ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ነውን? -2
ብዙ ሙስሊሞች ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ እንደሆነ ለመቀበል ይከብዳቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ኢየሱስ አምላክ ሳይሆን ነቢይ ብቻ ነው በማለት ይከራከራሉ፡፡ የመጽሐፍ ቅዱሱ ጌታ ኢየሱስ ግን ሰው የሆነ አምላክ ነው፡፡ ሰው የሆነውም በፈቃዱና ለሰዎች ካለው ፍቅር የተነሳ ነው፡፡
ባለፈው አምድ ላይ ለዚህ ጥያቄ የመጀመሪያውን መልስ ሰጥተን ነበር፣ ያም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በግልፅና ሰዎች በሚገባቸው መንግድ እኔ አምላክ ነኝ ማለቱን የሚገልፁትም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን በመመልከት ነበር፡፡ በዚህ አምድ ደግሞ በጥያቄ አንድ ላይ መመልከት ያለብንን ሁለተኛውን መልስ ነው፡፡
ጥያቄ አንድ ሁለተኛው መልስ
ሰዎች በሚገባቸው መንገድ እኔ አምላክ ነኝ ቢልም በአደባባይ ግን ሰዎች ሆይ! ስሙ እኔ እኮ አምላክ ነኝ አላለም ነበር፣ ይህ ያልተባለበት ብዙ ምክንያቶች አሉ፡፡ እርሱ አምላክ ስላልሆነ ሳይሆን ከሚከተሉት አስፈላጊ ምክንያቶች የተነሳ ነበር፡
· የመጀመሪያው በመጣበት ባህልና እምነት ውስጥ ሊፈጥር ከሚችለው የተምታታ ሁኔታ ለሰሚዎች በመጠንቀቅ ነበር፣
ሁላችንም እንደምናውቀው ሰዎች ሁሉ በአንድ ጊዜ የሚነገረው ነገር አይገባቸውም፣ ጊዜ ይፈልጋሉ ነገሮችም ሊምታቱባቸው ይችላሉ፣ ከዚህም በላይ ወደ የተለየና የተሳሰተ አመለካከትና እምነት ውስጥ የመግባትም ችግር ሊያጋጥማቸው ይችላል፡፡
ሞርሞኖች፣ የምስራቅ ዮሮፕ ልዩ እምነት ተከታዮች አምላክ ሰው የሆነው እኛ አምላክ እንድንሆን ነው እንዲሁም የአሁኑ ዘመን የእምነት እንቅስቃሴ የሐሰት አስተማሪዎች እንደሚሉት እኛ ትንንሽ አምላክ ነን፣ መንፈስ ነን በስጋ ውስጥ እንኖራለን የሚሉት ዓይነት የስህተት እንቅስቃሴ ሰዎች እንዳይገቡም ነበር፡፡
· በአይሁድ ባህል ማንም ስጋ የለበሰ አምላክ ነኝ ብሎ ቢናገር ብላስፌሚ ወይም ስድበ መለኮት ስለነበር ጌታ ኢየሱስ በአደባባይ አምላክ ነኝ አላለም ነበር፡፡
በአይሁድ ስነ መለኮት ወይንም ነገረ መለኮት መሰረት እግዚአብሔር የሚኖረው በሰማይ ነው፣ እግዚአብሔር መንፈስ ነው፣ እግዚአብሔር በሰው አካል የማይወሰን ነው፣ ስለዚህም ለአይሁዳውያን እኔ ነቢይ ነኝ፣ ከእግዚአብሔር ተልኬያለሁ ብትል ያምኑሃል መልአክ ነኝም እንኳን ብትል ችግር አይኖርባቸውም ይሆናል፣ ነገር ግን እኔ እግዚአብሔር ነኝ ብሎ መናገር ግን ሊቀበሉት የማይችሉት አስቸጋሪ ነገር ነው፣ በቀጥታም መምታታትን የሚያስከትል ነገር ይሆንባቸው ነበር፡፡
· ከዚህም ባሻገር ለጌታ ኢየሱስና ለአገልግሎቱ ከሚሰጠው ጥቅም ይልቅ ጉዳቱ ይበልጥ ነበርና ይህን አላለውም ነበር፡፡
· በእርግጥ በአይሁዳውያን ዘንድ ስለመሲህ የሚጠበቁ ነገሮች ነበሩ፣ ማለትም ከእግዚአብሔር ቃል ውጭ የጌታን ቃል ከመገንዘብ ውጭ በሆነ መንገድ የሚጠበቁ ነገሮች ነበሩ፡፡ እነርሱ ይጠብቁት የነበረው መሲህ የፖለቲካ መሪ፣ ብልጥግናና ሃብት ሰጪ፣ እስራኤልን እንደገና ገናና መንግስት አድራጊ፣ የሚል ነበር እንደምታዩት ሁሉ ነገር ከፖለቲካ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ማሻሻል ጋር የተያያዘ እንጂ ከግለሰብ መንፈሳዊ ነፃነትና ከመንግስተ ሰማይ እምነት ጋር የተያያዘ አልነበረም፡፡ ስለዚህም ጌታ ኢየሱስ ጊዜያዊ ተቀባይነት ለማግኘት በአይሁድ መንገድ፣ ፍልስፍና ግምትና አባባል ውስጥ እራሱን አላስገባም ነበር፡፡ እርሱ መንፈሳዊ ነፃ አውጪ ነው የመንግስተ ሰማይ አውራሽ ነው፣ በእርሱ የሚታመኑ ደግሞ ያለምንም ጥርጥር ከኃጢአት ይቅርታንና አዲስ ልብና መንፈስን ያገኛሉ፡፡
ጌታ ኢየሱስ በአደባባይ እኔ እግዚአብሔር ነኝ ያላለበትም ሌላው ምክንያት
· አይሁድ እግዚአብሔርን ሲጠቅሱ ወይንም ሲያነሱ የሚያነሱትና የሚጠቅሱት እግዚአብሔር አብን ነው፣ በብሉይ ኪዳን ስላሴ አንድ አምላክ የሚለው እውነት ስለሌለ ሳይሆን፣ ስለ ስላሴ ግልፅ የሆነ መረዳት ስላልነበራቸው ነው፣ ጌታ ኢየሱስ እግዚአብሔር አብ ሳይሆን ቃል የነበረውና በኋላ ስጋ የሆነው ዮሐንስ 1.1 እና 14 የእግዚአብሔር ልጅ ተብሎ የተሰየመው ስለሆነም ጭምር ነበር፡፡
ጌታ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ተብሎ የተሰየመበትን ምክንያትና እውነቶቹንም ሰፋ ባለመንገድና በራሱ እንመለከታቸዋለን፡፡ ነገር ግን እርሱ እራሱ እግዚአብሔር እንደሆነ ለደቀመዛምርቱ በትክክል ነግሯቸው እንደነበርና ያደርግ ከነበረውም ነገር ሁሉ ይህንን እንደተረዱ በኋላ ከሰበኩት ስብከት ከአስተማሩት ትምህርትከመሰከሩት ምስክርነት ሁሉ በጣም ግልፅ ነው፣ የሚከተለው ጥቅስ ይህን እውነት ለማየት ይረዳናል፡-
16 የእርሱን ግርማ አይተን እንጂ በብልሃት የተፈጠረውን ተረት ሳንከተል የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ኃይልና መምጣት አስታወቅናችሁ። 17 ከገናናው ክብር። በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው የሚል ያ ድምፅ በመጣለት ጊዜ ከእግዚአብሔር አብ ክብርንና ምስጋናን ተቀብሎአልና፤ 18 እኛም በቅዱሱ ተራራ ከእርሱ ጋር ሳለን ይህን ድምፅ ከሰማይ ሲወርድ ሰማን። 2 ጴጥሮስ 1.16-18
የአዘጋጁ ማሳሰቢያ
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ነው፣ የዚህ ግዙፍ ፍጥረተ ዓለም ፈጣሪ ነው፣ ለጥበቡና ለኃይሉ ወሰን የሌለው ነው፡፡ ነገር ግን የፈጠራቸው የሰዎችን ልጆች ወደ ዘላለም ሲዖል በመጓዝ ላይ በመሆናቸውና የሚያድናቸው ምንም ሌላ መንገድ ስለሌለ እራሱ የሰው አዳኝ ለመሆን ወደደ፡፡ ስለዚህም ሰዎች በኃጢአታቸው መቀበል የሚገባቸውን ቅጣት ለመቀበልና ስለ ሰዎች ሞቶ እነርሱን ከሞት ለማዳን እራሱን በፈቃዱ በሰው ሁኔታ ውስጥ አስገባ፡፡
ይህንን ያደረገው በፈቃዱ ነገር ግን ሰዎችን ለማዳን ነው፡፡ ሰዎችን ለማዳን የሰውን ስጋ መልበስና ለሰዎች ኃጢአት ንፁህ መስዋዕት ያስፈልጋልና ነው፡፡