በቁርአን ውስጥ የወንጀለኛ መቅጫዎች

M. J. Fisher, M.Div

ትርጉምና ቅንብር በአዘጋጁ

 

መግቢያና ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ንፅፅር

ቁርአን እራሱ ጥቂት የወንጀለኛ፣ ወንጀል መቅጫዎችን ይናገራል፡፡ በዚህ ምዕራፍ ውስጥ አስራ ስምንት ቁጥሮች ብቻ ተጠቅሰዋል፡፡ ሙስሊሞች የሚያከብሯቸው ሌሎች መጽሐፎች ውስጥ ማለትም ሃዲቶች የእስልምናን ሕግ የሻሩት እንዴት መቀጣት እንዳለባቸው እጅግ በጣም ዝርዝር የሆኑ ነገሮችን ይገልጣሉ፡፡

በቁርአን ውስጥ የተዘረዘረው ቅጣት አረመኔያዊ ነው፣ እጅግ በጣም ጭከና የተሞላበትና ሙስሊም ባልሆኑት ዘንድ እጅግ በጣም ኋላ ቀር ነው፡፡ ይህንን አመለካከት ተቃውመው ሲመልሱ፣ ሙስሊሞች (የሚሉት) እንዲህ ዓይነት ቅጣቶች በመጽሐፍ ቅዱስ የብሉይ ኪዳንም ነቢያት የታዘዙ እንደሆኑ በመናገር ነው፡፡ እግዚአብሔር በእስራኤላውያን መካከል ኃጢአት እንዲቀጣ ጥብቅ ቅጣቶችን እንዳዘዘ መናገሩ ትክክል ነው፡፡ ነገር ግን የጥንት የመጽሐፍ ቅዱስ አዋቂዎች እነዚህን ተግባራዊ በማድረግ እና በመተርጎም በኩል ጥበብንና ብልሃትን ይጠቀሙ ነበር፡፡ ለምሳሌም ያህል ምሳሌያዊው ‹ዓይን ለዓይን› በፍፁም በጥሬው ተወስዶ አይታወቅም ነበር፡፡ የጥንት ሽማግሌዎች ይህ ክፍል በግጥም መልክ የሚያስረዳው በፍርድ ቤት ፍትህ እኩል መሆን እንዳለበት እንደሆነ ነው፡፡ ስለዚህም አፈፃፀሙን ሰዎች ይገነዘቡ የነበረው (ሚዛናዊ ፍርድን ስለመስጠት) የሚያወሩ ክፍሎች መሆናቸውን ነበር፡፡

ምንም እንኳን በሙሴ ሕግ ውስጥ የሞት ቅጣት ታዝዞ የነበረ ቢሆንም በመጽሐፍ ቅዱስና በቁርአን መካከል እጅግ በጣም ከፍተኛ ልዩነቶች አሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ቶርቸርን ማለትም እንደስቅላት ያሉትን ወይንም ሴቶችን መምታትን በፍፁም አያነሳሳም፡፡ በቤተክስትያን ውስጥ ስነ ስርዓት (ዲሲፕሊን) አለ ነገር ግን የአካል ቅጣትን በፍፁም አያካትትም፡፡ አዲስ ኪዳንም የክፉ አድርጊዎችን ቅጣት አሳልፎ የሚሰጠው ለሕግ ባለስልጣናት እጅ ብቻ ነው ሮሜ 13.1-7፡፡

ቁርአን እንደሚከተለው ይናገራል፡-

አመንዝራዎች 100 ጊዜ ግርፋት፡- ዝሙትን ወይንም ከጋብቻ በፊት የግብረ ስጋ ግንኙነትን የፈፀሙ ወንዶችም ሴቶችም አንድ መቶ ጊዜ ይገረፋሉ፡፡ ለእነሱም ምንም ምህረት አይደረግላቸውም፡፡ ይህም በሙስሊሞች ቡድኖች ሊመሰከር ይገባዋል፡፡ ዝሙትን አድራጊዎች ለመጋባት የሚችሉት እንደዚህ ዓይነት ወንጀል ከሰራ ሰው ጋር ብቻ ነው ወይንም ሃይማኖት በማያምን ወይንም እስላም ካልሆነ ሰው ጋር ብቻ ነው 24.2፣3፡፡

የሐሰት ውንጀላ ሰማንያ ግርፋት፡- አንድ ሰው ጥሩ የሆነች ሴትን (ምንም ጥፋት የሌለባትን ሴት) በዝሙት ቢወነጅል እና ለዚህም አራት ምስክሮችን ማምጣት ባይችል ያ በሐሰት የወነጀለው ሰው ሰማንያ ግርፋት መገረፍ አለበት፡፡ ከዚያም በኋላ ምስክነት መስጠት አይችልም 24.4፡፡

አራት ጊዜ መማል፡- አንድ ሰው ሚስቱን ያለ ምስክር ቢከስ (ቢወነጅል) እሱ በራሱ ላይ አራት ጊዜ መማል አለበት ይህም የተናገረው ነገር ውሸት ከሆነ በራሱ ላይ እርግማን ነው እንዲሆንበት ነው 24.6-9፡፡

ለግድያ ወንጀል የሚደረግ በቀል፡- አንድ ሰው ሲገደል መበቀል ይፈቀዳል፣ ይህም በቀሉ ተመጣጣኝ እስከሆነ ድረስ ነው፡፡ ነፃ የሆነ ሰው ተገድሎ ከሆነ ነፃ የሆነ ሰው መገደል አለበት - ባሪያ ከተገደለ ባሪያ መገደል አለበት፣ ሴት ከተገደለች - ሴት መገደል አለባት፡፡ የተበደለው ክፍል ይቅርታን ካደረገ ግን የደም ካሳ ሊከፈለው ይገባል 2.178፡፡

እስልምናን መካድ፡- አማኞች የሙስሊም እምነታቸውን እንዲክዱ ቢገደዱ እና ቢክዱ ነገር ግን በልባቸው ውስጥ ቢያምኑ ምህረት ይደረግላቸዋል፡፡ እነዚያ ሙስሊም ከሆኑ በኋላ እስልምናን የሚክዱት የአላህ ቁጣ በእነሱ ላይ ይሆናል በጣምም ይቀጣሉ 16.106፡፡

ዝሙትን የሰሩ ሴቶች በቤት ውስጥ ይዘጋባቸው፡- አንድ ሴት ዝሙትን ለማድረጓ ተወንጅላ በአራት ምስክሮች ከተረጋገጠባት እንዲዚሁም ካመነች እስክትሞት ድረስ በቤት ውስጥ ዝጉባት፡፡ በተመሳሳይ ወንጀልም ሁለት ወንዶች ከተወነጀሉ መቀጣት አለባቸው ነገር ግን ቢፀፀቱና ስራቸውን ቢያሳምሩ ተውአቸው 4.15፣16፡፡

ዓመፀኞች ሴቶችን መምታት፡- ባለመታዘዝ የምትጠረጠር ሴት መገሰፅ አለባት እንዲሁም ብቻዋን መተኛት እና መመታት አለባት፡፡ ወደ መታዘዝም ሲመለሱ ተጨማሪ ቅጣት ሊሰጣቸው አይገባም 4.34፡፡ የመጽሐፍ ቅዱሱ ባለታሪክ ኢዮብ ሚስቱን በመምታት ግልፅ ያልሆነ መሐላን እንዲፈፅም እንደታዘዘ ቁርአን ይናገራል ‹በእጅህም ጭብጥ አርጩሜን ያዝ በርሱም (ሚስትህን) ምታ ማላህንም አታፍርስ (አልነው) ...› 38.44፡፡

የሌቦችን እጆች ቁረጥ፡- ስርቆትን የፈፀሙ ሴቶችም ወንዶችም ለፈፀሙት ወንጀል ሽልማት ይሆን ዘንድ እጃቸውን ቁረጥ፡፡ ይህም ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን ነው 5.38፡፡

ጭንቅላትን መቁረጥ እና አካለ ስንኩል ማድረግ፡- የማያምኑት ሰዎች ልብ እጅግ መፍራት አለበት ስለዚህም ሙስሊሞች በጀግንነት ማጥቃት አለባቸው እናም እራሶቻቸውን ቁረጡ ጣቶቻቸውንም በሙሉ ቁረጡ፡፡ እነሱን አካለ ስንኩል ማድረግ አላህንና መሐመድን መቃወም ከፍተኛ ቅጣትን እንደሚያስከትል ያሳያል፡፡ እነሱም ወደ ሲዖል ነው የሚሄዱት 8.12-14፡፡

መስቀል ወይንም አካለ ስንኩል ማድረግ፡- በመሐመድና በአላህ ላይ ጦርነትን የሚያደርጉት፣ ወይንም በምድሪቱ ላይ ስርዓተ አልበኝነትን ለማስፈን የሚፈልጉት መገደል፣ መሰቀል አለባቸው እጆቻቸው እና እግሮቻቸው በተቃራኒ መቆረጥ አለበት (ማለትም ግራ እግርና ቀኝ እጅ፣ ወይንም ቀኝ እግርና ግራ እጅ) ወይንም ከአገር መሰደድ አለባቸው፡፡ በዚህ ዓለም መዋረድ እና በሚመጣው ዓለም ደግሞ መውደም አለባቸው ይህም ሙስሊሞች ከመያዛቸው በፊት ንስሐ ከገቡት በስተቀር ነው፡፡ በእነሱ ሁኔታ አላህ ይቅር ይላቸዋል 5.33፣34፡፡

የአዘጋጁ ማሳሰቢያ፡

ከዚህ በላይ ተመርጠው በቀረቡት አስራ ስምንት የቁርአን ጥቅሶች መሠረት የእስልምና የወንጀለኛ መቅጫ ሕግጋት ምን ያህል ጭከና የተሞላበቸው መሆኑን እናስተውላለን፡፡ ቅጣቶቹ ትምህርት ሰጪዎች ሆነው ሰዎችን ወደ ንስሐና ወደ መመለስ የሚጣሩ አይደሉም፡፡

በማህበረ ሰብ ውስጥ ወንጀሎች እንዳይስፋፉ እና  ሕዝቡ በሰላም እንዲኖር ማድረግ የአንድ አገር ግዴታ ቢሆንም፣ ባለስልጣናትና ሕግ አስፈፃሚዎች በሚያወጡት ሕግ ወንጀለኞች መቀጣት ያለባቸው ሰብዓዊ መብታቸው ተጠብቆ ትምህርትንም እንዲያገኙ በሚያደርግ መልኩ ነው፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ወንጀለኛ ሚዛናዊ ቅጣት እንዲቀበል ቢያዝም የሩቅ ዓላማውና ግቡ ግን ሰዎችን ወደ ንስሐ መጥራትና ወደ እግዚአብሔር ስርዓትና እምነት እንዲመጡ ማድረግ ነው፡፡ የእግዚአብሔርንም ምህረትና ይቅርታ እንዲናፍቁና እንዲጠሙ ማመልከትም ነው፡፡ ይህንንም ሲያደርግ ሰው በኃጢአት የወደቀ ተፈጥሮ ያለው መሆኑን በማሳየት በእግዚአብሔር የፀጋ ኃይል ላይ እንዲታመን በመጥራትም ጭምር ነው፡፡

ስለዚህም በዚህም አጋጣሚ እንኳን አንባቢዎቻችንን በቅንነት የምንጋብዘው መጽሐፍ ቅዱስን በማግኘት እንዲያነቡና፣ በኃጢአተኝነታችን ሁልጊዜ ከምናሳዝነው ከእግዚአብሔር ጋር ልንታረቅ፣ ምህረትንም ልናገኝ የምንችለው እንዴት እንደሆነ የሚገልጠውን የፍቅር መልእክት እንድትገነዘቡልን ነው፡፡

ለምሳሌም ያህል በሮሜ መልእክት ላይ ብቻ የሚከተለውን እናገኛለን፡- ‹ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል። ይልቁንስ እንግዲህ አሁን በደሙ ከጸደቅን በእርሱ ከቍጣው እንድናለን። ጠላቶች ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ከታረቅን፥ ይልቁንም ከታረቅን በኋላ በሕይወቱ እንድናለን፤ ይህም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን አሁን መታረቁን ባገኘንበት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በእግዚአብሔር ደግሞ እንመካለን።› ሮሜ 5.8-11፡፡

የመልእክቱም ሐሳብ እኛ ኃጢአተኞች፣ የእግዚአብሔር ጠላቶች እንደነበርን፣ ከዚህም የተነሳ ከፍፁምና ቅዱስ እግዚአብሔር የሚጠብቀን ቅጣት እንደሆነ፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ለእኛ ባለው በትልቅ ፍቅሩ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ስለእኛ ቅጣት እንዲቀበል አድርጎ ለእኛ ምህረትን እንዳመጣልን ማሳየት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ምህረት የተገለጠልን ስለሆነ ወደዚህ ምህረት እንምጣ እግዚአብሔርም በልጁ በክርስቶስ በኩል ሙሉ ለሙሉ ይምረናል፣ ይቅርም ይለናል ከእሱም ጋር ለዘላለም በመንግስቱ ውስጥ እንኖራለን እግዚአብሔር በፀጋው እና በምህረቱ ይርዳን አሜን፡፡

 

የትርጉም ምንጭ: Criminal Punishments, Chapter 23 of "A Topical Study of the Qur'an From a Christian Perspective" by M.J Fisher, M.Div

ሙሉ መጽሐፉ በአማርኛ: ርእሳዊ የቁርአን ጥናት በክርስትና አይን ሲመረመር

 

ለእስልምና መልስ አማርኛ  ዋናው ገጽ