ የተጠቀሰው ግብፃዊው ሪዳ ይገኙበታል፡፡ ሪዳ እስከሚሞትበት ዕለት ድረስ ሙሶሊንን ይቃወም የነበረ ሲሆን ሦስቱ ግን ከጣሊያን ጋር የቅርብ ትስስርን አድርገዋል፡፡

ሊባኖሳዊው ሐምዛ እንደ አርስላን የተማረ ሰው ሲሆን የሳውዲው ኢብን ሳውድ አድናቂና እርሱንም የአረባ ባህረሰላጤ አረብ እስላም ታሪክ ማዕከል አድርጎ የሚቆጥርና የእርሱም ሰራተኛ ለመሆን በ1924 የመጣ ነው፡፡ ይህንንም ፅንሰ ሐሳቡን በ1933 ባሳተመው መጽሐፉ “The Heart of the Arab Peninsula’ በሚለው መጽሐፉ ውስጥ አስቀምጦታል፡፡ በዚያ መጽሐፉ ውስጥ ለኢትዮጵያ የሰጠው ግልፅ የሆነ እጅግ መጥፎ ገፅታ ነው፡፡ የነቢዩ መሐመድን ታሪክ ሲያወሳ ወደ ኢትዮጵያ የተደረገውን ጉዞ ጠቅሶ ለሳሃባዎቹ ኢትዮጵያ ያደረገችውን ነገር ፈፅሞ አልጠቀሰውም (ገፅ 262-271}፡፡ በአንፃሩ (በተቃራኒው ግን) ቀደም ብሎ ኢትዮጵያውያን የመንን እንደወጉና ካዓባን ለማጥፋት እንደዛቱ በጣም በሰፊው ዘግቧል (ገፅ 252)፡፡ በዚያ አንቀፅ ውስጥ ያስተላለፈው መልእክት አረቦች ከወራሪ ክርስትያን ኢትዮጵያ ቅዱሳን ቦታዎቻቸውን ለማዳን ሲሉ አንድ መሆን አለባቸው የሚለውን መልእክት ነው፡፡ በዚያን ጊዜ የነበረውን የአቢያን ባህረ ሰላጤ ሲገልጠው ሐምዛ የሰጠው ነጥብ ውስጥ “ንፁህ አረብ” እና 435,000 “አረብ ያልሆኑ” በግምት አረቢያ ውስጥ እንደሚኖሩ ነበር ከእነዚህም ውስጥ 200,000 ዎቹ ጥቁሮችና ኢትዮጵያውያን ናቸው በማለት ነበር፡፡ የኋለኞቹ ምንም እንኳን ሙስሊሞችም ቢሆኑ እንኳን በሐምዛ መሰረት ግን እነርሱ የባርያ ዝርያዎች ወይንም ወራሪዎች ናቸው የሚል ገለፃ ነበራቸው (ገፅ 85፣ 96-97)፡፡

ይህ ሰው ነው በሳውዲው ንጉስ በኢብን ሳውድ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድሮ የነበረው፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ ልኡካን ባዶ እጃቸውን እንዲመለሱና ለጣሊያን ጦርነት መሰረታዊ የሆኑ ምቹ ሁኔታዎች እንዲመቻቹ አድርጎ በዚያን ጊዜ ለተከሰተው የኢትዮጵያ ውድቀት ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡

አርስላንም ከፍተኛ ሚናን ተጫውቷል ፕሮፌሰር ኢርሊች እንደሚለው ከሐምዛ የበለጠ እርሱ በዓለም ውስጥና በአረብ አገር ሁሉ ይዞርና የእስላማዊ አረብ አንድነትን ሚሊታንታዊ አንድነት ያደራጅ ነበር፡፡ በእርሱም ዓይን ውስጥ እስላምና እና አረብነት የማይነጣጠሉ ነገሮች ነበሩ፡፡ አርስላን ከዚህም የተነሳ የአረቡን ዓለም አንድ በማድረግ በኩል የሚቀጥለው ካሊፍ ኢብን ሳውድ እንደሆነ በተለያየ መንገድ ይናገርና ይገልፅ ስለነበር፣ እራሱ ኢብን ሳውድ ሐሳቡን በግልፅ ባይቃወመውም ከአርስላን ጋር በጣም የቀረበ ግንኙነትን መስርቷል፡፡ አርስላንም የኢብን ሳውድን ስም ታላቅ ለማድረግ እጅግ በጣም ጥረትን ያደርግ የነበረ በመሆኑ በ1929 የሳውዲ ዜግነት ፓስፖርት እንዲሰጠው ንጉሱ አድርጓል፡፡

ይህም ብቻ ሳይሆን አርስላን በአረቡ ዓለም ውስጥ የጣሊያንም ወኪል ሆኖ ይሰራ ነበር፡፡ አርስላን አርቦች በመካከለኛው ምስራቅ ውስጥ ድል እንዲያደርጉ ከተፈለገ ጣሊያንን መጠጋት እንዳለባቸው ብዙ ይቀሰቅስ የነበረ ሲሆን በዚህም ቅስቀሳው ኢትዮጵያ የምትባለው አገር ሙሉ ለሙሉ ብትወድም ምንም ቅር እንደማይለው ነበር፡፡ እርሱ እራሱ በ1928 ለራስ ተፈሪ በጻፈው ደብዳቤ ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሙስሊሞች መሰረታዊ መብት እንዲጠበቅ ጥያቄን አቅርቦ ነበር፡፡ ለጥያቄውም ምንም የደብዳቤ መልስም ስላልተሰጠው (እንደ በቀል አድርጎ) በ1930ዎቹ ሁሉ ውስጥ ንጉሱን ኃይለስላሴን ይጠራ የነበረው ተፈሪ በማለት ነበር፡፡ በ1933 ላይ ደግሞ “የኢትዮጵያ ሙስሊሞች” በሚል ርዕስ ስር እጅግ ረጅም ጽሑፍን ጽፎ ነበር በዚያም ውስጥ ከአረብ ምንጭ የተወሰዱትን የግራኝ መሐመድን የጦርነት ዘገባዎች በማስቀመጥ የአፍሪካ ቀንድ እራሱን የቻለ ክብርና ድልን ይጋራል ብሎ ነበር፡፡

ከዚያም በፍጥነት በመቀጠል፣ ወዲያውኑ ሙሶሊኒን በማድነቅ እርሱ (ሙሶሊኒ) እስልምናን ከኢትዮጵያ ጭቆና ነፃ የሚያወጣ ነው በማለት እንደ እስልምና አዳኝ አድርጎ ማቅረቡን ቀጠለ፡፡ በ1934 ጥቅምት ላይ አርስላን ኤርትሪያን ጎብኝቶ ከተመለሰ በኋላ በ”La Nation Arabe’ ላይ ሙሶሊኒ እስልምናን በጥሩ ሁኔታ እንደያዘው በማድነቅ ረጅም ጽሑፍን ጽፎ ነበር፡፡ በ1935 ጥር ላይ ደግሞ እንደገና በዚያው በ”La Nation Arabe’ ላይ ለሕትመት ያቀረበው ሌላው ጽሑፍ ላይ ለኢትዮጵያ ማስጠንቀቂያን አስቀምጦ ነበር ይህም ለጅማና ለሐረር የራስን በራስ ማስተዳደር ስልጣን እንድትሰጥ አለበለዚያ ግን እንደምትወድም አስጠንቅቆ ነበር፡፡ ይህ ሰው ጣሊያንን፣ ኢትዮጵያንና፣ እስልምናን በተመለከተ ከጻፋቸው እጅግ በጣም ብዙ ጽሑፎች መካከል፤ ኢትዮጵያ በጣሊያኖች እጅ ውስጥ ከወደቀችም በኋላ እንኳን የጻፈው አስገራሚ ነበር ለመጥቀስም ያህል በAl-Jami’a al-Arabiyya በፍልስጥኤም ጋዜጣ ላይ ያወጣው ጽሑፍ በመጋቢት 4 1935 “ኢትዮጵያን ለመደገፍ የሚፈልጉ ሁሉ በመጀመሪያ መመልከት ያለባቸው ሙስሊሞች እንዴት በአገሪቱ ውስጥ እንደሚኖሩ፤ ከኢትዮጵያውያን እጅ ምን እንደሚቀበሉና፤ እነርሱ (የኢትዮጵያ ሙስሊሞች በኢትዮጵያ ማለቱ ነው) እዚያ እንደሚሰቃዩት ማንም ሙስሊም በየትኛውም አገር ተሰቃይቶ አያውቅም” በማለት ነበር፡፡ ቀጥሎም በአገሪቱ ውስጥ ያሉት ስድስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን በጭቆና እንደሚኖሩ ነበር ይህም ከአውሮፓውያን ኮሎኒያሊዝም በከፋ ሁኔታ ነው በማለት አስቀምጦት ነበር፡፡ አርስላን ከኢብን ሳውድ ጋር በጣም ቅርብ ስለነበር ኢብን ሳውድ ኢትዮጵያን በተመለከተ መጥፎ ሐሳቡን ያገኘው ከ”አብድ አል ዋሃብ’ ብቻ ሳይሆን ከአርስላንም ጭምር ነበር ማለት ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ተደማምረው ነበር ኢብን ሳውድ ከዚህ በፊት የተጠቀሰውን የቁጭት ንግግር በመናገር በሚያዝያ ወር ለወዳጅነት ግንኙነት ምስረታ የተላከውን የኢትዮጵን ቡድን አሳፍሮ ባዶ እጃቸውን እንዲመለሱ ያደረገው፡፡

ኢብን ሳውድና ሙሶሊኒ

የኢትዮጵያ ልኡካን ከተመለሱ አንድ ወር በኋላ ነበር የሳውዲ ልኡካን ወደ ሮም በጣሊያን ልዩ መርከብ ጉዞ አደረጉ፣ ልዑል ሳውድ እና ሐምዛ ነበሩበት፡፡ ግንቦት 20 ሮም ደርሰው ከፍተኛ አቀባበል ተደረገላቸው፣ ልዑል ሳውድ ከጣሊያን ንጉስና ከሙሶሊኒ ጋር እንደተገናኘ ሙሶሊኒ በአድናቆት የተናገረው ነገር የኢትዮጵያን ልዑካን እንዴት አሳፍረው እንደመለሷቸው ነበር፡፡ ከዚያም የተወሰኑ ስምምነቶች ተደርገዋል በመሆኑም ሙሶሊኒ፡

 • የእስላሞች ወዳጅ እና በኢትዮጵያ ውስጥ በክርስትያን መንግስት የጭቆና ቀንበር ስር ያሉት ሙሰሊሞች (የበላይ) ጠባቂ እንደሆነ፡፡
 • ሳውዲ ከየትኛውም አቅጣጫ የሚመጣውን ፀረ ጣሊያን ቅስቀሳን እንድታግድ እንዲሁም በሶማሊያና በኤርትሪያ የሚደረገውን የጣሊያንን ወታደራዊ ግንባታ በሰራተኞች ምልመላና በበጎ ፈቃደኞች እንድትረዳ፡፡
 • ሳውዲዎች ለጣሊያን ሰራዊት ምግብን እንደሚሸጡ፡፡
 • ለዚህም ምላሽ ጣሊያን የሳውዲን የአየር ኃይል እንደምትገነባ እንዲሁም ለሳውዲዎች ክፍያዋን በጦር መሳሪያ እንደምታደርገው፣ በተለይም ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ጦርነት ካለቀ በኋላ፡፡
 • በመጨረሻም ሳውዲ አረቢያ በኢትዮጵያና በጣሊያን መካከል ያለውን ግጭት የሁለት ክርስትያን አገር ግጭት እንደሆነ አድርጋ እንድታየውና በስተውጭው በሁለቱ አገሮች መካከል ባለው ጦርነት ላይ ገለልተኛ እንደሆነች እንደሚታይ ተስማሙ፡፡
 • ከዚህም የተነሳ ማንኛውንም ዓይነት የዲፕሎማቲክ ግንኙነት ሳውዲ አረቢያ ከኢትዮጵያ ጋር እንደማታደርግ ተስማማ፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ጦርነቱም ከተጀመረ በኋላ እንኳን ከሳውዲ ጋር ግንኙነትን ለማድረግ ብዙ ያልተሳካ ሙከራዎችን አድርጓል በተደጋጋሚም ሳውዲ አረቢያ ከኢትዮጵያ ጋር የወዳጅነት ግንኙነት ለማድረግ ያሳየችው ምንም ዝንባሌ አልነበረም፡፡

ሙሶሊኒና የሳውዲው የግመሎች ግዢ

በግንቦቱ ስምምነት መሰረት የሳውዲና የጣሊያኖች ግንኙነት በጣም እየተቀጣጠለ ሄደ፤ በዚያው ወር የጣሊያን ወኪል የሆነውና በጣሊያን የወታደራዊ ስለላ ውስጥ የሌተናንት ኮሎኔልነት ማዕረግ ያለው “ሴልሶ ዖዴሎ” ባለቤቱና ሴት ልጃቸው ጅዳ ደረሱ፡፡ እርሱም እራሱን የተለያዩ የጣሊያን የንግድ ድርጅቶች ወኪል እንደሆነ አድርጎ አቀረበ፡፡ እርሱም ወዲያውኑ የጅዳ ሕይወት ማዕከል ሆነና ከምሁራን እንዲሁም ከያሲን ጋር ጥብቅ ወዳጅነትን መሰረተ፡፡ በሐምሌም ወር ዖዴሎና ያሲን በኤርትራ ውስጥ እየተከማቸ ላለው የጣሊያን ሰራዊት አስፈላጊ ስለሆኑት የ12,000 ግመሎች ለጣሊያን የመግዛት ጉዳይ ላይ ውይይት አደረጉ፡፡ “ሴልሶ ዖዴሎም” ከመደበኛ ዋጋቸው ሦስት እጥፍ እንደሚከፍል ሐሳብን አቀረበ፡፡ ዓለም አቀፉ ውጥረት እየተፋፋመ ነበርና ሳውዲ አረቢያ ከመቼውም በላይ ከሙሶሊኒ ጋር ባደረገችው ድርድር ብሪቴንን የሚያስቆጣና በመካከላቸው ማለትም በብሪቴንና በጣሊያን ጦርነት ያስከትላል በማለት በጣም ተጨንቃለች፡፡ በዚህም ምክንያት ከሳውዲ የጦር ወታደር እንዳይመለመል አግዳለች፣ ይሁን እንጂ ሌሎች ነገሮች የምግብ ግዢዎችና ግመሎች ግዢዎች ላይ ምንም ችግር አልነበረም፡፡

በዖዴሎም አማካኝነት ለጣሊያኖች አትክልቶች ይሸጡላቸው ነበር፣ ምፅዋ ላይ በሚደርሱበት ጊዜ ከጥቅም ውጭ ይሆኑ የነበረ ቢሆንም፡፡ አሁን የጣሊያን ጦር መሳሪያዎች የሚፈልጉት ግመሎችን ነበር፤ ለጦርነት የሚደረገው ዝግጅት እንደቀጠለ ከባድ የሆኑ የጦር መሳሪያዎችን ማጓጓዝ በጣም ችግር እንደነበረ በጣም ግልፅ እየሆነ መጥቷል፡፡ በኢትዮጵያ ተራራዎች አካባቢዎች መሳሪያዎችን ለማጓጓዝና አስፈላጊ ነገሮችን ለማግኘት የጣሊያን ሰራዊት በግመሎች ላይ መደገፍ ነበረበት፡፡ በእርግጥ ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላም እንኳን የተረጋገጠው ነገር የግመሎች አስፈላጊነት ነበር፡፡

በሐምሌ ወር ኢብን ሳውድ በየወሩ 300 ግመሎች በዖዴሎ በኩል እንዲሸጥ ቀስ በቀስ የተደረገውን ስምምነት አፀደቀው፡፡ ነገር ግን ሼክ ያሲን ተጨማሪ ግመሎች እንዲሸጡ በጣም ይገፋፋ ነበር፡፡ ከጣሊያን ጋር የሚደረገውን ድርድር እንዲጠናከር የሚያደርጉት እርሱና ሐምዛ ነበሩ እርሱም በግሉ ከግመሎች ሽያጭ ድርድር የሚያገኘው ጥቅም ነበር፣ ያሲን በመጨረሻ ዖዴሎን ከኢብን ሳውድ ጋር ያገናኛው ሲሆን የ12,000 ግመሎቹ ግዢ እንዲከናወን ተደርጓል፣ በግዢውም 7 ፓውንድ ለመንግስት ግምጃ ቤት፣ 7 ፓውንድ ለባለግመሎቹ የናጅድ ጎሳዎች እና 1 ፓውንድ ለያሲን እንደ ደላላ እንዲከፈል ነበር፡፡ ሆኖም ግን ኢብን ሳውድ ብሪቲሾችን በጣም ፈርቶ ስለነበር ሽያጩን በተመለከተ እንደ ፀረ ብሪቲሽ ያዩት መሆንና አለመሆኑን እንዲያጣራ ያሲንን ወክሎትም ነበር፡፡ ብሪቲሾችም ቀደም ብሎ ኢትዮጵያን ለመሰዋት ባቀዱት ስልት መሰረት ምንም ግድ እንደሌላቸው ሲገልፁ ኢብን ሳውድም ጦርነቱ በኢትዮጵያና በጣሊያን መካከል ስለሆነ በሽያጩ ምንም ግድ እንደሌለው አሳይቶ ነበር፡፡

የብሪቲሾች መልስ ለኢብን ሳውድ ጣሊያን ስለሚያደርገው የጦር እንቅስቃሴ ምንም ችግር እንደሌለባቸውና በግመሎች ሽያጩም እንዳይጨነቅ ሲያደርጉ፤ ጣሊያንም ኢትዮጵያን ለመያዝ ለሚያደርገው ዘመቻ ሰፊ ዕድልን ሰጥተውታል፡፡ ስለዚህም ብሪቲሽና ፈረንሳይ ለኢብን ሳውድ ምክራቸው ጣሊያኖችን በትህትና እንዲይዛቸውና የግመል ሽያጭ ድርድሩ ምንም ሊያሳስበው እንደማይገባ ነበር፡፡ በእርግጥ እዚህ ላይ እራሳቸው ያወጡት አንድ ምስጢር ጣሊያን ከሱዳን ግመልን ሲገዛ ዝም እንዳሉትም በመጠቆም ነው፡፡ በመስከረም 20 የ32 ገፅ የግመሎች መግዛት ስምምነት ተዘጋጅቶ በሁለቱ አገሮች መካከል ተፈርሞ የግመል ግዢው ቀጥሏል፡፡ ሙሶሊኒ እንዲህ ዓይነቱን ትብብር ከሳውዲ ማግኘቱ ኢትዮጵያን ለመውረር ለሚያደርገው እንቅስቃሴ ሁሉ የጦር የበላይነትን እንዲቀዳጅ አድርጎታል፡፡

ኢትዮጵያን አሳፍሮ ፋሽስትን መርዳት

በጥቅምት 3 1935 ጣሊያኖች ኢትዮጵያን ወረሩ፡፡ በጥቂት ቀናት ውስጥ አድዋን ያዙ ነገር ግን በ1896 ጦርነት ላይ ድል ለተደረጉት በቀልን ለማድረግ ያቀዱት ዓላማ ወዲያውኑ አልተሳካላቸውም ይሁን እንጂ ቀደም ብሎ በተጠቀሰው በኃይለስላሴ ጉግሳ ክዳት የተነሳ የኢትዮጵያ ጦር በፍጥነት ተፍረክርኮ ነበር፣ የሽምቅ ተዋጊዎች ጣሊያኖችን ብዙም ስላላራመዷቸው መቀሌን የያዙት ህዳር 8 ቀን ነበር፡፡ ይህን እንጂ ብዙ ጦርነቶች እየተካሄዱ እያሉ የኃይለስላሴ መንግስት አሁንም የዲፕሎማቲካዊ እንቅስቃሴውን ጎን ለጎን በማካሄድ ሌሎች ልዑካንን ወደ ሳውዲ ላከ እነዚህም ብላታ አየለ ገብሩና ወጣቱ ሳይድ መሃመድ ማህዲ ነበሩ ሁለቱም በፈረንሳይ የተማሩና አረብኛንም በጥራት የሚናገሩ ነበሩ፡፡ ጉዟቸውም ከሳውዲ ጋር የወዳጅነት ስምምነት ለመፈራረምና በሳውዲ ከተማም በጂዳ ውስጥ አምባሳደር ቢሮ ለመክፈት ነበር፣ ልክ እንደቀድሞዎቹ ልዑካን እነዚህም የህዳርን ወር ሙሉ እስከ ታህሳስ 24 ድረስ ለብዙ ቀናት ያለምንም ምላሽ ሲጉላሉ ቆይተው ባዶ እጃቸውን ተመልሰዋል፡፡ ከጅዳም ታህሳስ 29 ሲነሱ ምንም የስምምነት ደብዳቤ አልያዙም ነበር፡፡

ይህ ሁሉ ሲሆን የመንግስታቱ ህብረት በወቅቱ አባል ለነበረችው ለኢትዮጵያ ምን አድርጓል? ከነበረው ዓለም አቀፍ ውጥረት የተነሳ ምንም ነገር አልተደረገላትም፡፡ በወቅቱም የመንግስታቱ ድርጅት አባል ያልነበረችው ሳውዲ አረቢያ በነፃነት ግመሎችን ለወራሪው ለማቅረብም ችላ ነበር፡፡ በታህሳስና በጥር 1936 ሐምዛ እንደዘገበው ጣሊያኖች ለአንድ ግመል አስከ 100 ፓውንድ ድረስ ለመክፈል ዝግጁዎች ነበሩ ብሎ ነው፡፡ ከየካቲት 1936 በኋላ ጣሊያኖች የጦር የበላይነትን ይዘው በጦርነቱ ላይ ድልን ለማግኘት የቻሉት በግመሎቹ አማካኝነት ብቻ ነበር፡፡  

በዚህ ሁሉ ወቅት ሳውዲዎች ገለልተኞች እንደሆኑ ቢናገሩም ጦርነቱ በከፊል የሙስሊም ሳውዲና የክርስትያን ኢትዮጵያ የነበረ መሆኑን ለማንም ለመረዳት አስቸጋሪ አይደለም፡፡ ይህንን የምናየው ሳውዲዎች ለኢትዮጵያ ልዑካን በተደጋጋሚ ካሳዩት መጥፎ አመለካከትና የጥላቻ ምላሽ እንዲሁም ከፋሽስት ጣሊያን ጋር ኢትዮጵያን ለማጥፋት ከመስማማታቸው እውነታ ላይ ነው፡፡

በውጤቱ ሙሶሊኒ በጣም ተደስቶ ኢብን ሳውድንና አማካሪዎቹን ከልብ አመስግኗል፡፡ የሳውዲ ህዝብ ስለ ኢትዮጵያ መከበብ ምን ይል ነበር? ጋዜጦቻቸውስ? ይህ ጥያቄ ድብልቅ መልስ ያለው ይሆናል የሳውዲ ሕዝብ መንግስቱን ከመደገፍ ሌላ ምን ሊያደርግ ይችላል ተብሎ ቢታሰብም የኢትዮጵያ መከበብ ላይ ሳውዲ ባደረገችው ድጋፍ አንዳንዶች ተቃውሞአቸውን ሲያሰሙ ተደምጠዋል፡፡ ይሁን እንጂ ጋዜጦቻቸው ይሰጡ የነበረው የተቃረነ ነገርን ነበር፡፡

የኢትዮጵያና የጣሊያን ጦርነት ከአጠቃላይ አካሄዱና ከታሪካዊ እውነታው እንደተገመገመው የዋሃቢው ሳውዲ መንግስትና የክርስትያን ኢትዮጵያ ጦርነት እንደነበር መናገር ስህተት አይመስልም፡፡ ከፕሮፌሰር ኤርሊች ታሪካዊ ጽሑፍ የምንገነዘባቸው ነጥቦች:

 • ሳውዲ የኢትዮጵያን ጥያቄ ችላ ብላ ለሙሶሊኒ እርዳታ ማድረጓ፤
 • የጣሊያን መንግስት ጦርነቱን ባደረገበት ወቅት 70,000 የሙስሊም ወታደሮች መጠቀሙ፤
 • ሙሶሊኒ በተደጋጋሚ በኢትዮጵያ ውስጥ የእስላም ነፃ አውጭ ሆኖ እራሱን ማቅረቡ፤
 • ለዘመናዊ የጣሊያን የጦር መሳሪያው ማጓጓዣና የጦር የበላይነት ለመያዙ 12,000 ግመሎችን ከሳውዲ በሳውዲው ንጉስ የበላይ ተቆጣጣሪነት ጣሊያን መግዛቱና መጠቀሙ ናቸው፡፡

በዚህ ሁሉ ውስጥ የኃይለስላሴ መንግስት በአገሪቱ ውስጥ ያሉትን ሙስሊሞች ለማስተባባር እንዲያውም አዲስ “የኢትዮጵያ መንግስት ሞዴል” መቀረፁን በማስተዋወቅ የተቻለውን ዲፕሎማቲካዊ እንቅስቃሴ ቢያደርግም የዋሃቢዝም ደጋፊዎች ከጣሊያን ወገን በመሆን አገሪቱን ለጠላት በመስጠት አገሪቱን ተዋግተው እንደነበር በታሪኩ ውስጥ ፍጥጥ ያለ እውነታ ነው፡፡

ከዚህ በላይ የቀረበው የፕሮፌሰር ኤርሊች ታሪካዊ እውነተኛና ገለልተኛ ዘገባ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የተለያዩና መሰረታዊ ጥያቄዎችን ማስነሳት አለበት፡፡ ለሚነሱትም ጥያቄዎች መንደርደሪያ ይሆኑ ዘንድ የሚከተሉት የማጠቃለያ ሐሳቦች ይጤኑ ዘንድ ያስፈልጋል እነዚህም፡-

 • ታሪክ የሚያሳየው በየጊዜው የተነሱ የኢትዮጵያ ንጉሶችና መሪዎች ከሙስሊም አገሮች ጋር ወዳጅነት እንመስርት ወይንም እንተባበር ጥያቄ ሲያነሱ በግልፅና በተዘዋዋሪ ይጠየቁ የነበሩት ሃይማኖት እንዲቀይሩ የነበረ መሆኑ፡፡
 • ጥንት ለጎንደሩ ንጉስ ፋሲለደስ በየመኖችና ቆይቶም በሱዳኖች ለአፄ ዮሐንስ የቀረቡት ጥያቄዎች ሁሉ “እንደ ነጃሺ እስላም” ብትሆኑ ከጎናችሁ እንቆማለን የሚል የነበረ መሆኑ፡፡
 • በሳውዲ የሚመራው የዋሃቢዝም እንቅስቃሴ ባለፈው ምዕተ ዓመት በጣሊያኖች አማካኝነት ከዚያም ቀደም ብሎ በኦቶማን ቱርክ ድጋፍ የተነሳው ግራኝ መሐመድ አገሪቱን የእስላም አገር ለማድረግ ከፍተኛ ትግል አድርጎ የነበረ መሆኑን፡፡
 • ጣሊያንም እራሱ በኢትዮጵያ የእስልምና ጠባቂ ነኝ ብሎ ጦር ይዞ ሲመጣ በአገሪቱ ውስጥ የነበሩትን እውነተኛ ዜጋዎች በማስጨፍጨፍ ትብብር ድጋፍ አብሮም መሰለፍ ላይ የተሰማሩት ሁሉ ሙስሊሞች የነበሩ መሆናቸው፡፡
 • በአሁኑ ጊዜ በሳውዲ መንግስት የሚመራው የዋሃቢዝም እንቅስቃሴ እና የተለያዩ የተቃውሞ ሰልፎችና ድጋፎች ታሪካዊ ጥልቅ አመጣጥ ያላቸው መሆኑ ናቸው፡፡

የዚህ ድረ ገፅ አዘጋጆ ፖለቲከኞች ወይንም የሆነ የፖለቲካ ድርጅት ደጋፊዎች አይደለንም ነገር ግን እንደማንኛውም የአገሪቱ ዜጋ የአገራችን ጉዳይ ያሳስበናል፡፡ ይህንን በተመለከተ የአንዳንድ ታዋቂ ግለሰቦችና ጋዜጠኞች እንዲሁም የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች የሃይማኖት ነፃነት ተደፍሯል በሚል ሰበብ የሚሰጡት አስተያየት ያስገርመናል፡፡

ስለዚህም በእነዚህ ታሪካዊ ጽሑፎች አማካኝነት ለኢትዮጵያውያን ሁሉ ታሪክ ምን ይመስል እንደነበረ ለማሳየት እንሞክራለን ዋናው ዓላማችንም የምናደርገውን አስተውለን እንድናደርግና “የጠላቴ ጠላት ወደጄ ነው” የሚል የተሳሳተ ድጋፍ ውስጥ እንዳንገባ ነው፡፡ በመሆኑም የአሁኑ የሙስሊሞች የተቃውሞ እንቅስቃሴ ዋና ዓላማው ምንድነው? በእርግጥ በአሁኑ ጊዜ ያለው መንግስት ሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ እየገባ ነውን? ወይንስ አገሪቱ በሰላም የሁሉም አገር ሆና እንድትኖር የበኩሉን ጥረት እያደረገ ነው?

ጎረቤቷን ኢትዮጵያን ለጣሊያን ወረራ አሳልፋ የሰጠችው ሳውዲ አረቢያ አሁንስ ምን እያደረገች ነው? ባላፈው የካቲት 27 በወጣው ሱዳን ቲሪቡን ላይ የቀረበው የሳውዲ አረቢያ ከፍተኛ ባለስልጣን ንግግር www.ethiomedia.com/addis/5677.html ምክንያቱ ምንድነው? ሳውዲ አረቢያ ኢትዮጵያን እስላም አገር ለማድረግ አሁንም የማትፈነቅለው ድንጋይ የላትም፡፡ በአገሪቱ ውስጥ ቁጥር የሌላቸው መስጊዶች በማሰራት፣ የቁርአን ማእከሎችና ሌሎች ማዕከሎችን በተለያዩ ቦታዎች በማቋቋም፣ እስልምና በአገሪቱ ውስጥ የብዙው ሕዝብ እምነት እንደሆነ ተደርጎ የተቀናበረ ቅስቀሳ በማሰራጨትና በዚህም በዚያም ትሞክራለች፡፡ ይህ ሁሉ አልሳካ ስላለ ወደ መንግስት ፍንቀላ ይህም አልሳካ ካለ በሱዳንና በግብፅ በኩል ኢትዮጵያን ለመውጋት አትመለስም! በዚህ ሁሉ የሳውዲ መንግስት ዓላማ ምንድነው? በኢትዮጵያ ውስጥ የተጨቆኑትን እስላሞች ነፃ ለማውጣት? ወይንስ በካኣባ ላይ ተነግሯል የሚባለው የጥንቱ ትንቢት  እንዳይፈፀም ሊኖር የሚችለውን ፍርሃት ለማጥፋት? ወይንስ የመጀመሪያ የእስላም ንጉስ ነጃሺን ገድላለች ተብላ በውሸት የተወነጀለችውን ክርስትያን ትባል የነበረውን ኢትዮጵያን ለመበቀል ነውን? ለነዚህ ጥያቄዎች መጪው የወደፊት ጊዜ የሚያሳየን ቢሆንም ያለፈው ታሪክም የሚነግረን ብዙ ምስጢር አለ፡፡

በመሆኑም በሚቀጥለው ጊዜ የዋሃቢ እንቅስቃሴና ኢትዮጵያ በሚል ርዕስ ላይ በ በፕሮፌሰር ኤርሊች መጽሐፍ ላይ የተመሰረተውን እውነተኛ ታሪካዊ ዘገባ እንመለከታለን፡፡

 

ለእስልምና መልስ አማርኛ  ዋናው ገጽ